የጤና አገልግሎት ጥራትን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምርምር ስራዎች ላይ ሊያተኩሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የጤና አገልግሎት ጥራትን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምርምር ስራዎች ላይ ሊያተኩሩ ይገባል
አምቦ፤ ሕዳር 15/2018(ኢዜአ)፦ የጤና አገልግሎት ጥራትን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጥናትና ምርምር ስራዎች ላይ ማተኮር እንዳለባቸው የጤና ዘርፍ መምህራን አመለከቱ።
የጤና ትምህርት አሰጣጥን በማዘመን ብቁና ተወዳዳሪ ባለሙያ ማፍራት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ተካሄዷል።
በመድረኩ ላይ የተሳተፉት የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉ ኪታባ፣ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎትን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በዘርፉ ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ሀይል ማፍራት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ለተግባራዊነቱም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የሰው ሀይል ለማፍራት በተግባር የተደገፈ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ማካሄድ እንዳለባቸው አስረድተዋል።
የጤና ትምህርት አሰጣጥን ማዘመን መንግስት ተግባራዊ ያደረገውን የበሽታ መከላከልና አክሞ የማዳን የጤና ስራ ለማሳካትም መሰረት መሆኑን ተናግረዋል።
በአምቦ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት የተካሄደው የምክክር መድረክም የዚሁ አካል መሆኑን ጠቅሰው የአምቦ ዩኒቨርሲቲም የጤና ትምህርት አሰጣጥን በጥናትና ምርምር በማስደገፍ ከዘመኑ ጋር ማጣጣም ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በተለይም አምቦ፣ ጅማ እና የኖርዌይ ቪ.አይ.ዲ ዩኒቨርሲቲ በጋራ የጤና ዘርፍ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች የሚያደርጉትን የጥናትና ምርምር ስራዎች የህብረተሰቡን ችግር በተጨባጭ እንዲፈቱ የማማከር ስራዎችን በጋራ ያከናውናሉ ብለዋል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ረዳት ፕሮፌሰር አበበ አበራ በበኩላቸው፤ የጤና ትምህርትን ውጤታማ ለማድረግ የምሁራን እና ባለድርሻ አካላት ትብብር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በአምቦ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት የተካሄደው የምክክር መድረክም የጤና ትምህርት አሰጣጡን በተግባር በማስደገፍና የጥናት እና ምርምር ስራዎች የህብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ የፖሊሲ ሀሳቦች እንዲሆኑ የሚያግዝ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኖርዌይ ቪ.አይ.ዲ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ተስፋዬ ለታ (ዶ/ር)፤ የጤና ትምህርት አሰጣጥን ወቅቱ በደረሰበት ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማስደገፍ መሰጠቱ ብቁና ተወዳዳሪ የጤና ባለሙያ ለማፍራት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
በዚህም ዩኒቨርሲቲዎቹ የጀመሩት ትብብር ዘርፉን ለማሻሻል በጎ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።