ቀጥታ፡

በመናኸሪያው የተጀመረው የኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎት እንግልትን አስቀርቷል

ሆሳዕና፤ ህዳር 17/2018(ኢዜአ)፦ በሆሳዕና ከተማ በህዝብ መናኸሪያ የተጀመረው የኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎት በተሳፋሪ ላይ ሲደርስ የነበረን ያልተገባ የዋጋ ጭማሪና እንግልት ማስቀረቱን ተገልጋዮች ገለጹ። 

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ በበኩሉ ለህዝብ የሚሰጠው የትራንስፖርት አገልግሎት ዲጂታላይዝ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

መንግስት የትራንስፖርት ዘርፉን ማነቆዎች በመፍታት በህዝቡ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስና የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ  ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።


 

በዚህም በዲጂታል የታገዘ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት በህዝብ መናኸሪያዎች የኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎት በማስጀመሩ ለውጥ እየተመዘገበ መጥቷል።

ኢዜአ በሆሳዕና ከተማ የህዝብ መናኸሪያ ተገኝቶ ያነጋገራቸው ተሳፋሪዎችና አሽከርካሪዎች በመናኸሪያው የኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎት ትርፍ ሰው ከመጫንና ተጨማሪ ክፍያን በማስቀረት በተሳፋሪ ላይ ሲደርስ የነበረን እንግልት ማስቀረቱን ተናግረዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አቶ ወንድም ዳኜ  እንደገለጹት ፤ ከዚህ ቀደም በመናኸሪያው ትርፍ መጫንና ማስከፈልን ጨምሮ የተለያዩ እንግልቶች ይገጥሙ ነበር። 


 

በዲጂታል የተደገፈ አገልግሎት መስጠት ከተጀመረ ወዲህ ከትራንስፖርት አገልግሎቱ ጋር በተያያዘ ቀደም ሲል ሲገጥሙን የነበሩ  ችግሮች ተፈተዋል፤ አሰራሩም በቀጣይ መጠናከር አለበት ብለዋል።

አቶ አየለ ጊፊሶ የተባሉ ተሳፋሪ በበኩላቸው እንዳሉት በመናኸሪያው የተጀመረው የኢ-ትኬቲንግ አገልግሎት ተገቢ ያልሆነ ክፍያን ከማስቀረት ባለፈ በተሳፋሪ ላይ ሲደርስ የነበረን እንግልት አስቀርቷል።


 

ይሁንና የዲጂታል አገልግሎቱ በወረዳ ባሉ መናኸሪያዎች ባለመጀመሩ ከታሪፍ ውጭ ማስከፈል አሁንም እንዳለ ጠቅሰው ዲጂታል ትራንስፖርት አገልግሎቱ በሁሉም መዋቅሮች እንዲስፋፋ ጠይቀዋል፡፡

መንግስት ባስቀመጠው የታሪፍ ክፍያ መሰረት ማህበረሰቡን እያገለገሉ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በመናኸሪው የህዝብ ትራንስፖርት አሽከርካሪው ግዛቸው ሃይሉ ናቸው።


 

የኢ-ቲኬቲንግ መጀመር ከተራ አስከባሪዎች ጋር የነበራቸውን ያለመግባባት ችግር መፍታቱን ተናግረዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ  ኃላፊ መሀመድ ኑርዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በክልሉ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎትን ዲጂታላይዝ በማድረግ የተመዘገበውን ውጤት ለማጠናከር ይሰራል ብለዋል።


 

የኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎት በክልሉ በሚገኙ 23 መናኸሪያዎች ተግባራዊ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

አገልግሎቱ በትራንስፖርት ዘርፍ የነበሩ ብልሹ አሰራሮችን ከመቀነስ አኳያ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቅሰው፣ በቀጣይም  አገልግሎቱን በሁሉም መናኸሪያዎች የማስፋት ሥራ ይሰራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም