ቀጥታ፡

ቴክኖሎጂን በመጠቀም ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 19/2018(ኢዜአ)፦ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ገለጸ፡፡

የመስሪያ ቤቱ ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ መስሪያ ቤቱ የሀገሪቱን ውስን ሀብትና ንብረት ከብክነት ለማዳን እንዲሁም ብልሹ አሠራሮችን የመከላከል ተልዕኮውን አጠናክሮ መቀጠሉንም ተናግረዋል፡፡

በዚህም የፌዴራል መስሪያ ቤቶች የተበጀተላቸውን በጀት ለታለመለት ዓላማ ማዋላቸውን ኦዲት በማድረግ በማረጋገጥ ላይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በዚህም ፋይናንሻል ኦዲት፣ ክዋኔ ኦዲት፣ ልዩ ኦዲትን ጨምሮ በሌሎችም ጉዳዮች የኦዲት ስራ በመከናወን ላይ እንሚገኙ ገልጸዋል፡፡

መስሪያ ቤቱ ተጠያቂነትን ለማስፈንም ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከፍትህ ሚኒስቴር እና ከስነ ምግብርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ዋና ኦዲተሯ ጠቅሰዋል።

እንደ ኦዲት ግኝቱም መሸለም የሚገባቸው ተቋማት የሚሸለሙበትና ተጠያቂ የሚሆኑ ተቋማት የሚጠየቁበት አሠራር መዘርጋቱን ተናግረዋል፡፡

በኦዲት ግኝቱ መሠረት ከኃላፊነታቸው የተነሱና ተጠያቂ የሆኑ አመራሮች መኖራቸውን ለአብነት አንስተው፤ ከለውጡ ወዲህ የክዋኔ ኦዲት ቁጥርና የክትትል አቅም እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመዋል።

በቴክኖሎጂ የታገዘ ዲጂታል አሠራር ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲኖር፣ የገንዘብ ንክኪን ለማስቀረት እንዲሁም የአሠራር ስርዓትን በማዘመን ሙስናን ለመከላከል ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

ይህም ሙስናና ብልሹ አሠራሮችን ለመቆጣጠር ትልቅ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ጠቁመው፤ ወቅቱ የሚፈልገውና ዓለም እየሄደበት ያለው አቅጣጫ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

መስሪያ ቤቱም አሠራሩን ለማዘመን ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም