በኢትዮ ኮደርስ ስልጠና አለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል ዕውቀት ቀስመናል- የአሪ ዞን ሰልጣኞች - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮ ኮደርስ ስልጠና አለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል ዕውቀት ቀስመናል- የአሪ ዞን ሰልጣኞች
ጂንካ፤ ህዳር 24/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮ ኮደርስ ስልጠና አለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል ዕውቀት መቅሰማቸውን የአሪ ዞን የኢትዮ ኮደርስ ሰልጣኞች ተናገሩ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢንሺዬቲቭ በሀገሪቱ በዲጂታል ክህሎት የታገዘ ማህበረሰብን ለመፍጠርና ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያግዝ የኢትዮ -ኮደርስ ስልጠና በሁሉም አካባቢዎች እየተሰጠ ነው።
በስልጠናው ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ የአሪ ዞን ወጣቶችም ስልጠናው የዲጂታል ክህሎታቸውን በማሳደግ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርጋቸውን እውቀት አንደቀሰሙ ተናግረዋል።
በዞኑ የጂንካ ከተማ ነዋሪ ገላዬ ስምዖን፥ መንግስት በነፃ ለዜጎች ያመቻቸው የ5 ሚሊዮን ኮደርስ ስልጠና የዲጂታል ክህሎታቸውን በማሳደግ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርጋቸውን እውቀት ማግኘታቸውን ጠቁመዋል ።
በአሁኑ ወቅት የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕውቀትን ማሳደግ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል አቅም ለመፍጠር እንደሚያግዝ ጠቅሶ፥ ስልጠናው ዲጂታል ኢትዮጵያን በመገንባት ሀገራዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ለተጀመረው ጥረት አጋዥ መሆኑንም ገልጸዋል።
በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እና በዳታ አናሊስስ ኮርሶችን ያጠናቀቀው ገላዬ ስምኦን፥ በተለይ የዳታ አናሊስስ ኮርስ ለሁለተኛ ዲግሪ ማሟያ ለሚሰራው የመመረቂያ ፅሁፍ በእጅጉ እንዳገዛቸው አስረድተዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የጂንካ ከተማ ነዋሪው ወጣት ኬብሮም ዕቁባይ በበኩሉ የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ለወጣቱ ትልቅ እድል ይዞ መምጣቱን ተናግሯል።
ስልጠናው ጠቃሚና አለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል ዕውቀት እንደሚያስጨብጥ ገልፆ በዳታ ሳይንስ እና በፕሮግራሚንግ የሚሰጠውን ስልጠና በማጠናቀቅ ሰርተፊኬት ማግኘቱን ጠቁሟል ።
በአሪ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን መምሪያ የማህበራዊ ሚዲያ ሪፖርተር እየሩሳሌም ይንቲሶ በበኩሏ ስልጠናው ለጋዜጠኝነት ሙያ እጅግ አጋዥና የዲጂታል ዕውቀትን የሚያልቅ እንደሆነም ጠቁማለች።
በፕሮግራሙ ከሚሰጡ አራት ስልጠናዎች አርቲፊሻል ኢንተለጀንስና ዳታ አናሊስ ኮርሶችን ማጠናቀቋን ጠቁማ፥ በዌብ-ፕሮግራሚንግ እና የአንድሮይድ ማበልፀግ ኮርሶችን ለማጠናቀቅም ማቀዷን ገልፃለች።
ሌሎች ወጣቶችም የዚህ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማህበራዊ ሚዲያ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እየሰራች እንዳለችም ተናግራለች።
የአሪ ዞን ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይኼነው ተስፋዬ በበኩላቸው የኢትዮ ኮደርስ ስልጠናን ውጤታማ ለማድረግ ከሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀት በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገለጸዋል።
በዞኑ በሶስት ዓመታት ውስጥ ከ12 ሺህ 400 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች ስልጠናውን ለመስጠት መታቀዱን ጠቁመው ካለፈው ዓመት እስካሁን ከ4 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች ስልጠናው መሰጠቱን ጠቁመዋል።
ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ በተገኘ መረጃ መሰረት በክልሉ ከ235 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ለመስጠት እየተሰራ መሆኑም ተመላክቷል።