ማህበራዊ
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ
May 2, 2024 98
አዲስ አበባ ፤ ሚያዝያ 24/2016 (ኢዜአ)፦ በመዲናዋ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ። በአዲስ አበባ መጪውን የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ከ255 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ማዕድ የማጋራት መርሐ ግብረ ተካሂዷል።   ከንቲባ አዳነች በዚህ ወቅት የማዕድ ማጋራቱ እውን እንዲሆን ባለሀብቶች እና በጎ ፈቃደኞች ላደረጉት አስተዋፅኦ አመስግነዋል። በቀጣይም በመዲናዋ የተቸገሩ ወገኖችን መደገፍና የአቅመ ደካሞችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።   የአዲስ አበባ ኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር አብርሃም ታደሰ በበኩላቸው በከተማዋ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል። የባለሀብቶች፣ የተቋማትና እና የበጎ ፈቃደኛ ግለሰቦች ተሳትፎም እየጎለበተ መሆኑን ጠቅሰው፥ በዛሬው ዕለትም በሁሉም ክፍለ ከተሞች እና ወረዳዎች ማዕድ ማጋራት እየተከናወነ ነው ብለዋል። ድጋፍ የተደረገላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በበኩላቸው፥ ከተማ አስተዳደሩ፣ ባለሀብቶችና በጎ ፈቃደኛ ግለሰቦች ለበዓል መዋያ ላደረጉላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።    
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ከ350 ለሚበልጡ አቅመ ደካሞች እና አረጋዊያን ማዕድ አጋሩ
May 2, 2024 97
ሀዋሳ፤ ሚያዝያ 24/20216 (ኢዜአ)፦ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ከ350 ለሚበልጡ አቅመ ደካሞች እና አረጋዊያን ማዕድ አጋሩ። በድጋፍ ርክክቡ ወቅት አቶ ደስታ እንደገለጹት በዓልን በመረዳዳትና በአብሮነት ማሳለፍ የነባር እሴት መሰረት በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። ባለፋት አምስት ዓመታት የአቅመ ደካሞችን መኖሪያ ቤት ከማደስና በአዲስ መልክ ከመስራት ባለፈ ማዕድ በማጋራት ድጋፍ ሲደረግላቸው መቆየቱን አስታውሰዋል። እርስ በርስ መረዳዳት በበዓል ወቅት ብቻ ሳይሆን በሌሎች ጊዜያትም መጠናከር እንዳለበት የገለጹት አቶ ደስታ፤ በበዓል ወቅት በተለይ አቅመ ደካሞችን መጠየቅና ያለን ማካፈል እንደሚገባ ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች ውስጥ የሚገኙትን በመተጋገዝና በመተባበር ማለፍ ተገቢ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳደሩ አስገንዝበዋል።   የሲዳማ ክልል ወጣቶችና ሕፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ እመቤት ኢሳያስ በበኩላቸው፤ በማዕድ ማጋራቱ ለአረጋውያን፣ ለአቅመ ደካሞች እና እገዛ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል። ድጋፉ አቅመ ደካሞች በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ ታስቦ የተደረገ መሆኑን ያመለከቱት ወይዘሮ እመቤት፤ የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ በክልል ደረጃ ከ16 ሺህ 500 በላይ ለሆኑ ወገኖች ማዕድ የማጋራት ሥራ እንደሚሰራ ገልጸዋል። "ቢሮው ከበዓል ውጪም የመደጋገፍና የመረዳዳት ዕሴቶች እንዲጠናከሩ እየሰራ ይገኛል" ያሉት ሃላፊዋ፣ በክልሉ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት በርካታ ሰዎችን ተጠቃሚ መሆናቸውንም ጠቁመዋል። በበዓል ወቅት አቅም የሌላቸውን ወገኖች ማሰብ ለአብሮነት መጠናከር ሚናው የጎላ በመሆኑ በተለያዩ አካላት እየተደረጉ ያሉ ድጋፎች ተጠናክረው መጠቀል እንዳለባቸው ተናግረዋል።      
በድሬዳዋ በበጋ ወራት የበጎ ፍቃድ ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የተገነቡ ቤቶች ለአቅመ ደካሞች ተላለፉ
May 2, 2024 62
ድሬዳዋ፤ሚያዝያ 24/2016 (ኢዜአ) ፦ በድሬዳዋ አስተዳደር በበጋ ወራት የበጎ ፍቃድ መርሃ ግብር ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የተገነቡ ቤቶች ለአቅመ ደካሞች ተላለፉ። የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን በበኩሉ በአስተዳደሩ በበጋ የበጎ ፍቃድ የልማት ተግባራት ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የተለያዩ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን ተገልጿል። አስተዳደሩ የተለያዩ ተቋማትን በማስተባበር ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ አራት ቤቶች ናቸው ለአቅመ ደካሞች ተላልፈው የተሰጡት። ቤቶቹን ያስገነቡት ደግሞ የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ቅርንጫፍ፣ የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያና የቀበሌ መስተዳድሮች ናቸው። በቤቶቹ ርክክብ ላይ የተሳተፉት የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ካሊድ መሐመድ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በዘንድሮ የበጋ ወራት ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱና የማህበራዊ አገልግሎት ችግሮችን ያቃለሉ የልማት ስራዎች ተሰርተዋል። በበጋ ወራት በየደረጃው የሚገኙ ተቋማትንና በጎ ፍቃደኞችን በማስተባበር በተፋሰስ ልማት፣ በትምህርት፣ በደም ልገሳ ፣ በማዕድ ማጋራት፣ በአካባቢ ልማትና ፅዳት፣ በስፖርት፣ የተቸገሩ አረጋዊያን ቤቶች ግንባታና እድሳት እንዲሁም የትራፊክ አደጋ በመከላከል የተሰሩት ልማቶች ተጠቃሽ ናቸውን ብለዋል። ዛሬ በተቋማት የተቀናጀ ጥረት ተሰርተው የተላለፉት ቤቶችም የበጋ ወራት የበጎ ፍቃድ ልማቱ መሳያ መሆናቸውን በማከል። የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህላችንን እያጎለበቱ የሚገኙትን የበጎ ፍቃድ ስራዎችን በመጪው ክረምት ይበልጥ ለማሳደግ ዝግጅት ተጠናቋል ብለዋል። በበጋ የበጎ ፍቃድ ልማት ላይ በመሳተፍ ቤቶቹን ያስገነቡት የየተቋማቱ የአመራር አባላት በበኩላቸው ፤ የደሃውን ማህበረሰብ መሠረታዊ ችግሮች ለማቃለል እና የከተማውን ማህበራዊ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል። በ04 ወረዳ ገንደ ቆሬ በተባለው ቀበሌ ቤታቸው የተገነባላቸው ወይዘሮ ወሰኔ በጋሻው በትንሳኤ ዋዜማ ቤት ተገንብቶ በዓሉን በደስታ ለመቀበል በመታደሌ ታላቅ ደስታ ተሰምቶኛል ብለዋል። በወደቀ ትንሽዬ ጎጆ ከቤተሰቦቼ ጋር ለዓመታት በችግር ውስጥ አሳልፌያለሁ ያሉት ደግሞ በመልካ ጀብዱ ቀበሌ ቤት የተሰራላቸው አቶ ሰዒድ ሽኩር ናቸው። መንግስትና በጎ ፍቃደኞች የደሃውን እንባ የሚያብስ ልማት እያከናወኑ በመሆናቸው የደሃውን ህብረተሰብ ተስፋ እያለመለመ ይገኛልም ብለዋል።      
የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ያስገነባቸውን 10 የአቅመ ደካማ ወገኖችን ቤቶች አስረከበ
May 2, 2024 75
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 24/2016(ኢዜአ)፡- የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በሰበታ ሀዋስ ወረዳ ተፍኪ ከተማ ያስገነባቸውን 10 የአቅመ ደካማ ወገኖችን ቤቶች አስረክቧል። የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ የቤቶችን ቁልፍ ለአቅመ ደካሞች አስረክበዋል። ሚኒስትሩ እንዳሉት ባለሃብቶችን በማስተባበር ከዚህ በፊት ለኑሮ የማይመቹ የነበሩ ቤቶች ደረጃቸውን በጠበቀ ጥራት እንዲገነቡ ተደርጓል። ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ የመደጋገፍና ችግሮችን በጋራ የማለፍ ባህልን ማጠናከር አለብን ብለዋል። ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የምትመች ኢትዮጵያን በመገንባት ሂደት አቅመ ደካሞችንና ጧሪ የሌላቸው ወገኖችን ማገዝ እንደሚገባም ተናግረዋል። ቤታቸውን የተረከቡ ወገኖች በበኩላቸው፥ ሚኒስቴሩ እና ባለሃብቶች ምቹ ቤት ገንብቶ ስላስረከባቸው አመስግነው፥ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ እርስ በርስ መደጋገፍ ነው ብለዋል።  
በትንሳኤ በዓል ከ500 ሺህ በላይ አቅመ ደካሞችን ለመደገፍ እቅድ ተይዟል 
May 2, 2024 74
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 24/2016(ኢዜአ)፡- ለትንሳኤ በዓል በአዲስ አበባ የሚገኙና ድጋፍ የሚሹ ከ500 ሺህ በላይ አቅመ ደካሞችን በበጎ ፍቃድ ለማስፈሰክና ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት አስታወቀ ፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ተቀዳሚ ምክትል ሰብሳቢ ላይከሔራን መንክር ለኢዜአ እንደገለጹት በአዲስ አበባ 250 ሰንበት ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ። ሰንበት ትምህርት ቤቶቹ ከአገልግሎት ተልዕኳቸው ባሻገር የቤተክርስቲያኗ አስተምህሮ ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ በሆነው በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ በስፋት ይሳተፋሉ። የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶቹ በቋሚነትና በበዓላት ወቅት የሚደረጉ ሲሆን በዚህ ረገድ አቅመ ደካሞች በቋሚነት በገንዘብ ፣ በምግብ ፍጆታና በአልባሳት እንደሚደገፉ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ወጣቶችና ህጻናት መሰል ድጋፎች የሚደረግላቸው ሲሆን ትምህርት ማስተማርና የስራ እድሎችን ማመቻቸት ተጠቃሽ ናቸው። በዚህም በዘንድሮው የትንሳኤ በዓል ሰንበት ትምህርት ቤቶቹ እንደ ወትሯቸው ነዳያንን የማስፈሰክና ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን የመደገፍ በጎ ፍቃድ አገልግሎቶችን እንደሚያከናውኑ አስታውቀዋል። ለዚህም እስካሁን የድጋፍ አይነቶችን በየዘርፉ የመለየትና መሰል የቅድመ ዝግጅት ምዕራፎች የተጠናቀቁ ሲሆን ለትንሳኤ በዓል ከ500 ሺህ በላይ የሚሆኑ ወገኖችን ለማስፈሰክና ድጋፍ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል ነው ያሉት። ይህንን በተመለከተ ኢዜአ በደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን እና በማሕደረ ስብሃት ቅድስት ልደታ ማርያም ቤተክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶችን እንቅስቃሴ ጎብኝቷል። በደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን የአንቀጸ ብጹአን ሰንበት ትምህርት ቤት ሰብሳቢ ጳውሎስ ደምሴ አንደገለጹት የዓቢይ ጾምና ሰሙነ ህማማት ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ ሲል የከፈለው ዋጋና የመስቀል ጉዞ የሚታሰብበት ነው።   በዚህ ረገድ ቤተ ክርስቲያን ተምሳሌት መሆኗን ጠቁመው በተለይም ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ጥንታዊትና ነባር መሆኗን ገልጸው ከ1981 ዓ.ም ጀምሮ ይሰጥ የነበረው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እየዳበረ መምጣቱን አብራርተዋል። አሁንም የሰንበት ትምህርት ቤት አባላቱ የትንሳኤ በዓልን በተለያዩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ለማሳለፍ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል። ይህ የመደጋገፍና የመረዳዳት ልምድ በዓላትን ጠብቆ የሚከናወን አለመሆኑን ጠቁመው በተለይ በቋሚነት ለሚደገፉና ለሚታገዙ ወገኖች ሰብዓዊ ድጋፍ የሚደረግ መሆኑን አንስተዋል። የማሕደረ ስብሃት ቅድስት ልደታ ማርያም ቤተክርስቲያን የተክለ ሳዊሮስ ሰንበት ትምህርት ቤት ምክትል ሊቀመንበር ጎይቶም አለማየሁ በበኩላቸው የዓቢይ ጾም ከምግብ በመቆጠብ ከሚደረግ ጾም በተጨማሪም ልዩ ልዩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች የሚሰጡበት ነው።   በተለይም ጠያቂ ለሌላቸው ደራሽ በመሆን፣ የተቸገሩ ወገኖችን መርዳትና ሰብዓዊ ድጋፎችን ማድረግ እየሱስ ክርስቶስ ለፍቅር የከፈለውን ዋጋ በተግባር እንደማሳየት ይቆጠራል ነው ያሉት። በዚህም ሰንበት ትምህርት ቤቱ የዘንድሮውን የትንሳኤ በዓል ጨምሮ በተለያዩ በዓላት የምገባና ሌሎች ሰብዓዊ ድጋፎችን በማድረግ አጋርነቱን በተግባር እያሳየ መሆኑን ተናግረዋል። በዓላትን ጠብቆ የሚደረግ ድጋፍ ዘላቂ መፍትሔ እንዳልሆነ በመጠቆም ከጊዜያዊ ድጋፉ ጎን ለጎን ቋሚ የድጋፍ መርኃ ግብሮችን በማዘጋጀት የተለያዩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶችን እንደሚሰጡ አስታውቀዋል።              
በአብይ ፆምና ሰሙነ ህማማት የተማርነውን ፍቅርና ይቅርታ በእለት ተእለት ህይወታችን በተግባር ልንገልጸው ይገባል 
May 2, 2024 70
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 24/2016(ኢዜአ)፡- በአብይ ፆምና ሰሙነ ህማማት የተማርነውን የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅርና ይቅርታ በእለት ተእለት ህይወታችን በተግባር ልንገልጸው ይገባል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ምዕመናን ገለጹ። በአብይ ጾም ራስን ከምግብ በመቆጠብ ከሚደረግ ጾም በተጨማሪም ጠያቂ ለሌላቸው ደራሽ በመሆን፣ የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና ሌሎች ሰብዓዊ ድጋፎችን በማድረግ ማሳለፍ የተለመደ ነው። ኢዜአ በአዲስ አበባ በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት በመዘዋወር ያነጋገራቸው ምዕመናን በአብይ ፆምና ሰሙነ ህማማት የተማርነውን የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅርና ይቅርታ በእለት ከእለት የኑሮ ሒደት ማስቀጠል ይገባል ብለዋል። በተለይም በጾም ወቅት የሚደረግ መደጋገፍ፣ አብሮነትና ትህትና ሁል ጊዜ ተግባራዊ ሊደረግ የሚገባ ስለመሆኑም ገልጸዋል። አቶ ዳዊት አሰፋ ይቅርታ ከራስ ሰላምም ከቤት የሚጀምር መሆኑን በመግለጽ ሰውን እንደራስ መውደድን የሁልጊዜ ተግባራችን ልናደርገው ይገባል ብለዋል። ለዚህ ደግሞ የይቅርታ ልብና ሁሉን በእኩልነት የሚመለከት ሰብእና ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል። ወይዘሮ ዝናሽ አሰፋ በበኩላቸው ሰው ሆነን በመፈጠራችን ብቻ ሁላችንም እኩል መሆናችንን በመረዳት መቀራረብና አንድነታችንን ማጠናከር ያስፈልገናል ብለዋል።   ከአብይ ፆምና ሰሙነ ህማማት ወቅቶች ባሻገር እርስ በእርስ መተጋገዝ፣ መተዛዘንና መተሳሰብ በተግባር የምንኖረው የህይወታችን አካል ልናደርገው ይገባዋል ያሉት ደግሞ ፍቃዱ መልኬ ናቸው።   ሰናይት ስሜና እታፈራሁ ደርበው የተባሉ አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጅን ለማዳን የከፈለው መስዋዕትነት ያለ ልዩነት መሆኑን በመገንዘብ ሰው በመሆናችን ሰውነትን ማስቀደም ይጠበቅብናል ነው ያሉት።   ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ጌታነህ እሸቱ አብሮነትና መደጋገፍን የዕለት ተዕለት መገለጫ በማድረግ በብዙ ችግር ውስጥ የሚኖሩ ወገኖችን በዘላቂነት ማገዝ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።   መለያየት፣ መነቃቀፍና ጥላቻን ለማስወገድ የኢየሱስ ክርስቶስን ፍቅርና ይቅርታ በየእለት የህይወት ጉዟችን በተግባር ልንገልጸው ይገባል ሲሉ ምዕመናኑ አክለዋል፡፡  
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለተከናወኑት የ'ገበታ ለሀገር' ፕሮጀክቶች አንድ ሌላ ምዕራፍ ተከናወነ
May 2, 2024 119
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 24/2016(ኢዜአ)፡- ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለተከናወኑት የ'ገበታ ለሀገር' ፕሮጀክቶች አንድ ሌላ ምዕራፍ ተከናውኗል። በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በተዘጋጀ መርሃ ግብር ፕሮጀክቶቹን ለአማራ፣ ለኦሮሚያ እና ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት አስረክቧል። በተጨማሪም በገበታ ለሀገር የተገነቡ ሎጆችን ስራ የማስኬድ ተግባርን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በስካይ ላይት ሆቴል ተቋሙ በኩል እንዲወጣ የስምምነት ፊርማ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል። ከአራቱ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ሶስቱ (ሃላላ ኬላ ሎጅ፣ ጨበራ ጩርጩራ የዝሆን ዳና ሎጅ እና ወንጪ ኢኮ ሎጅ) በቅርቡ መመረቃቸው የሚታወሰ ሲሆን የጎርጎራ ፕሮጀክት ስራም በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ ትኩረት እና አመራር የተከናወነው የ’ገበታ ለሀገር’ ስራ የብሔራዊው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አንዱ ማዕዘን የሆነውን ቱሪዝምን የማሳደግ አላማ ያለው ነው። እነዚህ ፕሮጀክቶች በመጀመሪያው ፋይናንስ የማሰባሰብ ምዕራፍ የኅብረተሰቡን ድጋፍ በሰፊው ያሰባሰቡ፣ በግንባታቸው ምዕራፍ ግዙፍ የስራ ዕድል የፈጠሩ ብሎም ታላላቅ የመሰረተ ልማት ስራዎች እንዲከናወን በር የከፈቱ ናቸው። በፈጠራ የተሞላ የፕሮጀክት ስራ እና አስተዳደርና ፈጣን አፈፃፀም ምን ሊመስል እንደሚችል ማሳያም መሆናቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል። ቀጣይ የስራ ማስኬድ እና ማስተዳደር ተግባሩ ለብሔራዊ ሰንደቅ ተሸካሚው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሃላፊነት መሰጠቱም የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ ከማስቻሉም ባለፈ ለአለም አቀፍ የቱሪዝም መዳረሻነት ትውውቅ ከፍ ያለ ዕድል ይፈጥራል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ለ1 ሺህ 455 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ
May 2, 2024 80
ሶዶ ፤ሚያዝያ 24/2016 (ኢዜአ)፡- የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት የትንሣኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለ1 ሺህ 455 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ ማድረጉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ አስታወቁ። ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ እንዳሉት፤ የፊታችን ዕሁድ የሚከበረውን የትንሣኤ በዓል ምክንያት በማድረግ የክልሉ መንግስት ለ1 ሺህ 455 የህግ ታራሚዎች ይቅርታ ተደርጓል። የይቅርታው ተጠቃሚ የሆኑ ታራሚዎች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው መልካም ሥነ-ምግባር የነበራቸውና በሕግ የተደነገገው የይቅርታ መስፈርትን ያሟሉ መሆናቸው ጠቁመው፤ ይህም በክልሉ የይቅርታ ቦርድ ተጣርቶ የቀረበ መሆኑን ተናግረዋል። እንዲሁም ከተፈረደባቸው አንድ ሶስተኛ እና ከግማሽ በላይ የፍርድ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ መሆናቸውንም አስረድተዋል። እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ፤ ይቅርታው ከተደረገላቸው የህግ ታራሚዎች መካከል 1 ሺህ 435ቱ ከእስር የሚፈቱ ሲሆን፤ ሃያዎቹ ታራሚዎች ደግሞ የእስራት ጊዜያቸው የተቀነሰላቸው ናቸው። የይቅርታ ተጠቃሚ ከሆኑት የህግ ታራሚዎች መካከል 95ቱ ሴቶች ሲሆኑ፤ 1 ሺህ 360ዎቹ ወንዶች መሆናቸውም ተገልጿል። የይቅርታው ተጠቃሚ የሆኑ የህግ ታራሚዎች በቀጣይ ህይወታቸው የይቅርታን እሴት ተላብሰው ሰላምን በመስበክ፣ ለሕግ ተገዥ በመሆንና በልማት ስራዎች ጠንካራ ተሳትፎ በማድረግ ህዝብረተቡን ሊክሱ እንደሚገባ አቶ ጥላሁን አሳስበዋል ።  
ለሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን አቀባበል እየተደረገ ነው
May 2, 2024 80
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 24/2016 (ኢዜአ)፡-ሀገራዊ ጥሪውን ተቀብለው በሁለተኛው ምዕራፍ ወደ ሀገራቸው ለመጡ የሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቀባበል እየተደረገላቸው ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲመጡ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወቃል። ይህንኑ ተከትሎ ዛሬ ማለዳ በተለያዩ የአለም ክፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እየገቡ ነው።   ኢትዮጵያውያኑ ቦሌ ዓለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ እና ሌሎች የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ጥሪ በመጀመሪያው ምዕራፍ "ከባህላችሁ ጋር ተዋወቁ" በሚል ሃሳብ ተመሳሳይ መርኃ ግብር መካሄዱ ይታወቃል። ሁለተኛው ምዕራፍ "ከታሪካችሁ ተዋወቁ" በሚል መሪ ሃሳብ ነው እየተካሄደ ያለው። በቀጣይ የሚካሔደው ሶስተኛው ምዕራፍ" አሻራችሁን አኑሩ" በሚል ከሰኔ 2016 እስከ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ እንደሚከናወን ተገልጿል።    
በህገወጥ መንገድ 46 በርሜል ናፍጣና ቤንዚን ሲያዘዋውሩ የተገኙ ተጠርጣሪ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ
May 1, 2024 89
ሚዛን አማን ፣ሚያዚያ 23/2016 (ኢዜአ)፡- በሚዛን አማን ከተማ በህገወጥ መንገድ 46 በርሜል ናፍጣና ቤንዚን ሲያዘዋውሩ የተገኙ ሦስት ተጠርጣሪ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአስተዳደሩ ፖሊስ አስታወቀ። ሕገወጥ የነዳጅ አቅርቦትና ሽያጭ በከተማዋ በሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች ላይ እጥረት እንዲያጋጥም በማድረግ ተደጋጋሚ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እያስነሳ መሆኑንም ጠቁመዋል። የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ አዛዥ ረዳት ኢንስፔክተር አዳነ አለማየሁ በከተማዋ ምሽትን ተገን በማድረግ 35 በርሜል ናፍጣና 11 በርሜል ቤንዚን በህገ ወጥ መንገድ ሲያዘዋውሩ የተገኙ ሦስት ተጠርጣሪ ግለሰቦች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ተናግረዋል።   በህገ ወጥ መንገድ ቤንዚንና ናፍጣ የሚያሸሹና እጥረት እንዲከሰት የሚያደርጉ አካላት መኖራቸውን ፖሊስ ከህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሰረት ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው፤ በዚህም ተጠርጣሪ ግለሰቦቹ ሊያዙ መቻላቸውን አስረድተዋል። በዚህ መሰረት ትናንት ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ገደማ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-A38706 AA የሆነ አይሱዙ መኪና 11 ቤርሜል ቤንዝል ጭኖ ሊወጣ ሲል በተደረገው ክትትል ከነአሽከርካሪው መያዙን ተናግረዋል። በተጨማሪም ከምሽቱ ስምንት ሰዓት ገደማ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-B52395 AA የሆነ የአይሱዙ መኪና 35 ቤርሜል ናፍጣ በህገወጥ መንገድ ጭኖ ሊወጣ ሲል አሽከርካሪው ከነረዳቱ መያዙን ነው የገለጹት። በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉ ሶስቱም ተጠርጣሪ ግለሰቦች ላይ ምርመራ እያደረገ እንደሚገኝም አስረድተዋል። የቁጥጥርና ክትትል ተግባርን በማጠናከር በህገወጥ መንገድ ከማደያ የሚያወጡ፣ በበርሜልና በሌሎችም ቁሶች ነዳጅ የሚቸረችሩ አካላት ላይ የተጠናከረ እርምጃ እንደሚወሰድም ተናግረዋል። ህገወጥ የነዳጅ ግብይት በመበራከቱ የግብይት ስርአቱ እንዳይረጋጋ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ ኅብረተሰቡ ጥቆማ በመስጠት እና ከፖሊስ ጎን በመቆም እያሳየ ያለውን ትብብር እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።  
በደብረ ብርሃን ከተማ 69 መኖሪያ ቤቶች ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች ተላለፉ
May 1, 2024 75
ደብረ ብርሀን ፤ ሚያዝያ 23/2016(ኢዜአ)፡- የደብር ብርሃን ከተማ አስተዳደር የተለያዩ አካላትን በማስተባበር ያስገነባቸውን 69 መኖሪያ ቤቶችን ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች ማስተላለፉን አስታወቀ። የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት እንደገለጹት፤ አስተዳደሩ የተለያዩ አካላትን በማስተባበር ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ወገኖች የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ነው።   በዚህም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን፣ ባለሃብቶች እና ወጣቶችን በመስተባበር ከ10 ሚሊዮን ብር ወጪ 12 ብሎክ ያላቸው 98 መኖሪያ ቤቶችን ግንባታ እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል። እየተገነቡ ካሉ መኖሪያ ቤቶች መካከል ግንባታቸው የተጠናቀቁ 69 መኖሪያ ቤቶችን በዛሬው እለት ለተጠቃሚዎች ማስተላለፍ መቻሉን ተናግረው፣ ቀሪ ቤቶችም በቅርቡ ተጠናቀው ለተጠቃሚዎች ይተላለፋሉ ብለዋል። ተጠቃሚዎቹ የፋሲካ በዓልን በደስታ እንዲያሳልፉ ታሳቢ ተደርጎ ቤቶቹ መተላለፋቸውን ጠቁመው፣ ለቤቶቹ ግንባታ ህብረተሰቡ በገንዘብ፣ በጉልበትና በቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል መኖሪያ ቤቶችን በመገንባት የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታት የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አቶ በድሉ አስታውቀዋል። በተጨማሪም በከተማው የሚስተዋለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል በዚህ ዓመት በ196 ማህበራት ለተደራጁ 5 ሺህ 500 አባወራዎች የግንባታ ቦታ እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል። በከተማው ጠባሴ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ዮርዳኖስ ዓለሙ እንዳሉት፤ ከጎናቸው ደጋፊ በማጣት ከሁለት ልጆቻቸው ጋር በቤት እጦት ምክንያት ሲቸገሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል። ከተማ አስተዳደሩ በትንሳኤ በዓል ዋዜማ የዘመናት የመኖሪያ ቤት ችግራቸው በመፍታቱ መደሰታቸውንና ለተደረገላቸው እገዛም ምስጋና አቅርበዋል። ሌላዋ ተጠቃሚ ወይዘሮ ብዙአየሁ ዓለማየሁ በበኩላቸው፤ ባላቸው አነስተኛ ገቢ የቤት ኪራይ ከፍለው ለመኖር ተቸግረው እንደነበር አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት ችግራቸው በመፈታቱ አስተዳደሩን አመስግነዋል። በመኖሪያ ቤት ርክክቡ ላይ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችና የሚመለከታቸው አካላት እንዲሁም የእድሉ ተጠቃሚዎች ተገኝተዋል።        
በክልሉ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ለማሳደግ የፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ ነው - ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሰታ ሌዳሞ
May 1, 2024 110
ሀዋሳ ፤ ሚያዝያ 23/2016(ኢዜአ)፡- በሲዳማ ክልል የንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ለማሳደግ የሚረዱ ፕሮጀክቶች በመገንባት ላይ መሆናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ አስታወቁ ። በሀዋሳ ከተማ 80 ሺህ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርገው የፋራ-ሂጣታ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ ሥራ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በተገኙበት ተጀምሯል።   ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ሲዳማ በክልል ከተደራጀ በኋላ የክልሉ መንግስት ለመጠጥ ውሃ ተደራሽነት ትኩረት ሰጥቷል። በወቅቱ የክልሉ የንፁህ መጠጥ ውሀ ተደራሽነት 38 በመቶ እንደነበር ያወሱት አቶ ደስታ፤ በአሁን ወቅት 66 በመቶ ማድረስ የሚችሉ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ መሆኑን ተናግረዋል። የፋራ-ሂጣታ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክትም የዚሁ አካል እንደሆነ ጠቅሰዋል። "ለኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ተመራጭ በሆነችው ሀዋሳ እየጨመረ የመጣውን የነዋሪ ቁጥር ፍላጎት ጋር የሚመጣጠንና ደረጃውን የጠበቀ የውሃ አቅርቦት ተደራሽ ይደረጋል" ብለዋል። የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ መኩሪያ መርሻዬ በበኩላቸው፤ "ፕሮጀክቱ የፋራና ሂጣታ ቀበሌ ነዋሪዎችን የዓመታት የመጠጥ ውሃ ጥያቄ የሚመልስ ነው" ብለዋል።   አስተዳደሩ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ተጀምረው በወቅቱ ስራቸው ባለመከናወኑ የተጓቱ ፕሮጀክቶችን ገምግሞ ለህዝቡ ከሚሰጡት ጠቀሚታ አኳያ 790 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ለአገልግሎት እንዲበቁ ማድረጉንም ተናግረዋል። "ፕሮጀክቱ ከስድስት እስከ ዘጠኝ ወራት ባለው ጊዜ ግንባታው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ጥረት እናደርጋለን" ብለዋል። "በከተማዋ የአላሙራ ተራራን ተንተርሰው የተመሰረቱት የፋራና ሂጣታ ቀበሌዎች ካሉበት ከፍታ ቦታ አኳያ ለከተማዋ ሚሰራጨው የመጠጥ ውሃ ሳይደርሳቸው ለዓመታት ቆይተዋል" ያሉት ደግሞ የሀዋሳ ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳዊት ሌላሞ ናቸው።   ፕሮጀክቱ በቀበሌዎቹ የሚኖሩ 80 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመው፤ ከተማው ያለውን የመጠጥ ውሀ ሽፋን ከ80 በመቶ ወደ 84 በመቶ የሚያሳድግ እንደሆነ አብራርተዋል። ፕሮጀክቱ የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራን ጨምሮ በ232 ሚሊዮን ብር እንደሚገነባ አስታውቀዋል ። የፋራ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ማርቆስ ቡኡሻ "በአካባቢያችን የመጠጥ ውሀ ባለመኖሩ ከሌላ አካባቢ አንድ ጀሪካን ውሃ በሁለት ብር ገዝተን በማምጣት አልያም በጋሪ አዙረው ከሚሸጡ ሰዎች አንዱን ጀሪካን በ20 ብር በመግዛት እየተጠቀምን እንገኛለን" ብለዋል።   የመጠጥ ውሃ ችግራቸው የከፋ በመሆኑ ለዓመታት ቅሬታ ሲያሰሙ መቆያታቸውን አንስተው፤ ዛሬ ባገኙት ምላሽ መደሰታቸውን ገልጸዋል ። የሂጣታ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አማረ ብሩ በበኩላቸው፤ በውሃ እጦት ከሚያገኛቸው ድካምና እንግልት ባለፈ ለውሃ ወለድ በሽታዎች እንደሚጋለጡ ገልፀዋል።   ይህንን ችግራችንን የሚፈታልን የመጠጥ ውሃ ግንባታ ሊካሄድ በመሆኑ እጅግ ደስ ብሎናል " ብለዋል ። በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዐቱ ላይ የክልልና የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የባህል አባቶችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በአማራ ክልል የዳኝነትና ፍትህ ሥርዓቱን በማሻሻል ለህብረተሰቡ ፈጣንና ፍትሃዊ አገልግሎት ይሰጣል--አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ
May 1, 2024 96
ደሴ ፤ ሚያዝያ 23/2016(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የፍትህና የዳኝነት ስርዓቱን በማሻሻል ለህብረተሰቡ ፈጣንና ፍትሃዊ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ገለጹ። የአማራ ክልል የፍትህ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ስትሪንግ ኮሚቴ በደሴ ከተማ ከህብረተሰብ ተወካዮች ጋር መክሯል።   ዋና አፈ ጉባኤዋ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ በየደረጃው ከህዝብ ጋር በተደረጉ ምክክሮችና የዳሰሳ ጥናቶች በዘርፉ የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተትና የስነ ምግባር ግድፈቶች እንዳሉ ተረጋግጧል። እንዲሁም የቅንጅት ክፍተት፣ የአሳሪ ደንብና መምሪያዎች መኖራቸውን ገልፀዋል። ለዚህም ዋነኛው ችግር የዳኝነትና ፍትህ ስርዓቱ መሆኑን ጠቁመው፣ ሥርዐቱን ከባለድርሻ አካላት ጋር በማሻሻል ለህብረተሰቡ ፈጣን፣ ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህም ከህዝብ ጋር በመሆን ክፍተቱን ለይቶ ዘርፉን የሚያሻሽል ኮሚቴ በማቋቋም ወደሥራ እንዲገባ መደረጉን የገለጹት ወይዘሮ ፋንቱ፣ "በየደረጃው በመምከርና ፍትህን በማስፈን ለክልሉ ዘላቂ ሰላም በትኩረት ይሰራል" ብለዋል። ህብረተሰቡ በፍትህ ስርዓቱ እምነት እንዲኖረው፣ መንግስትና ህዝብ እንዲቀራረብ፣ የህግ የበላይነት እንዲከበርና በእርቅና ሽምግልና ችግሮች መፈታት እንዲችሉ ኮሚቴው እየሰራ መሆኑንም ወይዘሮ ፋንቱ አስታውቀዋል። የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አብዬ ካሳሁን በበኩላቸው እንዳሉት፤ በፍትህ ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን በማስተካከል ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት በየደረጃው ውይይት እየተደረገ ነው።   እስካሁን በተደረጉ ውይይቶች በዘርፉ ላይ የፍርድ መጓደል፣ የቅንጅት ክፍተት፣ የአቅም ውስንነት፣ የአገልግሎት አሰጣጥ እና ሌሎች ችግሮች እንደተስተዋሉ መለየታቸውንም ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ደንብና መመሪያዎችን ጭምር በማስተካከል የዳኝነት አገልግሎቱ ቀልጣፋና ፍትሃዊ እንዲሆን ጥረት እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ ለውጤታማነቱ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል። አቶ አብዬ እንዳሉት ለችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ሽምግልናና አበጋርን ጨምሮ ሌሎች ባህላዊ የእርቅ አሰራሮችም በህግ እንዲደገፉና ሚናቸውን ከፍ እንዲል ይደረጋል። የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ሀብታሙ አሊ በበኩላቸው እንደገለጹት የተጀመረው ውይይት ችግሩን ለማስተካከል ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፣ "ችግሩን ለመፍታት ለሚከናወኑ ሥራዎች ስኬታማነት የድርሻዬን ለመወጣት ዝግጁ ነኝ" ብለዋል።   ሌላዋ የውይይቱ ተሳታፊ ወይዘሮ ፋጡማ መሃመድ በበኩላቸው፤ ችግሮች በዘላቂነት መፍትሄ እንዲያገኙ ባህላዊ የእርቅ ስነ ስርዓቶች በህግ ጭምር ተደግፈው ወደ ተግባር ሊቀየሩ ይገባል ብለዋል።   በመድረኩ የክልል፣ የደቡብ ወሎ ዞን እና የደሴ ከተማ አስተዳደር አመራሮች እንዲሁም የከተማዋ ምክር ቤት አባላት፣ የፍትህ አካላትና ሌሎችም ተሳትፈዋል።  
ተቋማቱ የትንሳኤን በዓል ምክንያት በማድረግ ድጋፍ ለሚሹ 120 የማህበረሰብ ክፍሎች ማዕድ አጋሩ
May 1, 2024 121
ጂንካ፣ሚያዚያ 23/2016 (ኢዜአ)፡-የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሦስት ተቋማት መጪውን የትንሳኤ በዓል ምክንያት በማድረግ በጂንካ ከተማ ድጋፍ ለሚሹ 120 የማህበረሰብ ክፍሎች ማዕድ አጋሩ። አቅም ለሌላቸው የህብረተስብ ክፍሎች ድጋፉን በቅንጅት ያደረጉት ተቋማት የክልሉ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ የሴቶችና ህፃናት ቢሮ እንዲሁም የአሪ ዞን ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ናቸው። "በጎነት ለራስ ነው!" በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር ማዕድ ከማጋራት ባለፈ የአልባሳት ድጋፍ ተደርጓል። የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዋኖ ዋኖሌ፤ ድጋፉ መጪውን የትንሳኤ በዓል በችግር ውስጥ ካሉ ወገኖች ጋር በአብሮነት ለማክበር ታስቦ የተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።   በዚህም በጂንካ ከተማ ለሚገኙ 120 አረጋዊያን፣ አቅመ ደካሞችና አካል ጉዳተኞች ለእያንዳንዳቸው 5 ኪሎ ዱቄት እና 5 ሊትር ዘይት እንዲሁም የአልባሳት ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል። በዓላትን ነባሩን የመረዳዳት፣ የመተጋገዝና የመተሳሰብ ባህላችንን በሚያሳድግ መልኩ በጋራ ማክበር አብሮነታችንን ለማጠናከር ያግዛል ሲሉም ገልጸዋል። በክልሉ ችግር ውስጥ ያሉ ወገኖችን ታሳቢ ያደረጉ ሰው ተኮር የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን የገለጹት ዶክተር ዋኖ፣ "ልማቶቹ ከግብ እንዲደርሱ ሁሉም የራሱን አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይገባል" ብለዋል። የክልሉ ሴቶችና ህፃናት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ካሰች ኤሊያስ በበኩላቸው፣ "ዘመናትን የተሻገሩና የትስስራችን ምሶሶ የሆኑ የመረዳዳት፣ የመተሳሰብና የመተጋገዝ እሴቶች ጎልተው መውጣት አለባቸው" ብለዋል። ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ለሀገር በቀል ዕውቀቶች በተሰጠው ትኩረት በዓላትን በአብሮነት የማሳለፍ እንዲሁም አቅመ ደካሞችን የመጠየቅ ልምድና እሴቶች እየጎለበቱ መምጣታቸውን ተናግረዋል። ችግረኞችን መርዳትና የሀገር ባለውለታ አረጋዊያንን መጠየቅ የሰውነት ባህሪና የኢትዮጵያዊነት መገለጫ እንደሆኑም ወይዘሮ ካሰች አስታውሰዋል። በተለይ በችግር ምክንያት ወደጎዳና የሚወጡ ህፃናትን ከጎዳና ህይወት ለመታደግ ሁሉም የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ፤ ተቋማት በመቀናጀት አቅም ለሌላቸው ባደረጉት ድጋፍ መደሰታቸውን ገልጸው፣ ተሳተፎ ያደረጉ አካላትን አመስግነዋል። በቀጣይም በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖችን ታሳቢ በማድረግ በዞኑ የሚሰሩ ሰው ተኮር የልማትና የበጎ አድራጎት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል። በማዕድ ማጋራቱ ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል ወይዘሮ አመለወርቅ ጽጌ "ችግራችን ታይቶ በዓሉን በደስታ እንድናሳልፍ ድጋፍ በመደረጉ ተደስቻለሁ" ብለዋል። በዓል በመጣ ቁጥር ከችግራቸው በመነሳት እንደሚጨነቁ ያስታወሱት ወይዘሮ አመለወርቅ፣ "ዛሬ የተደረገልኝ ድጋፍ ወገን አለኝ ብዬ እንድኮራ አድርጎኛል" ሲሉ ገልጸዋል። በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ ድጋፍ ላደረጉላቸው አካላትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ምዕመናን ከሰሙነ ህማማት ፍቅርን ፣ትህትናን ፣ እርስ በርስ መረዳዳትንና አንድነትን ሊማሩ ይገባል- የሃይማኖት አባቶች
May 1, 2024 79
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 23/2016(ኢዜአ)፡- ምዕመናን ከሰሙነ ህማማት ፍቅርን፣ አንድነትን ፣ትህትናን፣እርስ በርስ መረዳዳትን በመማር ህይወትን በተግባር መኖር እንደሚገባቸው የሃይማኖት አባቶች ገለፁ ። ሰሙነ ህማማት ከሆሳዕና እሁድ ሰርክ ጀምሮ እስከ ትንሳኤ ሌሊት ያሉት ቀናትን ያካተተ ሲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ለማዳን የተቀበለውን ፍዳ ፣መከራና ሞት የሚታሰብበት ሳምንት ነው። የሳምንቱ ቀናት የራሳቸው የተለየ ስያሜ የተሰጣቸው ሲሆን በ "መርገመ በለስ" ተጀምሮ "ቅዳሜ ስዑር" በሚል ይጠናቀቃል፡፡ የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የነገረ-መለኮትና የስነ-ልቦና መምህር አባ ጌድዮን ብርሃነ ለኢዜአ እንዳሉት ሰሙነ ህማማት ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ ሲል የከፈለው ዋጋና የመስቀል ጉዞ የሚታሰብበት ነው።   ከብሉይ ኪዳን ወደ አዲስ ኪዳን እንዴት እንደተሸጋገርን በማሰብ የአዲስ ኪዳንን ከፍታና የክርስቶስን ውለታ የምናስብበት ሳምንት መሆኑን ገልፀዋል። ሰሙነ ህማማት ምዕመናን ምን ያህል ዋጋ እንደተከፈለላቸው በማሰብ በዋጋቸው ፀንተው ለመገኘታቸው ራሳቸውን የሚመረምሩበት የመንፈሳዊ ህይወት መመልከቻ መንፈሳዊ መስታወት ነውም ብለዋል። በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሐዋሪያዊት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አባ ጴጥሮስ በርጋ በበኩላቸው ሰሙነ ህማማት ኢየሱስ ክርስቶስ አለምን ለማዳን በፍቅር ህይወቱን በመስቀል የሰጠበት እለት የሚታሰብበት ነው ብለዋል።   በአብይ ፆም የኢየሱስ ክርስቶስ የሚታሰብ ሲሆን በሰሙነ ህማማት ደግሞ በልዩ ሁኔታ እግዚአብሄር ፍቅር ገዶት ለሰው ልጆች የከፈለው ውለታ የሚታሰብበት ወቅት መሆኑን አስረድተዋል። ህማማት ኢየሱስ ክርስቶስ አለምን ለማዳን በፍቅር ህይወቱን በመስቀል አሳልፎ መስጠቱንና የመዳን ምንጭና መሰረት መሆኑ የሚታሰብበት መሆኑንም ተናግረዋል።   ምዕመናን ከሰሙነ ህማማት ፍቅርንና ትህትናን በመማር እርስ በርስ መረዳዳትና አንድነትን ገንዘብ ሊያደርጉ እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶቹ ጠይቀዋል። ህማማት የችግር መፍቻና ራስን የመስጠት ምሳሌ የተማርንበት በመሆኑ ምዕመናን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተማሩትን ፍቅር በተግባር በመኖር መግለፅ እንዳለባቸውም አሳስበዋል። በሰሙነ ህማማት ጎልተው ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል ትህትና አንዱ መሆኑን በመግለጽ የእኔ ብቻ ትክክል ነው ከሚል እሳቤ በመውጣትና በመደማመጥ ችግርን መፍታት እንደሚገባ ተናግረዋል። ሰሙነ ህማማት የፈጣሪ ጥልቅ ፍቅር የሚታሰብበት በመሆኑ እርስ በርሳችንም በፍቅርና በመተሳሰብ መኖር ያስፈልገናል ብለዋል። ከሰላም የሚበልጥ ነገር አለመኖሩን የገለጹት የሀይማኖት አባቶች ሰላምን ለማረጋገጥ ለዕርቅ፣ ለይቅርታ ለአብሮነት ራስን ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።            
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ለ926 ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ
May 1, 2024 57
ቦንጋ ፤ ሚያዝያ 23/2016(ኢዜአ)፡- የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት መጪውን የትንሳኤ በዓል ምክንያት በማድረግ ለ926 ታራሚዎች ይቅርታ ማድረጉን አስታወቀ። የክልሉ ፍትህ ቢሮ ሀላፊ አቶ እሸቱ ጎዴቶ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፤ የክልሉ የይቅርታ ቦርድ በይቅርታ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ መሰረት መስፈርቱን የሚያሟሉ ታራሚዎችን ከመንግስት፣ ከህዝብና ከታራሚ ጥቅም አኳያ ሲመረምር ቆይቷል። በተደረገው ምርመራም በአጠቃላይ የይቅርታ ጥያቄ ካቀረቡ 978 ታራሚዎች መካከል መስፈርቱን ያሟሉ 926 ታራሚዎች ጥያቄያቸው ለክልሉ መንግስት ቀርቦ የይቅርታ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን ተናግረዋል። እንደ አቶ እሸቱ ገለጻ፤ የይቅርታው ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል፤ 920 ታራሚዎች ከእስር የሚለቀቁ ሲሆን፤ ስድስቱ ደግሞ የእስራት ጊዜያቸው የተቀነሰላቸው ናቸው። በከባድ ወንብድና፣ በግፍ ግድያ፣ በሙስና እንዲሁም በሴቶችና ህፃናት ላይ ወንጀል በመፈጸም የፍርድ ሂደት ላይ ያሉ ታራሚዎች የይቅርታው ተጠቃሚ አይደሉም። ታራሚዎቹ በማረሚያ ቤት በነበራቸው ቆይታ በአግባቡ ስለመታረማቸው፣ ስለመታነጻቸውና ስለመልካም ባህሪያቸው ምስክርነት የተሰጠባቸው መሆኑንም አመልክተዋል። ይቅርታ የተደረገላቸው ታራሚዎች ወደ ህብረተሰቡ ሲመለሱ ሰላምን ከመስበክ ባለፈ አምራችና ህግ አክባሪ ዜጋ ሆነው ህብረተሰቡን መካስ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዘበዋል። ህብረተሰቡም ግለሰቦቹ በአግባቡ ታርመውና ታንጸው ከእስር መለቀቃቸውን በመረዳት በበጎ ህሊና ተቀብሎ ማስተናገድ እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል።  
በክልሉ በትራንስፖርት ዘርፍ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሰራ ነው
May 1, 2024 271
አዳማ፤ ሚያዝያ 23/2016 (ኢዜአ):- በኦሮሚያ ክልል በትራንስፖርት ዘርፍ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ትራንስፖርት ኤጄንሲ ገለጸ። ኤጄንሲው ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር ያሰለጠናቸውን 419 የትራፊክ ደህንነት ተቆጣጣሪዎችን አስመርቋል። በዚሁ ጊዜ የኤጄንሲው ሃላፊ አቶ ዳንኤል ቸርነት እንደገለፁት በትራንስፖርት ዘርፍ የአቅርቦት ችግርን መነሻ ያደረጉ ብልሹ አሰራሮችና ሌብነት በስፋት ይስተዋላል። በዘርፉ በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው ብለዋል። ከዚህ ውስጥ የዘርፉ የአገልግሎት አሰጣጥን በቴክኖሎጂ አስደግፎ ለመምራት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። በዚህ ወቅትም የስምሪትና የታሪፍ ክፍያ ዲጂታል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በእስከ አሁኑ ሂደት በርካታ መናኸሪያዎች የዲጂታል አገልግሎቱ ተግባራዊ ማድረጋቸውን አክለዋል። የፍጥነት መቆጣጠሪያ ራዳርና የአልኮል መጠን መለኪያ መሳሪያዎችን ስራ ላይ በማዋልም የዘርፉን ችግሮች ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል። በምረቃው ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ የመንገድ ደህንነትና መድህን ፈንድ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አባሶ በበኩላቸው "ኢትዮጵያ ከሌሎች አገራት አንጻር በቁጥር ትንሽ ተሽካርካሪ ቢኖራትም በርካታ የትራፊክ አደጋ የምታስተናግድ አገር ናት" ብለዋል። ከሚደርሰው የትራፊክ አደጋ ውስጥ ደግሞ አብዛኛው በአሽከርካሪዎች ስህተት እንዲሁም በተሽከርካሪ የቴክኒክ ችግር ምክንያት የሚከሰቱ መሆናቸውን ገልጸዋል። በተጨማሪም መንጃ ፍቃድ አሰጣጥ ችግር እንዲሁም ፍጥነትና ቸልተኝነትም ለአደጋዎቹ መከሰት መንስኤ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ችግሩን ለመቀነስ በየአካባቢው ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የተቀናጀ ስራ የሚጠናከር መሆኑን አስገንዝበዋል። የስነ-ምግባር ችግር፣ የብቃትና የትራፊክ ደህንነት ቁጥጥር መላላት የትራፊክ አደጋ እንዲባባስ መንስኤ መሆኑን የጠቀሱት ደግሞ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ የትምህርትና ስልጠና ዳይሬክተር ኮማንደር ዲሪባ ለታ ናቸው። እየተበራከተ የመጣውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ኮሌጁ በአቅም ግንባታ ላይ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው የትራፊክ ደህንነት ተቆጣጣሪዎች ክህሎትና ስነ-ምግባር እንዲላበሱ ለማስቻል የበኩሉን እየተወጣ መሆኑንም ተናግረዋል። ዛሬ 419 የትራፊክ ደህንነት ተቆጣጣሪዎችን በትራፊክ ደህንነት፣ ቁጥጥርና ህግ ማስከበር የሙያ ዘርፎች አስልጥኖ ማስመረቁን ጠቁመዋል።  
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሰራተኞቹን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል
May 1, 2024 77
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 23/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሰራተኞቹን የስራ ትጋት የሚመጥን ምቹ ከባቢ የመፍጠርና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ቀዳማዊ መሰረታዊ የሰራተኛ ማህበር ዓለም አቀፍ የሰራተኞች ቀንን ከሁሉም የስራ ክፍሎች የተውጣጡ አመራሮችና ሰራተኞች በተገኙበት አክብሯል።   የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ከአየር መንገዱ ስኬት በስተጀርባ የአመራሩና የሰራተኞቹ ተቀናጅቶ መስራት ቁልፍ ሚና አለው። በዚህም ሰራተኞቹ በሙሉ አቅማቸው የሚያደርጉትን የስራ ትጋት የሚመጥን ምቹ ከባቢ ለመፍጠርና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ብለዋል። ለአብነትም በአየር መንገዱ የሰራተኞቹ ዋነኛ ጥያቄዎች ከነበሩት መካከል የቤት ችግርን ለመቅረፍ 5 ሺህ ቤቶችን በተቋሙ 30 በመቶ ቅድመ ክፍያ ግንባታ ማስጀመሩን ገልጸዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን ተጨማሪም 5ሺህ ቤቶች ለማስገንባት ከሪል ስቴትና የቤት አልሚዎች ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ገልጸዋል። በበረራ አስተናጋጆች አካባቢ ያሉ የስራ ሁኔታዎች ለማሻሻል በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን በማንሳት ይህን ተሞክሮ በሁሉም የስራ ክፍሎች ላይ ለመድገም እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል። አየር መንገዱ ስኬታማነቱን ይዞ እንዲቀጥል ለማስቻል ከጀርባ ሆነው ጠንካራ ስራዎችን ለሚሰሩ ሰራተኞች ቅድሚያ በመስጠት በቀጣይም በርካታ ማሻሻያዎች እንደሚደረጉ ዋና ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ቀዳማዊ መሰረታዊ የሰራተኛ ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ተካልኝ ተርፋሳ በበኩላቸው፣ እለቱ ሲከበር በአየር መንገዱ የሁሉም ሰራተኞች ሚና በጉልህ የሚታወስበት ነው ብለዋል።   በመሆኑም በሰራተኞችና በድርጅቱ አመራሮች መካከል ያለውን አዎንታዊ ግንኙነትን ለማስቀጠልና የሰራተኛውን መብት ለማስጠበቅ እየተወሰዱ ያሉት እርምጃዎች አበረታች መሆናቸውን ገልጸዋል። ይህም የሰራተኛውን ምርታማነት ለማሳደግና ለማስቀጠል እንዲሁም የኢንዳስትሪውን ሰላም ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ17 ሺህ በላይ ሰራተኞች ያሉት ሲሆን 5 ትልልቅ የስራ ዘርፎች የሚመራበት ግዙፍ ተቋም ነው። ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ቀን በኢትዮጵያ ለ49 ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ135 ጊዜ በመላው ዓለም እየተከበረ ይገኛል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም