የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሰራተኞቹን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 23/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሰራተኞቹን የስራ ትጋት የሚመጥን ምቹ ከባቢ የመፍጠርና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ቀዳማዊ መሰረታዊ የሰራተኛ ማህበር ዓለም አቀፍ የሰራተኞች ቀንን ከሁሉም የስራ ክፍሎች የተውጣጡ አመራሮችና ሰራተኞች በተገኙበት አክብሯል።


 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ከአየር መንገዱ ስኬት በስተጀርባ የአመራሩና የሰራተኞቹ ተቀናጅቶ መስራት ቁልፍ ሚና አለው።

በዚህም ሰራተኞቹ በሙሉ አቅማቸው የሚያደርጉትን የስራ ትጋት የሚመጥን ምቹ ከባቢ ለመፍጠርና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ለአብነትም በአየር መንገዱ የሰራተኞቹ ዋነኛ ጥያቄዎች ከነበሩት መካከል የቤት ችግርን ለመቅረፍ 5 ሺህ ቤቶችን በተቋሙ 30 በመቶ ቅድመ ክፍያ ግንባታ ማስጀመሩን ገልጸዋል።

ይህ ብቻ ሳይሆን ተጨማሪም 5ሺህ ቤቶች ለማስገንባት ከሪል ስቴትና የቤት አልሚዎች ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ገልጸዋል።

በበረራ አስተናጋጆች አካባቢ ያሉ የስራ ሁኔታዎች ለማሻሻል በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን በማንሳት ይህን ተሞክሮ በሁሉም የስራ ክፍሎች ላይ ለመድገም እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

አየር መንገዱ ስኬታማነቱን ይዞ እንዲቀጥል ለማስቻል ከጀርባ ሆነው ጠንካራ ስራዎችን ለሚሰሩ ሰራተኞች ቅድሚያ በመስጠት በቀጣይም በርካታ ማሻሻያዎች እንደሚደረጉ ዋና ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ቀዳማዊ መሰረታዊ የሰራተኛ ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ተካልኝ ተርፋሳ በበኩላቸው፣ እለቱ ሲከበር በአየር መንገዱ የሁሉም ሰራተኞች ሚና በጉልህ የሚታወስበት ነው ብለዋል።


 

በመሆኑም በሰራተኞችና በድርጅቱ አመራሮች መካከል ያለውን አዎንታዊ ግንኙነትን ለማስቀጠልና የሰራተኛውን መብት ለማስጠበቅ እየተወሰዱ ያሉት እርምጃዎች አበረታች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይህም የሰራተኛውን ምርታማነት ለማሳደግና ለማስቀጠል እንዲሁም የኢንዳስትሪውን ሰላም ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ17 ሺህ በላይ ሰራተኞች ያሉት ሲሆን 5 ትልልቅ የስራ ዘርፎች የሚመራበት ግዙፍ ተቋም ነው።

ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ቀን በኢትዮጵያ ለ49 ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ135 ጊዜ በመላው ዓለም እየተከበረ ይገኛል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም