ተቋማቱ የትንሳኤን በዓል ምክንያት በማድረግ ድጋፍ ለሚሹ 120 የማህበረሰብ ክፍሎች ማዕድ አጋሩ

ጂንካ፣ሚያዚያ 23/2016 (ኢዜአ)፡-የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሦስት ተቋማት መጪውን የትንሳኤ በዓል ምክንያት በማድረግ በጂንካ ከተማ ድጋፍ ለሚሹ 120 የማህበረሰብ ክፍሎች ማዕድ አጋሩ።

አቅም ለሌላቸው የህብረተስብ ክፍሎች ድጋፉን በቅንጅት ያደረጉት ተቋማት የክልሉ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ የሴቶችና ህፃናት ቢሮ እንዲሁም የአሪ ዞን ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ናቸው።

"በጎነት ለራስ ነው!" በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር ማዕድ ከማጋራት ባለፈ  የአልባሳት ድጋፍ ተደርጓል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዋኖ ዋኖሌ፤ ድጋፉ መጪውን የትንሳኤ በዓል በችግር ውስጥ ካሉ ወገኖች ጋር በአብሮነት ለማክበር ታስቦ የተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በዚህም በጂንካ ከተማ ለሚገኙ 120 አረጋዊያን፣ አቅመ ደካሞችና አካል ጉዳተኞች ለእያንዳንዳቸው 5 ኪሎ ዱቄት እና 5 ሊትር ዘይት እንዲሁም የአልባሳት ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

በዓላትን ነባሩን የመረዳዳት፣ የመተጋገዝና የመተሳሰብ ባህላችንን በሚያሳድግ መልኩ በጋራ ማክበር አብሮነታችንን ለማጠናከር ያግዛል ሲሉም ገልጸዋል።

በክልሉ ችግር ውስጥ ያሉ ወገኖችን ታሳቢ ያደረጉ ሰው ተኮር የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን የገለጹት ዶክተር ዋኖ፣ "ልማቶቹ ከግብ እንዲደርሱ ሁሉም የራሱን አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይገባል" ብለዋል።

የክልሉ ሴቶችና ህፃናት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ካሰች ኤሊያስ በበኩላቸው፣ "ዘመናትን የተሻገሩና የትስስራችን ምሶሶ የሆኑ የመረዳዳት፣  የመተሳሰብና የመተጋገዝ እሴቶች ጎልተው መውጣት አለባቸው" ብለዋል።

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ለሀገር በቀል ዕውቀቶች በተሰጠው ትኩረት በዓላትን በአብሮነት የማሳለፍ እንዲሁም አቅመ ደካሞችን የመጠየቅ ልምድና እሴቶች እየጎለበቱ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ችግረኞችን መርዳትና የሀገር ባለውለታ አረጋዊያንን መጠየቅ የሰውነት ባህሪና የኢትዮጵያዊነት መገለጫ እንደሆኑም ወይዘሮ ካሰች አስታውሰዋል።

በተለይ በችግር ምክንያት ወደጎዳና የሚወጡ ህፃናትን ከጎዳና ህይወት ለመታደግ ሁሉም የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ፤ ተቋማት በመቀናጀት አቅም ለሌላቸው ባደረጉት ድጋፍ መደሰታቸውን ገልጸው፣ ተሳተፎ ያደረጉ አካላትን አመስግነዋል።

በቀጣይም በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖችን ታሳቢ በማድረግ በዞኑ የሚሰሩ ሰው ተኮር የልማትና የበጎ አድራጎት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።

በማዕድ ማጋራቱ ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል ወይዘሮ አመለወርቅ ጽጌ "ችግራችን ታይቶ በዓሉን በደስታ እንድናሳልፍ ድጋፍ በመደረጉ ተደስቻለሁ" ብለዋል። 

በዓል በመጣ ቁጥር ከችግራቸው በመነሳት እንደሚጨነቁ ያስታወሱት ወይዘሮ አመለወርቅ፣ "ዛሬ የተደረገልኝ ድጋፍ ወገን አለኝ ብዬ እንድኮራ አድርጎኛል" ሲሉ ገልጸዋል።

በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ ድጋፍ ላደረጉላቸው አካላትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም