በአብይ ፆምና ሰሙነ ህማማት የተማርነውን ፍቅርና ይቅርታ በእለት ተእለት ህይወታችን በተግባር ልንገልጸው ይገባል 

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 24/2016(ኢዜአ)፡- በአብይ ፆምና ሰሙነ ህማማት የተማርነውን የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅርና ይቅርታ በእለት ተእለት ህይወታችን በተግባር ልንገልጸው ይገባል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ምዕመናን ገለጹ።

በአብይ ጾም ራስን ከምግብ በመቆጠብ ከሚደረግ ጾም በተጨማሪም ጠያቂ ለሌላቸው ደራሽ በመሆን፣ የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና ሌሎች ሰብዓዊ ድጋፎችን በማድረግ ማሳለፍ የተለመደ ነው።

ኢዜአ በአዲስ አበባ በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት በመዘዋወር ያነጋገራቸው ምዕመናን በአብይ ፆምና ሰሙነ ህማማት የተማርነውን የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅርና ይቅርታ በእለት ከእለት የኑሮ ሒደት ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

በተለይም በጾም ወቅት የሚደረግ መደጋገፍ፣ አብሮነትና ትህትና ሁል ጊዜ ተግባራዊ ሊደረግ የሚገባ ስለመሆኑም ገልጸዋል።

አቶ ዳዊት አሰፋ ይቅርታ ከራስ ሰላምም ከቤት የሚጀምር መሆኑን በመግለጽ ሰውን እንደራስ መውደድን የሁልጊዜ ተግባራችን ልናደርገው ይገባል ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ የይቅርታ ልብና ሁሉን በእኩልነት የሚመለከት ሰብእና ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ወይዘሮ ዝናሽ አሰፋ በበኩላቸው ሰው ሆነን በመፈጠራችን ብቻ ሁላችንም እኩል መሆናችንን በመረዳት መቀራረብና አንድነታችንን ማጠናከር ያስፈልገናል ብለዋል።


 

ከአብይ ፆምና ሰሙነ ህማማት ወቅቶች ባሻገር እርስ በእርስ መተጋገዝ፣ መተዛዘንና መተሳሰብ በተግባር የምንኖረው የህይወታችን አካል ልናደርገው ይገባዋል ያሉት ደግሞ ፍቃዱ መልኬ ናቸው።


 

ሰናይት ስሜና እታፈራሁ ደርበው የተባሉ አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጅን ለማዳን የከፈለው መስዋዕትነት ያለ ልዩነት መሆኑን በመገንዘብ ሰው በመሆናችን ሰውነትን ማስቀደም ይጠበቅብናል ነው ያሉት።


 

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ጌታነህ እሸቱ አብሮነትና መደጋገፍን የዕለት ተዕለት መገለጫ በማድረግ በብዙ ችግር ውስጥ የሚኖሩ ወገኖችን በዘላቂነት ማገዝ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።


 

መለያየት፣ መነቃቀፍና ጥላቻን ለማስወገድ የኢየሱስ ክርስቶስን ፍቅርና ይቅርታ በየእለት የህይወት ጉዟችን በተግባር ልንገልጸው ይገባል ሲሉ ምዕመናኑ አክለዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም