በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ ፤ ሚያዝያ 24/2016 (ኢዜአ)፦ በመዲናዋ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው  እንደሚቀጥሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

በአዲስ አበባ መጪውን የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ከ255 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ማዕድ የማጋራት መርሐ ግብረ ተካሂዷል።


 

ከንቲባ አዳነች በዚህ ወቅት የማዕድ ማጋራቱ እውን እንዲሆን ባለሀብቶች እና በጎ ፈቃደኞች ላደረጉት አስተዋፅኦ አመስግነዋል።

በቀጣይም በመዲናዋ የተቸገሩ ወገኖችን መደገፍና የአቅመ ደካሞችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።


 

የአዲስ አበባ ኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር አብርሃም ታደሰ በበኩላቸው በከተማዋ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።

የባለሀብቶች፣ የተቋማትና እና የበጎ ፈቃደኛ ግለሰቦች ተሳትፎም እየጎለበተ መሆኑን ጠቅሰው፥ በዛሬው ዕለትም በሁሉም ክፍለ ከተሞች እና ወረዳዎች ማዕድ ማጋራት እየተከናወነ ነው ብለዋል።

ድጋፍ የተደረገላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በበኩላቸው፥ ከተማ አስተዳደሩ፣ ባለሀብቶችና በጎ ፈቃደኛ ግለሰቦች ለበዓል መዋያ ላደረጉላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም