የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ለ1 ሺህ 455 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ

ሶዶ ፤ሚያዝያ 24/2016 (ኢዜአ)፡- የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት የትንሣኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለ1 ሺህ 455 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ ማድረጉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ አስታወቁ።

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ እንዳሉት፤ የፊታችን ዕሁድ የሚከበረውን የትንሣኤ በዓል ምክንያት በማድረግ የክልሉ መንግስት ለ1 ሺህ 455 የህግ ታራሚዎች ይቅርታ ተደርጓል።

የይቅርታው ተጠቃሚ የሆኑ ታራሚዎች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው መልካም ሥነ-ምግባር የነበራቸውና በሕግ የተደነገገው የይቅርታ መስፈርትን ያሟሉ መሆናቸው ጠቁመው፤ ይህም በክልሉ የይቅርታ ቦርድ ተጣርቶ የቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።

እንዲሁም ከተፈረደባቸው አንድ ሶስተኛ እና ከግማሽ በላይ የፍርድ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ መሆናቸውንም አስረድተዋል። 

እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ፤ ይቅርታው ከተደረገላቸው የህግ ታራሚዎች መካከል 1 ሺህ 435ቱ ከእስር የሚፈቱ ሲሆን፤ ሃያዎቹ ታራሚዎች ደግሞ የእስራት ጊዜያቸው የተቀነሰላቸው ናቸው።

የይቅርታ ተጠቃሚ ከሆኑት የህግ ታራሚዎች መካከል 95ቱ ሴቶች ሲሆኑ፤ 1 ሺህ 360ዎቹ ወንዶች መሆናቸውም ተገልጿል።

የይቅርታው ተጠቃሚ የሆኑ የህግ ታራሚዎች በቀጣይ ህይወታቸው የይቅርታን እሴት ተላብሰው ሰላምን በመስበክ፣ ለሕግ ተገዥ በመሆንና በልማት ስራዎች ጠንካራ ተሳትፎ በማድረግ ህዝብረተቡን ሊክሱ እንደሚገባ አቶ ጥላሁን አሳስበዋል ። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም