በክልሉ በትራንስፖርት ዘርፍ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሰራ ነው

አዳማ፤  ሚያዝያ 23/2016 (ኢዜአ):- በኦሮሚያ ክልል በትራንስፖርት ዘርፍ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ትራንስፖርት ኤጄንሲ ገለጸ።

ኤጄንሲው ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር ያሰለጠናቸውን 419 የትራፊክ ደህንነት ተቆጣጣሪዎችን አስመርቋል።

በዚሁ ጊዜ የኤጄንሲው ሃላፊ አቶ ዳንኤል ቸርነት እንደገለፁት በትራንስፖርት ዘርፍ የአቅርቦት ችግርን መነሻ ያደረጉ ብልሹ አሰራሮችና ሌብነት በስፋት ይስተዋላል።

በዘርፉ በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው ብለዋል።

ከዚህ ውስጥ የዘርፉ የአገልግሎት አሰጣጥን በቴክኖሎጂ አስደግፎ ለመምራት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ ወቅትም የስምሪትና የታሪፍ ክፍያ ዲጂታል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በእስከ አሁኑ ሂደት በርካታ መናኸሪያዎች የዲጂታል አገልግሎቱ ተግባራዊ ማድረጋቸውን አክለዋል።

የፍጥነት መቆጣጠሪያ ራዳርና የአልኮል መጠን መለኪያ መሳሪያዎችን ስራ ላይ በማዋልም የዘርፉን ችግሮች ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በምረቃው ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ የመንገድ ደህንነትና መድህን ፈንድ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አባሶ በበኩላቸው "ኢትዮጵያ ከሌሎች አገራት አንጻር በቁጥር ትንሽ ተሽካርካሪ ቢኖራትም በርካታ የትራፊክ አደጋ የምታስተናግድ አገር ናት" ብለዋል።

ከሚደርሰው የትራፊክ አደጋ ውስጥ ደግሞ አብዛኛው በአሽከርካሪዎች ስህተት እንዲሁም በተሽከርካሪ የቴክኒክ ችግር ምክንያት የሚከሰቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም መንጃ ፍቃድ አሰጣጥ ችግር እንዲሁም ፍጥነትና ቸልተኝነትም ለአደጋዎቹ መከሰት መንስኤ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ችግሩን ለመቀነስ በየአካባቢው ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የተቀናጀ ስራ የሚጠናከር መሆኑን አስገንዝበዋል።

የስነ-ምግባር ችግር፣ የብቃትና የትራፊክ ደህንነት ቁጥጥር መላላት የትራፊክ አደጋ እንዲባባስ መንስኤ መሆኑን የጠቀሱት ደግሞ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ የትምህርትና ስልጠና ዳይሬክተር ኮማንደር ዲሪባ ለታ ናቸው።

እየተበራከተ የመጣውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ኮሌጁ በአቅም ግንባታ ላይ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው የትራፊክ ደህንነት ተቆጣጣሪዎች ክህሎትና ስነ-ምግባር እንዲላበሱ ለማስቻል የበኩሉን እየተወጣ መሆኑንም ተናግረዋል።

ዛሬ 419 የትራፊክ ደህንነት ተቆጣጣሪዎችን በትራፊክ ደህንነት፣ ቁጥጥርና ህግ ማስከበር የሙያ ዘርፎች አስልጥኖ ማስመረቁን ጠቁመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም