ምዕመናን ከሰሙነ ህማማት ፍቅርን ፣ትህትናን ፣ እርስ በርስ መረዳዳትንና አንድነትን ሊማሩ ይገባል- የሃይማኖት አባቶች

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 23/2016(ኢዜአ)፡- ምዕመናን ከሰሙነ ህማማት ፍቅርን፣ አንድነትን ፣ትህትናን፣እርስ በርስ መረዳዳትን በመማር  ህይወትን በተግባር መኖር እንደሚገባቸው የሃይማኖት አባቶች ገለፁ ።

ሰሙነ ህማማት ከሆሳዕና እሁድ ሰርክ ጀምሮ እስከ ትንሳኤ ሌሊት ያሉት ቀናትን ያካተተ ሲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ለማዳን የተቀበለውን ፍዳ ፣መከራና ሞት የሚታሰብበት ሳምንት ነው።

የሳምንቱ ቀናት የራሳቸው የተለየ ስያሜ የተሰጣቸው ሲሆን በ "መርገመ በለስ" ተጀምሮ "ቅዳሜ ስዑር" በሚል ይጠናቀቃል፡፡ 

የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የነገረ-መለኮትና የስነ-ልቦና  መምህር አባ ጌድዮን ብርሃነ ለኢዜአ እንዳሉት ሰሙነ ህማማት ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ ሲል የከፈለው ዋጋና የመስቀል ጉዞ የሚታሰብበት ነው።   


 

ከብሉይ ኪዳን ወደ አዲስ ኪዳን እንዴት እንደተሸጋገርን በማሰብ የአዲስ ኪዳንን ከፍታና የክርስቶስን ውለታ የምናስብበት ሳምንት መሆኑን ገልፀዋል።

ሰሙነ ህማማት ምዕመናን ምን ያህል ዋጋ እንደተከፈለላቸው በማሰብ በዋጋቸው ፀንተው ለመገኘታቸው ራሳቸውን የሚመረምሩበት የመንፈሳዊ ህይወት መመልከቻ መንፈሳዊ መስታወት ነውም ብለዋል።

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሐዋሪያዊት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አባ ጴጥሮስ በርጋ በበኩላቸው ሰሙነ ህማማት ኢየሱስ ክርስቶስ አለምን ለማዳን በፍቅር ህይወቱን በመስቀል የሰጠበት እለት የሚታሰብበት ነው ብለዋል። 


 

በአብይ ፆም የኢየሱስ ክርስቶስ የሚታሰብ ሲሆን በሰሙነ ህማማት ደግሞ በልዩ ሁኔታ እግዚአብሄር ፍቅር ገዶት ለሰው ልጆች የከፈለው ውለታ የሚታሰብበት ወቅት መሆኑን አስረድተዋል።

ህማማት ኢየሱስ ክርስቶስ አለምን ለማዳን በፍቅር ህይወቱን በመስቀል አሳልፎ መስጠቱንና የመዳን ምንጭና መሰረት መሆኑ የሚታሰብበት መሆኑንም ተናግረዋል።


 

ምዕመናን ከሰሙነ ህማማት ፍቅርንና ትህትናን በመማር እርስ በርስ መረዳዳትና አንድነትን ገንዘብ ሊያደርጉ እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶቹ ጠይቀዋል።

ህማማት የችግር መፍቻና ራስን የመስጠት ምሳሌ የተማርንበት በመሆኑ  ምዕመናን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተማሩትን ፍቅር በተግባር በመኖር መግለፅ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

በሰሙነ ህማማት ጎልተው ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል ትህትና አንዱ መሆኑን በመግለጽ  የእኔ ብቻ ትክክል ነው ከሚል እሳቤ በመውጣትና በመደማመጥ ችግርን መፍታት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሰሙነ ህማማት የፈጣሪ ጥልቅ ፍቅር የሚታሰብበት በመሆኑ እርስ በርሳችንም በፍቅርና በመተሳሰብ መኖር ያስፈልገናል ብለዋል።

ከሰላም የሚበልጥ ነገር አለመኖሩን የገለጹት የሀይማኖት አባቶች ሰላምን ለማረጋገጥ ለዕርቅ፣ ለይቅርታ ለአብሮነት ራስን ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

 

  

 

   

        

 

 

  

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም