የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ከ350 ለሚበልጡ አቅመ ደካሞች እና አረጋዊያን ማዕድ አጋሩ

ሀዋሳ፤ ሚያዝያ 24/20216 (ኢዜአ)፦ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ከ350 ለሚበልጡ አቅመ ደካሞች እና አረጋዊያን ማዕድ አጋሩ።

በድጋፍ ርክክቡ ወቅት አቶ ደስታ እንደገለጹት በዓልን በመረዳዳትና በአብሮነት ማሳለፍ የነባር እሴት መሰረት በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።

ባለፋት አምስት ዓመታት የአቅመ ደካሞችን መኖሪያ ቤት ከማደስና በአዲስ መልክ ከመስራት ባለፈ ማዕድ በማጋራት ድጋፍ ሲደረግላቸው መቆየቱን አስታውሰዋል።

እርስ በርስ መረዳዳት በበዓል ወቅት ብቻ ሳይሆን በሌሎች ጊዜያትም መጠናከር እንዳለበት የገለጹት አቶ ደስታ፤ በበዓል ወቅት በተለይ አቅመ ደካሞችን መጠየቅና ያለን ማካፈል እንደሚገባ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ  ማህበራዊ ችግሮች ውስጥ የሚገኙትን በመተጋገዝና በመተባበር ማለፍ ተገቢ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳደሩ አስገንዝበዋል።


 

የሲዳማ ክልል ወጣቶችና ሕፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ እመቤት ኢሳያስ በበኩላቸው፤ በማዕድ ማጋራቱ ለአረጋውያን፣ ለአቅመ ደካሞች እና እገዛ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

ድጋፉ አቅመ ደካሞች በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ ታስቦ የተደረገ መሆኑን ያመለከቱት ወይዘሮ እመቤት፤ የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ በክልል ደረጃ ከ16 ሺህ 500 በላይ ለሆኑ ወገኖች ማዕድ የማጋራት ሥራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

"ቢሮው ከበዓል ውጪም የመደጋገፍና የመረዳዳት ዕሴቶች እንዲጠናከሩ እየሰራ ይገኛል" ያሉት ሃላፊዋ፣ በክልሉ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት በርካታ ሰዎችን ተጠቃሚ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በበዓል ወቅት አቅም የሌላቸውን ወገኖች ማሰብ ለአብሮነት መጠናከር ሚናው የጎላ በመሆኑ በተለያዩ አካላት እየተደረጉ ያሉ ድጋፎች ተጠናክረው መጠቀል እንዳለባቸው ተናግረዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም