በትንሳኤ በዓል ከ500 ሺህ በላይ አቅመ ደካሞችን ለመደገፍ እቅድ ተይዟል 

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 24/2016(ኢዜአ)፡- ለትንሳኤ በዓል በአዲስ አበባ የሚገኙና ድጋፍ የሚሹ ከ500 ሺህ በላይ አቅመ ደካሞችን በበጎ ፍቃድ ለማስፈሰክና ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት አስታወቀ ፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ተቀዳሚ ምክትል ሰብሳቢ ላይከሔራን መንክር ለኢዜአ እንደገለጹት በአዲስ አበባ 250 ሰንበት ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ።

ሰንበት ትምህርት ቤቶቹ ከአገልግሎት ተልዕኳቸው ባሻገር የቤተክርስቲያኗ አስተምህሮ ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ በሆነው በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ በስፋት ይሳተፋሉ።

የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶቹ በቋሚነትና በበዓላት ወቅት የሚደረጉ ሲሆን በዚህ ረገድ አቅመ ደካሞች በቋሚነት በገንዘብ ፣ በምግብ ፍጆታና በአልባሳት እንደሚደገፉ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ወጣቶችና ህጻናት መሰል ድጋፎች የሚደረግላቸው ሲሆን ትምህርት ማስተማርና የስራ እድሎችን ማመቻቸት ተጠቃሽ ናቸው።  

በዚህም በዘንድሮው የትንሳኤ በዓል ሰንበት ትምህርት ቤቶቹ እንደ ወትሯቸው ነዳያንን የማስፈሰክና ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን የመደገፍ በጎ ፍቃድ አገልግሎቶችን እንደሚያከናውኑ አስታውቀዋል።

ለዚህም እስካሁን የድጋፍ አይነቶችን በየዘርፉ የመለየትና መሰል የቅድመ ዝግጅት ምዕራፎች የተጠናቀቁ ሲሆን ለትንሳኤ በዓል ከ500 ሺህ በላይ የሚሆኑ ወገኖችን ለማስፈሰክና ድጋፍ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል ነው ያሉት።

ይህንን በተመለከተ ኢዜአ በደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን እና በማሕደረ ስብሃት ቅድስት ልደታ ማርያም ቤተክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶችን እንቅስቃሴ ጎብኝቷል።

በደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን የአንቀጸ ብጹአን ሰንበት ትምህርት ቤት ሰብሳቢ ጳውሎስ ደምሴ አንደገለጹት የዓቢይ ጾምና ሰሙነ ህማማት ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ ሲል የከፈለው ዋጋና የመስቀል ጉዞ የሚታሰብበት ነው።


 

በዚህ ረገድ ቤተ ክርስቲያን ተምሳሌት መሆኗን ጠቁመው በተለይም ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ጥንታዊትና ነባር መሆኗን ገልጸው ከ1981 ዓ.ም ጀምሮ ይሰጥ የነበረው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እየዳበረ መምጣቱን አብራርተዋል።

አሁንም የሰንበት ትምህርት ቤት አባላቱ የትንሳኤ በዓልን በተለያዩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ለማሳለፍ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ይህ የመደጋገፍና የመረዳዳት ልምድ በዓላትን ጠብቆ የሚከናወን አለመሆኑን ጠቁመው በተለይ በቋሚነት ለሚደገፉና ለሚታገዙ ወገኖች ሰብዓዊ ድጋፍ የሚደረግ መሆኑን አንስተዋል።

የማሕደረ ስብሃት ቅድስት ልደታ ማርያም ቤተክርስቲያን የተክለ ሳዊሮስ ሰንበት ትምህርት ቤት ምክትል ሊቀመንበር  ጎይቶም አለማየሁ በበኩላቸው የዓቢይ ጾም ከምግብ በመቆጠብ ከሚደረግ ጾም በተጨማሪም ልዩ ልዩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች የሚሰጡበት ነው።


 

በተለይም ጠያቂ ለሌላቸው ደራሽ በመሆን፣ የተቸገሩ ወገኖችን መርዳትና ሰብዓዊ ድጋፎችን ማድረግ እየሱስ ክርስቶስ ለፍቅር የከፈለውን ዋጋ በተግባር እንደማሳየት ይቆጠራል ነው ያሉት።

በዚህም ሰንበት ትምህርት ቤቱ የዘንድሮውን የትንሳኤ በዓል ጨምሮ በተለያዩ በዓላት የምገባና ሌሎች ሰብዓዊ ድጋፎችን በማድረግ አጋርነቱን በተግባር እያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።

በዓላትን ጠብቆ የሚደረግ ድጋፍ ዘላቂ መፍትሔ እንዳልሆነ በመጠቆም ከጊዜያዊ ድጋፉ ጎን ለጎን ቋሚ የድጋፍ መርኃ ግብሮችን በማዘጋጀት የተለያዩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶችን እንደሚሰጡ አስታውቀዋል።

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም