የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ለ926 ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ

ቦንጋ ፤ ሚያዝያ 23/2016(ኢዜአ)፡- የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት መጪውን የትንሳኤ በዓል ምክንያት በማድረግ ለ926 ታራሚዎች ይቅርታ ማድረጉን አስታወቀ።

የክልሉ ፍትህ ቢሮ ሀላፊ አቶ እሸቱ ጎዴቶ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፤ የክልሉ የይቅርታ ቦርድ በይቅርታ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ መሰረት መስፈርቱን የሚያሟሉ ታራሚዎችን ከመንግስት፣ ከህዝብና ከታራሚ ጥቅም አኳያ ሲመረምር ቆይቷል።  

በተደረገው ምርመራም በአጠቃላይ የይቅርታ ጥያቄ ካቀረቡ 978 ታራሚዎች መካከል መስፈርቱን ያሟሉ 926 ታራሚዎች ጥያቄያቸው ለክልሉ መንግስት ቀርቦ የይቅርታ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን ተናግረዋል።

እንደ አቶ እሸቱ ገለጻ፤ የይቅርታው ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል፤ 920 ታራሚዎች ከእስር የሚለቀቁ ሲሆን፤ ስድስቱ ደግሞ የእስራት ጊዜያቸው የተቀነሰላቸው ናቸው።

በከባድ ወንብድና፣ በግፍ ግድያ፣ በሙስና እንዲሁም በሴቶችና ህፃናት ላይ ወንጀል በመፈጸም የፍርድ ሂደት ላይ ያሉ ታራሚዎች የይቅርታው ተጠቃሚ አይደሉም።

ታራሚዎቹ በማረሚያ ቤት በነበራቸው ቆይታ በአግባቡ ስለመታረማቸው፣ ስለመታነጻቸውና ስለመልካም ባህሪያቸው ምስክርነት የተሰጠባቸው መሆኑንም አመልክተዋል።

ይቅርታ የተደረገላቸው ታራሚዎች ወደ ህብረተሰቡ ሲመለሱ ሰላምን ከመስበክ ባለፈ አምራችና ህግ አክባሪ ዜጋ ሆነው ህብረተሰቡን መካስ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዘበዋል።

ህብረተሰቡም ግለሰቦቹ በአግባቡ ታርመውና ታንጸው ከእስር መለቀቃቸውን በመረዳት በበጎ ህሊና ተቀብሎ ማስተናገድ እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም