የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ያስገነባቸውን 10 የአቅመ ደካማ ወገኖችን ቤቶች አስረከበ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 24/2016(ኢዜአ)፡- የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በሰበታ ሀዋስ ወረዳ ተፍኪ ከተማ ያስገነባቸውን 10 የአቅመ ደካማ ወገኖችን ቤቶች አስረክቧል።

የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ የቤቶችን ቁልፍ ለአቅመ ደካሞች አስረክበዋል።

ሚኒስትሩ እንዳሉት ባለሃብቶችን በማስተባበር ከዚህ በፊት ለኑሮ የማይመቹ የነበሩ ቤቶች ደረጃቸውን በጠበቀ ጥራት እንዲገነቡ ተደርጓል።

ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ የመደጋገፍና ችግሮችን በጋራ የማለፍ ባህልን ማጠናከር አለብን ብለዋል።

ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የምትመች ኢትዮጵያን በመገንባት ሂደት አቅመ ደካሞችንና ጧሪ የሌላቸው ወገኖችን ማገዝ እንደሚገባም ተናግረዋል።

ቤታቸውን የተረከቡ ወገኖች በበኩላቸው፥ ሚኒስቴሩ እና ባለሃብቶች ምቹ ቤት ገንብቶ ስላስረከባቸው አመስግነው፥ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ እርስ በርስ መደጋገፍ ነው ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም