በድሬዳዋ በበጋ ወራት የበጎ ፍቃድ ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የተገነቡ ቤቶች ለአቅመ ደካሞች ተላለፉ

ድሬዳዋ፤ሚያዝያ 24/2016   (ኢዜአ) ፦ በድሬዳዋ አስተዳደር በበጋ ወራት የበጎ ፍቃድ መርሃ ግብር ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የተገነቡ ቤቶች ለአቅመ ደካሞች ተላለፉ።

የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን በበኩሉ በአስተዳደሩ በበጋ የበጎ ፍቃድ የልማት ተግባራት ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የተለያዩ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን ተገልጿል።

አስተዳደሩ የተለያዩ ተቋማትን በማስተባበር ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ አራት ቤቶች ናቸው ለአቅመ ደካሞች ተላልፈው የተሰጡት።

ቤቶቹን ያስገነቡት ደግሞ የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ቅርንጫፍ፣ የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያና የቀበሌ መስተዳድሮች ናቸው።

በቤቶቹ ርክክብ ላይ የተሳተፉት የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ካሊድ መሐመድ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በዘንድሮ የበጋ ወራት ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱና የማህበራዊ አገልግሎት ችግሮችን ያቃለሉ የልማት ስራዎች ተሰርተዋል።

በበጋ ወራት በየደረጃው የሚገኙ ተቋማትንና በጎ ፍቃደኞችን በማስተባበር  በተፋሰስ ልማት፣ በትምህርት፣ በደም ልገሳ ፣ በማዕድ ማጋራት፣ በአካባቢ ልማትና ፅዳት፣ በስፖርት፣ የተቸገሩ  አረጋዊያን ቤቶች ግንባታና እድሳት  እንዲሁም የትራፊክ አደጋ በመከላከል የተሰሩት ልማቶች ተጠቃሽ ናቸውን ብለዋል።

ዛሬ በተቋማት የተቀናጀ ጥረት ተሰርተው የተላለፉት ቤቶችም የበጋ ወራት የበጎ ፍቃድ ልማቱ መሳያ መሆናቸውን በማከል።

የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህላችንን እያጎለበቱ የሚገኙትን የበጎ ፍቃድ ስራዎችን በመጪው ክረምት ይበልጥ ለማሳደግ ዝግጅት ተጠናቋል ብለዋል።

በበጋ የበጎ ፍቃድ ልማት ላይ በመሳተፍ ቤቶቹን ያስገነቡት የየተቋማቱ የአመራር አባላት በበኩላቸው ፤ የደሃውን ማህበረሰብ መሠረታዊ ችግሮች ለማቃለል እና የከተማውን ማህበራዊ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

በ04 ወረዳ  ገንደ ቆሬ በተባለው ቀበሌ ቤታቸው የተገነባላቸው ወይዘሮ  ወሰኔ  በጋሻው  በትንሳኤ ዋዜማ  ቤት ተገንብቶ በዓሉን በደስታ ለመቀበል በመታደሌ ታላቅ ደስታ ተሰምቶኛል ብለዋል።

በወደቀ ትንሽዬ ጎጆ  ከቤተሰቦቼ ጋር ለዓመታት በችግር ውስጥ አሳልፌያለሁ ያሉት ደግሞ በመልካ ጀብዱ ቀበሌ ቤት የተሰራላቸው አቶ ሰዒድ ሽኩር ናቸው።

መንግስትና በጎ ፍቃደኞች የደሃውን እንባ የሚያብስ ልማት እያከናወኑ በመሆናቸው የደሃውን ህብረተሰብ ተስፋ እያለመለመ ይገኛልም ብለዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም