ፖለቲካ
የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ሹመቶችን በማጽደቅ ተጠናቀቀ
Jul 26, 2024 250
ጅግጅጋ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦ የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ለሦስት ቀናት ያካሄደውን ሰባተኛ መደበኛ ጉባኤ ሹመቶችን በማጽደቅ አጠናቀቀ። ምክር ቤቱ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ የቀረቡለትን ሰባት የሥራ ኃላፊዎችን ሹመት አጽድቋል። በምክር ቤቱ ኃላፊዎች የተሾመላቸው ተቋማት የክልሉ ንግድና ትራንስፖርት፣ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ፣ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ፤ ማዕድን፣ ኢነርጂና ነዳጅ እንዲሁም የገቢዎች ቢሮዎች ሲሆኑ፤ በተጨማሪም ለክልሉ ገጠር መንገዶች ባለሥልጣን እና ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ የሥራ ኃላፊዎች ተሹመዋል።   ምክር ቤቱ የክልሉ መንግሥት የ2016 በጀት ዓመት የእቅድና ክንውን ሪፖርት በልማትና በመልካም አስተዳደር ሥራዎች የተሻለ አፈፃፀም የተመዘገበበት እንደነበር በመጥቀስ በሙሉ ድምፅ አጽድቆታል። እንዲሁም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የኦዲት መሥሪያ ቤቶችን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቶች በምክር ቤቱ ጸድቀዋል። ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው የክልሉ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ አብዱላሂ ሁሴን ያቀረቡትን ሪፖርትም አድምጧል።   ኤጀንሲው ባቋቋማቸው የኤፍ ኤም ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያ እንዲሁም በማህበራዊ ትስስር ገጾቹ ከወቅታዊ መረጃ ባለፈ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ፕሮግራሞች ማቅረቡን ገልጸዋል። ኤጃንሲው የተደራሽነት አቅሙን ለማስፋት በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ እና በድሬዳዋ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጣቢያዎችን መክፈቱንም ኃላፊው አመልክተዋል።    
የኮማንዶ እና አየር ወለድ ዕዝ በበጀት አመቱ የተሰጠውን ሀገራዊ ተልዕኮ በላቀ ብቃት ፈፅሟል- ጀነራል አበባው ታደሰ
Jul 26, 2024 177
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦ የኮማንዶ እና አየር ወለድ ዕዝ በበጀት አመቱ በተሰማራበት የግዳጅ ቀጣና የተሰጠውን ሀገራዊ ተልዕኮ በላቀ ብቃት መፈፀሙን የጦር ኃይሎች ምክትል ኤታማዦር ሹም ጀነራል አበባው ታደሰ አረጋገጡ። ጀነራል መኮንኑ ይህንን ያረጋገጡት ዕዙ ከክፍለ ጦር አመራሮች እና ከመምሪያ ኃላፊዎች ጋር ለሁለት ቀናት ባደረገው ዓመታዊ የስራ አፈፃፀም ውይይት ማጠቃለያ መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው ነዉ። ጀነራል አበባው ታደሰ አሁን ባለው እውነታ ፅንፈኛው ኃይል ተመቷል፤ የቀረውም ቢሆን በሰፈር እና በጎጥ ተከፋፍሎ በስልጣን ፍላጎትና በሰበሰበው ገንዘብ እየተጣላ እንዲሁም እርስ በርሱ እየተገዳደለ እና አንዱ በአንዱ ላይ እየዘመተ ተራ ሽፍታ ሆኗል ነው ያሉት። በውሸት ፕሮፓጋንዳ የአማራ ህዝብ ጥያቄ ከሌላኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ የተለየ አስመስሎ ሲሰብከው የነበረው ማህበረሰብም የፅንፈኛውን ሴራ አውቆበት ይህን ቡድን መደገፍም ሆነ መርዳት እንደማያስፈልግ መግባባት ላይ መድረሱን ተናግረዋል።   የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ከአሁን በፊት በነበሩት በርካታ ግዳጆችም ወደር የሌላቸው አኩሪ ገድሎችን የፈፀመ ጀግና ክፍል መሆኑን አስታውሰዋል። በአሁኑ ሰዓት አቅሙን አጎልብቶ በበቂ ደረጃ የተደራጀ በመሆኑ በቀጣይም ብዙ የሚጠበቅበት የማይበገር የህዝብና የሃገር ትልቅ አለኝታ ስለሆነ የቀጣይ ተልዕኮውንም በውጤት ይፈፅማል ብለዋል ጀነራል አበባው ታደሰ። የኮማንዶ እና አየር ወለድ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጀነራል ሹማ አብደታ በበኩላቸዉ የክፍሉ የሠራዊት አባላት ከላይ እስከታች እጅና ጓንት ሆነው ለሀገራቸው ሰላምና ደህንነት በጋራ በመሥራታቸው በአመቱ ክፍሉ የሚፈለገውን ድል ማስመዝገብ መቻሉን ገልፀዋል፡፡   ሃገሩን እና ህዝቡን እያሰበ የሚሰራ ሠራዊት እና ለሃገር እና ለህዝብ የቆመ ሃይል ሁሌም አሸናፊ ነው ብለዋል የእዙ አዛዥ። ከዚህ የተነሳም በሰንደቅ አላማዋ ስር በገባነው ቃል መሠረት ለህዝባችን ለሃገራችን በትጋት በፍፁም ጀግንነት በመስራት ሰላሙን በዘላቂነት በማረጋገጥ ሀገራዊ ልማትና የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታው ያለ እንቅፋት እንዲቀጥል ማድረግ ይጠበቅብናል ማለታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ትብብር የሰፈነበትን አዲስ የአለም አሰላለፍ ዕውን ለማድረግ የጋራ ድምጻችን ጉልህ ሚና ይጫወታል- የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ፉአድ ገና
Jul 26, 2024 137
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦ ትብብር የሰፈነበትን አዲስ የአለም አሰላለፍ ዕውን ለማድረግ የጋራ ድምጻችን ጉልህ ሚና ይጫወታል ሲሉ የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ፉአድ ገና ገለጹ። የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት በተሳተፉበት የብሪክስ የወጣት ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሆና በመቀላቀሏ ኩራት አንደሚሰማት ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ከሁሉም የብሪክስ አባል አገራት ጋር ያላት መልካም ግንኙነት ለአለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ያላትን ቁርጠኝነት በጉልህ ያንጸባርቃል ሲሉም ተናግረዋል። በአዲሱ የአለም አሰላለፍ ውስጥ ብሪክስ ፍትሀዊነትና አካታችነትን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት የኢትዮጵያ ጽኑ እምነት መሆኑንም አስረድተዋል።   ትብብር የሰፈነበትን አዲስ የአለም አሰላለፍ ዕውን ለማድረግ በተለያዩ የአለም መድረኮች የጋራ ድምጻችንን ማሰማት ይጠበቅብናል ሲሉም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል። በዚህ ሂደት ውስጥም የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ማረጋገጥ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት። በወጣቶች ዘርፍ ለሚኖረው የትብብር ማዕቀፍ ትምህርት፤ኢኖቬሽንና ስራ ፈጠራ እንዲሁም የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸው አመላክተዋል። ኢትዮጵያ ለብሪክስ መጠናከር አስፈላጊውን ትብብርና እገዛ እንደምታደርግ መግለጻቸውን ከኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።            
ጉባኤው ኢትዮጵያ ያለችበትን ተጨባጭ ሁኔታ ለዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ ማስገንዘብ  የቻለችበት ነው- አምባሳደር ሳሙኤል ኢሳ  
Jul 26, 2024 168
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦አራተኛው የፋይናንስ ለልማት ቅድመ ጉባኤ ኢትዮጵያ ያለችበትን ተጨባጭ ሁኔታ ለዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ በማስገንዘብ ገጽታዋን ይበልጥ የገነባችበት ነው ሲሉ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ሳሙኤል ኢሳ ተናገሩ። አራተኛው የፋይናንስ ለልማት ቅድመ ጉባኤ በአዲስ አበባ የተካሄደ ሲሆን ከ193 አገራት የተወጣጡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገራት ተሳትፈውበታል። በጉባኤው መክፈቻ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ፣ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሀመድን ጨምሮ በርካታ ተሳታፊዎች ታድመዋል።   ጉባኤው እ.አ.አ ከሰኔ 30 እስከ ሐምሌ 3 ቀን 2025 በስፔን ለሚካሄደው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ጉባኤ የተዘጋጀ የቅድመ ጉባኤ መድረክ ሲሆን ልማትን ለማሳለጥ አካታች የፋይናንስ ሥርዓት መዘረጋትን ዓላማ ያደረገ ነው። የታክስ አሰባሰብ ስርአትን በማጎልበት ሀብት አሰባሰብን ማጠናከር ሌላው ዓላማ ሲሆን አገራት ሀብት አሰባሰብ ላይ የልምድ ልውውጥ አድርገዋል። ኢትዮጵያም በመድረኩ በማደግ ላይ ያሉ አገራትን ታሳቢ ያደረጉ የፋይናንስ ስርዓቶች ሊዘረጉ እንደሚገባ አቋሟን አንጸባርቃለች። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ሳሙኤል ኢሳ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ጉባኤው በኢትዮጵያ መካሄዱ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች አሉት ብለዋል።   የዜጎችን ህይወት ለማሻሻል በሚደረጉ ዓለም አቀፍ ጥረቶች ኢትዮጵያ ሁሌም ተሳታፊ ናት ያሉት አምባሳደሩ ጉባኤው ኢትዮጵያ ያላትን ቁርጠኝነት በድጋሚ ያረጋገጠችበት መሆኑን አብራርተዋል። በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የለውጥ ሥራዎች ፣የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብርን ጨምሮ የልማት እንቅስቃሴዎቿን ለዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ በሰፊው ማስገንዘብ የተቻለበት መሆኑን አስረድተዋል። እንደ አምባሳደር ሳሙኤል ገለጻ በጉባኤው በተካሄዱ የባለሙያዎች ውይይቶች ላይ ኢትዮጵያ በየዘርፉ ያስመዘገበቻቸውን ተጨባጭ ሁኔታዎች ማስረዳት ተችሏል። ጉባኤው ስኬታማና ግቡን ያሳካ መሆኑን ጠቁመው የኢትዮጵያን ገጽታ ይበልጥ ማስተዋወቅ የተቻለበት ነው ሲሉም ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ያለው ሠላምና መረጋጋት ትልልቅ ጉባኤዎችን እየሳበ መሆኑን ጠቅሰው አራተኛው የፋይናንስ ለልማት ቅድመ ጉባኤ የዚሁ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል። ከዚህ አኳያ ጉባኤው ኢትዮጵያ የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከልነቷን ያረጋገጠ ከመሆኑ በላይ የአገልግሎት ዘርፉን የማነቃቃት ፋይዳው ከፍ ያለ መሆኑን አብራርተዋል።                    
ምክር ቤቱ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለሀገሪቱ የምጣኔ ሃብት ዕድገት አቅም የሚሆኑ አዋጆችን አጽድቋል - የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች
Jul 26, 2024 142
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለአገሪቱ የምጣኔ ሃብት ዕድገት አቅም የሚሆኑ አዋጆች መጽደቃቸውንና ወደ ትግበራ መግባታቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች ገለጹ፡፡ የፕላን፣ የበጀትና የፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የምክር ቤት አባላት የህዝብን ጥቅምና የሀገርን ዕድገት የሚያረጋግጡ አዋጆችን የማፅደቅ ስራ እንዳከናወኑ ተናግረዋል። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የአስፈፃሚ አካላትን የመከታተልና የመቆጣጠር እንዲሁም ለአገሪቱ የምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት አቅም የሚሆኑ አዋጆች መጽደቃቸውን ጠቁመዋል፡፡ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያን፤ ተቋማት ከተልዕኮቻቸው፣ ከተግባራቸውና ከስልጣናቸው አንጻር አቅደው እንዲተገበሩት ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን አንስተዋል። ለፕላን ሚኒስቴር፣ ለገንዘብ ሚኒስቴር፣ ለገቢዎች ሚኒስቴርና ለብሔራዊ ባንክ በተለየ ሁኔታ ድጋፍ እንዳደረጉ ገልፀው ፤ አፈፃፀማቸውም ውጤታማ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተጨማሪ እሴት ታክስ፣ የኤክሳይዝ ታክስ ማሻሻያ፣ የግዥና የንብረት አስተዳደር አዋጆች መጽደቃቸውን ገልጸው፤ አዋጆቹም የሀገሪቱንና ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን ታሳቢ በማድረግ የወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ አዋጆቹ የምክር ቤት አባላት የሚያፀድቁትን በጀት ለሚፈለገው አላማና ጥቅም እንዲውል የሚያግዝ ከመሆኑም ባሻገር ሀገራዊ ልማትን ለማሳለጥ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የወጡ አዋጆች አድሎ፣ ብክነት፣ የተንዛዛ አሠራርን በማስቀረትና በመከላከል ጊዜና ጉልበትን ለመቆጠብ የሚያስችሉ መሆናቸውንም ነው ያብራሩት፡፡ እንደዚሁም ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ መሰረት በማድረግ ተገቢውን ግብር ለመሰብሰብ የሚያስችሉ አዋጆች ናቸውም ሲሉም አክለዋል። ይህንንም ምክንያት በማድረግ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተገኘውን ከ529 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ወደ 612 ቢሊየን ከፍ ለማድረግ መታቀዱን አስታውሰዋል፡፡ የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢና የቡድኑ አስተባባሪ ወይዘሮ ለጢፋ አባተማም በበኩላቸው በግብርናው ዘርፍ የአምራች አስመራች፤ የዘርና የገጠር መሬት አጠቃቀም አዋጅ መውጣቱን አስታውሰዋል፡፡ አዋጆቹ ጥራቱ የተጠበቀ ምርጥ ዘር በአግባቡ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ነው፡፡ በተመሳሳይም የአምራች አስመራች አዋጅ አርሶ አደሩና ባለሃብቱ በጋራ ሰርተው ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በምክር ቤቱ እየፀደቁ የሚገኙት አዋጆች በሁሉም ዘርፍ የሀገር ሃብት በአግባቡ በመጠቀም የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያግዙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በአዲሱ በበጀት ዓመትም የወጡ አዋጆች ተቋማት የተሰጣቸውን ተልዕኮ በአግባቡ እንዲያሳኩ እንደሚያግዛቸው ገልጸዋል፡፡        
በጋምቤላ ክልል ያለውን ሰላም በማጽናት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጠንክረን ልንሰራ ይገባል - አፈ- ጉባኤ ባንቻየሁ ድንገታ
Jul 26, 2024 130
ጋምቤላ ፤ ሀምሌ 19/2016 (ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል ያለውን ሰላም በማጽናት የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅዶችን እውን በማድረግ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጠንክረን ልንሰራ ይገባል ሲሉ የክልሉ ምክር ቤት አፈ- ጉባኤ ባንቻየሁ ድንገታ ገለጹ። የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ ምርጫ ጊዜ 3ኛ የስራ ዘመን 6ኛ መደበኛ ጉባኤ የተለያዩ ሹመቶችና ሌሎች ውሳኔዎችን በማሳለፍ ዛሬ ከሰዓት በኋላ ተጠናቋል። አፈ- ጉበኤዋ በጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ እንዳሉት የክልሉን ሰላም በማጽናት በህዝቡ ለሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተግቶ ሊሰራ ይገባል ብለዋል። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የነበሩትን የጸጥታ ፈተናዎች በመቋቋም በሁሉም የልማት ዘርፎች የተከናወኑት ስራዎች አበረታች እንደነበሩ የቀረበው ሪፖርት ማመላከቱን ተናግረዋል።   በመሆኑም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የታዩትን ውስንነቶች በማረምና ጥንካሬዎችን በማስፋት በተያዘው በጀት ዓመት የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በአንድነት ሊረባረብ እንደሚገባ አሳስበዋል። በተለይም በክረምቱ ወራት የግብርና፣ የአረንጓዴ አሻራና ሌሎች ልማት ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ህዝቡን በማስተባበር ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል። ምክር ቤቱ በክልሉ የታለሙት የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅዶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንዲተገበሩ የተለመደውን የክትትልና ቁጥጥር ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አፈ-ጉባኤዋ ገልጸዋል።   ጉባኤው በሁለት ቀናት ቆይታው በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም፣ በ2017 በጀት ዓመት እቅድና የማስፈፀሚያ በጀት ዙሪያ ተወያይቶ በማጽደቅ ነው የተጠናቀቀው። ጉባኤው የአምስት የምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎችና የሶስት ካቢኔ አባላትን፣ የዘጠኝ የጠቅላይ፣ የከፍተኛና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኞች ሹመት መርምሮ ያጸደቀ ሲሆን ሁለት ምክር ቤት አባላትን ከምክር ቤት አባልነት አንስቷል። በዚሁ መሰረት አቶ ቻም ኡበንግ የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ ባጓል ጆክ የክልሉ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ እንዲሁም አቶ ቱት ጆክ የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ሹመት ጸድቋል።
ኢትዮጵያ ለሶማሊያ መንግሥት መሰረተ ቢስ ውንጀላ ቦታ አትሰጥም - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
Jul 26, 2024 176
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለሶማሊያ መንግሥት መሰረተ ቢስ ውንጀላ ቦታ እንደማትሰጥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ። የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ፥ የሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ መንግሥት ባለሥልጣናት በኢትዮጵያ ላይ እየሰነዘሩት ያለውን መሰረተ ቢስ ውንጀላ እየተከታተለ መሆኑን አመልክቷል። ከሶማሊያ መንግሥት መሰረተ ቢስ ውንጀላ በተቃራኒ ኢትዮጵያ ለሁለቱ ሀገራት ወንድማማች ህዝቦች ሰላምና መረጋጋት ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ ዋጋ እየከፈለች መቆየቷን ሚኒስቴሩ አስታውሷል። የሶማሊያ ፌደራላዊ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ግን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ኃላፊነት የጎደላቸው መግለጫዎችን ኢትዮጵያ ላይ ማውጣታቸው ተቀባይነት የሌለው መሆኑን መግለጫው ጠቅሷል። የሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች ያላቸውን የደም እና የባህል ትስስር የምታስቀድመው ኢትዮጵያ ለሶማሊያ መንግሥት መሰረተ ቢስ ክስ ቦታ የማትሰጥ መሆኑን እና ጉዳዩን በትዕግሥት መያዟም ተገልጿል። ኢትዮጵያ የስጋት ቀጣና በሆነው የአፍሪካ ቀንድ ያለው ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ እና የታጣቂዎች እንቅስቃሴ በአካባቢው ሰላም ላይ ያለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ስለምትረዳ በትኩረት እየተከታተለችው መሆኑንም ሚኒስቴሩ ገልጿል። ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ባላት ፅኑ አቋም በቀጣናው ግጭት የሚፈጥሩ ጉዳዮችን መከላከሏን እንደምትቀጥል በመግለጫው ተብራርቷል። ኢትዮጵያ ወደፊትም ከሶማሊያ ወንድም ሕዝብ ጎን መሆኗን እንምትቀጥል በመግለጫው ተጠቅሷል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት 8ኛ መደበኛ ጉባዔ በመጪው ሰኞ ይጀመራል
Jul 26, 2024 131
ባህር ዳር፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦ የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን፣ 8ኛ መደበኛ ጉባዔ በመጪው ሰኞ መካሄድ እንደሚጀምር የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ አስታወቁ። አፈ ጉባዔዋ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ ለአራት ቀናት እንደሚቆይ የሚጠበቀው የምክር ቤቱ ጉባዔ የክልሉን የአስፈፃሚ አካላት የ2016 በጀት ዓመት የልማትና መልካም አስተዳደር ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ይገመገማል። በሚቀርበው ሪፖርት ላይ የምክር ቤት አባላት በስፋት ከመከሩ በኋላ ይፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል። በተጨማሪም የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት፣ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የክልሉን ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ሪፖርቶችን እንደሚያዳምጥ ተናግረዋል። እንዲሁም ምክር ቤቱ በሚቀርቡ ልዩ ልዩ አዋጆችና ደንቦች ላይ በመወያየት ያጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም አፈ ጉባዔዋ አስረድተዋል። ከዚህም ሌላ የ2017 በጀት ዓመት የልማት ዕቅዶች ማስፈፀሚያ በጀት ቀርቦ እንደሚፀድቅም አስታውቀዋል። በመጨረሻም ልዩ ልዩ ሹመቶችን በመስጠት የምክር ቤቱ ጉባዔ መርሃ ግብሩን እንደሚያጠናቀቅ የሚጠበቅ መሆኑን ገልጸዋል።    
የአጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት ችግሮቻችንን በውይይት መፍታት እንደምንችል ያመላከተ ነው---የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተሳታፊዎች
Jul 26, 2024 82
አሶሳ ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለአገራዊ ምክክር የተካሄደው አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት በውይይት ችግሮቻችንን መፍታት እንደምንችል ያመላከተ ነው ሲሉ ተሳታፊዎች ተናገሩ። በክልሉ ለአገራዊ ምክክር አጀንዳ ለመለየት በ10 ቡድኖች ሲካሄድ የነበረው ውይይት ተጠናቋል። በአጀንዳ ልየታና ምክክር ከተሳተፉ የክልሉ ማህበረሰብ ክፍሎች መካከል ወይዘሮ ፋጡማ አህመድ ለኢዜአ እንደገለፁት ላለፉት ቀናት የተካሄደው አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት ነጻ እና ገለልተኛ ነው። የክልሉን ብሎም የአገሪቱን ሠላምና ልማት የሚያስቀጥሉ ሃሳቦችን እና ጉዳዮችን ያለ ማንም ተጽዕኖ እንዳቀረቡበት በማመላከት። ''ይህም በአገሪቱ በሀሳብ ልዩነት የተፈጠሩ ችግሮች በመነጋገር መፍታት እንደምንችል ያሳየ እና ተስፋ የሰጠ ነው'' ብለዋል።   ሌላዋ ተሰታፊ ወይዘሮ እጸገነት ተስፋዬ፣ ''መነጋገር ችግሮችን ወደ ሠላም መመለስ ያስችላል'' ሲሉ ገልጸዋል። ''ውይይቱ አብሮነትን በማጠናከር የሃሳብ ልዩነቶቻችንን መፍታት እንደሚቻል አሳይቶናል'' ያሉት ወይዘሮ እፀገነት፣ ''አገራዊ ምክክሩ ግጭት የሌለባት አገር ለልጆቻችን ለማስረከብ ይረዳናል'' ብለዋል።   አቶ ታደሰ ደሬሳ በበኩላቸው በአገራዊ ምክክሩ አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት በነጻነት መወያየታቸውን ተናግረዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው ምክክር ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን የሚወክሉ 60 ተሳታፊዎችን መምረጣቸውን በኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች እና ዳያስፖራዎች አስተባባሪ አቶ ረታ ጌራ አስታውቀዋል።  
አገራዊ ምክክሩ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል እኩል አካታችና አሳታፊ ባደረገ መልኩ እንዲከናወን እየተሰራ ነው - ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ
Jul 26, 2024 97
አዳማ ፤ ሀምሌ 19/2016(ኢዜአ)፡- አገራዊ ምክክሩ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል እኩል አካታችና አሳታፊ ባደረገ መልኩ እንዲከናወን እየተሰራ መሆኑን የምክክር ኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ተናገሩ። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ጋር አካል ጉዳተኞች በአገራዊ ምክክሩ ያላቸውን ተሳትፎና ሚና ለማጠናከር ያለመ ውይይት ዛሬ በአዳማ ከተማ እያካሄደ ነው። በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፤ አገራዊ ምክክሩን ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል እኩል ባካተተ መልኩ ለማካሄድ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።   ለዚሁ ሲባል ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ጋር መድረኩን ማዘጋጀቱን አንስተዋል። ፌዴሬሽኑም አካል ጉዳተኞችን የተመለከቱ አጀንዳዎችን ቀድሞ ለምክክር ኮሚሽኑ ማቅረቡ የሚበረታታ መሆኑንም አንስተዋል። በቀጣይም ፌዴሬሽኑ አካል ጉዳተኞችን በማሳተፍ በምክክር ሂደቱ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል። የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ በበኩላቸው፤ አካል ጉዳተኞች በአገራዊ ምክክሩ እንዲሳተፉ የማንቃት ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።   አገራዊ ምክክር በሚያመጣው ዘላቂ መፍትሔ ውስጥ አካል ጉዳተኞች የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ነው የተናገሩት። አካል ጉዳተኞች በምክክሩ ንቁ ተሳታፊ በመሆን የለውጥ ሀሳብ በማምጣት ረገድ የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን አመራሮች እና ባለሙያዎች ስልጠና እየተካሄደ ነው
Jul 26, 2024 82
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦ 4ኛው ዙር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን አመራሮች እና ባለሙያዎች ስልጠና መድረክ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል። ስልጠናው የብልፅግና ፓርቲ ህዝብ እና አለምአቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ከአዲስ አበባ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር መዘጋጀቱ ተመላክቷል። በመርሀ ግብሩ ላይ የብልፅግና ፓርቲ ህዝብ እና አለምአቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሀላፊ አቶ አዲሱ አረጋን ጨምሮ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል። የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በመክፈቻ ንግግራቸው ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የፓለቲካ ባህላችንን ለመቀየር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል። የለውጡን ምንነትና አስፈላጊነት በአግባቡ ለማስረዳትና ለማስረጽ እንዲሁም የዴሞክራሲ ስርዓት በጽኑ መሠረት ላይ እንዲገነባ ለማድረግ የበኩር ትርክትን ማጎልበት አስፈላጊ መሆኑንና ለሂደቱም ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት አንስተዋል፡፡   በኢትዮጵያ የሚታዩ የበኩር ትርክትና የአጻፋ ትርክቶችን ለማስታረቅ ብልፅግና ፓርቲ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡ የፓርቲውን እሳቤዎችና አቋሞች በአግባቡ ለማስረጽ ብሎም ሁለንተናዊ ብልጽግና በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ የሚዲያ ባለሙያዎች የማህበራዊ ስልተ ቀመር ስልትን ባገናዘበ መልኩ በመስራት ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል። በድህረ እውነት ዘመን የሚፈጠሩ የውሽትና የፈጠራ መረጃዎችን በመከላከል የአባልና አመራሩን አቅም አሟጦ መጠቀም ይገባል ብለዋል፡፡ ቅቡልነት ያለው የአገረ መንግስት ግንባታን ለማረጋገጥ በጋራ እሴቶችና ማንነቶች ላይ በማተኮርና በሕዝብ ዘንድ በማስረጽ የሚዲያ ባለሙያዎች አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑ በመረዳት በትኩረት መሰራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡ ለተከታታይ 5 ቀናት "የብሔራዊነት ትርክት ለኢትዮጵያ ልዕልና!!" በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው የስልጠና መድረክ ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የኦሮምያ፣ የአማራ፣ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኮሙኒኬሽን እና የሚድያ አመራሮች እና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛል። መድረኩ ለ3 ተከታታይ ዙሮች በድሬዳዋ፣በሀዋሳ ፣እንዲሁም በጅማ ከተሞች መሰጠቱን ከብልፅግና ፓርቲ በማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የመከላከያ ሠራዊት በጠለምት ወረዳዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን በመመለስ የአካባቢውን ሰላም የማረጋገጥ ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ ይገኛል- ኮሎኔል ደረጀ ኩምሳ
Jul 26, 2024 86
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016 (ኢዜአ)፦ የመከላከያ ሠራዊት በጠለምት ወረዳዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን በመመለስ የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት የማረጋገጥ ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ እንደሚገኝ በሰሜን ምዕራብ እዝ የ501ኛ ኮር ምክትል አዛዥ ኮሎኔል ደረጀ ኩምሳ ገለጹ። ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለሱ ሂደት ሰላማዊና ስኬታማ እንዲሆን የአካባቢው ማህበረሰብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡ በሰሜን ምዕራብ እዝ የ501ኛ ኮር ምክትል አዛዥ ኮሎኔል ደረጀ ኩምሳ፤ በፕሪቶሪያው ስምምነት ማዕቀፍ ስር የአማራና ትግራይ ክልሎች በደረሱት ስምምነት መሰረት ከጠለምት ወረዳዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደቀያቸው የመመለስ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡ ሂደቱም የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል መሠለ በለጠ፣ የሁለቱ ክልሎች ምክትል ርዕሳነ መስተዳድሮች በተገኙበት የማስፈጸሚያ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል። የመከላከያ ሠራዊትም የሀገር ሽማግሌዎችን በማዋቀር በሶስቱ የጠለምት ወረዳ ማዕከላትና በእናዳባጉና ምክክር በማድረግ የተፈናቃዮችን ትክክለኛነት በማረጋገጥ የቅድመ ዝግጅት ስራ መስራቱን ገልጸዋል። የትግራይ ክልል ተሽከርካሪ አዘጋጅቶ ተፈናቃዮች ደህንነታቸው ተጠብቆ ወደመኖሪያ ቀያቸው እንዲመለሱ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡ በዚህም መከላከያ ሠራዊት ስድስት፣ ከአማራና ትግራይ ክልሎች ከእያንዳንዱ ሶስት በድምሩ 12 ታዛቢዎችን በማደራጀት በሶስት ጣቢያዎች ተፈናቃዮችን የመመለስ ስራ መጀመሩን ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅትም የመከላከያ ሠራዊት በጠለምት ወረዳዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን በመመለስ ዘላቂ ሰላም የማረጋገጥ ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡ በሂደቱ አዋኪ የሰላምና ጸጥታ ስጋት እንዳላጋጠመ ጠቁመው፤ ሂደቱ ስላማዊና ስኬታማ እንዲሆን የአካባቢው ማህበረሰብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡ ከሁለቱም ክልሎች ጋር በመነጋገር ለአርሶ አደሩ የአፈር ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር ተደራሽ በማድረግ ወደ እርሻ ስራ እንዲገባ መደረጉንም ገልጸዋል። ከኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽንና አጋር ደርጅቶች ጋር በመሆን ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች አስቸኳይ እርዳታ ተደራሽ ለማድርግ እየተሰራ መሆኑንም አውስተዋል፡፡ በቀጣይም የመከላከያ ሠራዊት የአከባቢውን ዘላቂ የሰላምና ደህንት የማስጠበቅ ተልዕኮውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡
በተለያዩ የትብብር መስኮች ላይ የተመሰረተው የኢትዮጵያና የአልጄሪያ ግንኙነት ተጠናክሮ ቀጥሏል   
Jul 26, 2024 104
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦ በተለያዩ የትብብር መስኮች ላይ የተመሰረተው የኢትዮጵያና የአልጄሪያ የሁለትዮሽ ግንኙነት ተጠናክሮ መቀጠሉን በኢትዮጵያ የአገሪቱ አምባሳደር ሞሃመድ ላሚን ላባስ ገለጹ። አምባሳደር ሞሃመድ ላሚን ላባስ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያና አልጄሪያ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀና በተለያዩ የትብብር መስኮች ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ወዳጅነት አላቸው። የሁለቱ አገራት ግንኙነት የተጀመረው፤ አልጄሪያ ከቅኝ ግዛት ለመላቀቅ በምታደርገው የነጻነት ትግል ኢትዮጵያ ከጎኗ መቆሟን ተከትሎ መሆኑን አንስተው ይህም ግንኘነቱን ታሪካዊ ያደርገዋል ነው ያሉት። ከዚህም በኋላ ሁለቱ አገራት በተለያዩ ጊዜያት በሚገጥማቸው ፖለቲካዊ ችግሮች እርስ በእርስ በመደጋገፍና መፍትሄ በማፈላለግ ያላቸውን ታሪካዊ አጋርነት ይበልጥ እየተጠናከረ መምጣቱንም አብራርተዋል። በባህል እንዲሁም በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት መስክም አጋርነቱ እየተጠናከረ መምጣቱን አንስተው ፤ለዚህም በርካታ የኢትዮጵያ ተማሪዎች በአልጄሪያ ትምህርታቸውን መከታተል መቻላቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል። በምጣኔ ኃብት ዘርፍ በተለይም በንግድና ኢንቨስትመንት የሁለቱ አገራት ግንኙነትን ለማጠናከር የሚያስችል የጋራ ሥልት ተቀይሶ ወደ ሥራ መግባቱን ጠቁመው፤ በዚህም የአገራቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የጉብኝት ልውውጥ ማድረጋቸውን ተናግረዋል። በቅርቡም በፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ላይ የተሰማሩ ልዑካን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የኢንቨስትመንት አማራጮችን መመልከት መቻላቸውንና መሰል እንቅስቃሴዎች በቀጣይ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል። በተለይም በግብርና ዘርፍ የሁለቱን አገራት የኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል። በንግዱ ዘርፍ፤ አልጄሪያ ከፍተኛ የቡና ተጠቃሚ አገር መሆኗን ጠቅሰው፤ ከኢትዮጵያ ቡናን በስፋት ወደ አልጄሪያ ለማስገባት እንዲሁም አልጄሪያን የኢትዮጵያን የአበባ ምርት ተጠቃሚ ለማድረግ የአየር ትራንስፖርቱን በማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የአየር ትራንስፖርት ሲጠናከር የአልጄሪያ ምርቶች በኢትዮጵያ፤ በአንጻሩ የኢትዮጵያ ምርቶች በአልጄሪያ እናያለን ብለን ተስፋ እንደርጋለን ብለዋል። ኢትዮጵያና አልጄሪያ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ ተደራራቢ ታክስን በማስቀረትና በሌሎች የትብብር መስኮች ከ20 በላይ ሥምምነት ከዚህ ቀደም አድርገዋል። የእነዚህን ሥምምነቶች ትግበራ ለማቀላጠፍ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል ያሉት አምባሳደሩ፤ በሁለቱ አገራት ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ደረጃ የፖለቲካ ምክክሮችና ውይይቶች ተጠናክረው መቀጠላቸውን አንስተዋል። በዚህ ረገድ የሁለቱ አገራት የጋራ ኮሚሽን የተሰሩ ሥራዎችን በመገምገምና ቀጣይ አቅጣጫ በማስቀመጥ ረገድ ትልቅ ሚና እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል። በሌላ በኩል ኢትዮጵያና አልጄሪያ የጋራ በሆኑ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ለአብነትም በሰላምና ደኅንነት በተለይም ሽብርተኝነትን በመወጋትና እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል የጋራ አቋም እንዳላቸው ጠቅሰው፤ ለዚህም በጋራ እየተሰራ ነው ብለዋል። በተለይም የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ረገድ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ችግኞችን በመትከል እየሰራች ያለው ሥራ የሚበረታታና ይህም ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች አገራትም ጭምር ምሳሌ የሚሆን ነው ሲሉ ተናግረዋል። ከዚህ አንጻር፤ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ታች ወርደው ችግኝ በመትከል የሚያሳዩት አርአያነት ያለው ተግባር የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል። አምባሳደር ሞሃመድ ላሚን ላባስ ከ40 ዓመታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንደነበር ጠቅሰው ኢትዮጵያ አሁን ላይ ያለችበት የእድገት ደረጃ የሚደነቅ መሆኑንም አንስተዋል። የአልጄሪያና የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጠጣር በ1960ዎቹ መጨረሻ ላይ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።    
የሀረሪ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ከነገ ጀምሮ ይካሄዳል 
Jul 26, 2024 79
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦ የሀረሪ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 3ኛ ዓመት 6ኛ መደበኛ ጉባዔውን ከነገ ጀምሮ ማካሄድ እንደሚጀምር የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አስታወቁ። የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ሱልጣን አብዱሰላም በሰጡት መግለጫ ምክር ቤቱ ከነገ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በሚያካሄደው ጉባኤ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ይመክራል ብለዋል። በዚህም የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት የ2016 ዓ.ም አፈጻጸም ሪፖርት እና 2017 እቅድ ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበት ተናግረዋል። እንዲሁም የጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የ2016 የበጀት ዓመት ሪፖርት እና የ2017 እቅድ ቀርቦም ውይይት ይደረግበታል ብለዋል። በጉባኤው የክልሉ መስተዳድር የ2017 ዓ.ም የሥራ ዘመን ማስፈጸሚያ በጀት ላይ በመምከርም ያፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል። ምክር ቤቱ በሚያካሂደው ጉባኤ የተለያዩ ሹመቶችንም ያፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ መግለጻቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ ለህዝብ የሚበጁ  አጀንዳዎች ላይ በመምከር ጠቃሚ ውሳኔዎችን  አሳለፈ
Jul 25, 2024 117
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 18/2016(ኢዜአ)፦ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ጉባኤ ለህዝብ የሚበጁ ወሳኝ አጀንዳዎች ላይ መክሮ ጠቃሚ ውሳኔዎችን ማሳለፉን የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ፋጤ ስርሞሎ ገለጹ። ለሁለት ቀናት የተካሄደው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ የተለያዩ አዋጆችና ሹመቶችን በማፅደቅ ተጠናቋል። የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ፋጤ ስርሞሎ፤ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ጉባኤው በርካታ ለህዝብ የሚጠቅሙ አዋጆችና ሹመቶች የጸደቁበት ስኬታማ ጉባኤ መሆኑን ገልጸዋል። በጉባኤው የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም እና የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ፣ የበጀት አመቱን ረቂቅ በጀት ማፅደቅ ላይ በጥልቀት መምከሩን አንስተዋል። ​   የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ምክር ቤት ከተመሰረተ በኋላ ባካሄዳቸው ጉባኤዎች በርካታ የሕግ ማዕቀፎችን ማፅደቁን አስታውሰው በአሁኑ ጉባኤም የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችና ደንቦችን ማጽደቁን ተናግረዋል። በተመሳሳይ ከ94 በላይ ከወረዳ እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚያገለግሉ ዕጩ ዳኞችን ሹመቶ በማጽደቅም መጠናቀቁን ጠቅሰዋል። ምክር ቤቱ በተለይም በ2016 በጀት ዓመት አፈፃፀም በጥልቀት በመገምገም ጠንካራ ጎኖቾ አንዲቀጥሉና ክፍተቶች እንዲታረሙ የሚያስችል አቅጣጫ ማስቀመጡን አፈ ጉባኤዋ ገልጸዋል። ለአብነትም በግብርና ምርታማነት እና በሰላምና ፀጥታ ማረጋገጥ ከምክር ቤቱ ወሳኝ አጀንዳዎች መካከል እንደሆኑ ገልጸዋል። በአጠቃላይ ምክር ቤቱ ለክልሉ ሁለንተናዊ ጉዞ የሚበጁ ወሳኝ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ያሳለፈበት ስኬታማ ጉባኤ መሆኑን አብራርተዋል። ምክር ቤቱ ለ2017 በጀት ዓመት የቀረበለትን 33 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ረቂቅ በጀት ያጸደቀ መሆኑ ይታወቃል።  
በብሔረሰብ አስተዳደሩ የመንግስት ሠራተኛው ሠላምን በማስጠበቅ ላይ የድርሻውን መወጣት አለበት
Jul 25, 2024 119
ሰቆጣ፤ ሐምሌ 18 / 2016 (ኢዜአ)፡- በዋግኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የመንግስት ሠራተኛው ሠላምን በማስጠበቅ ላይ የድርሻውን በመወጣት ለህብረተሰቡ ቀልጣፍ አገልግሎት መስጠት እንዳለበት የብሔረሰብ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ዋና አስተዳዳሪ አሳሰቡ። የብሔረሰብ አስተዳደሩ የመንግስት ሠራተኛ "ሠላም ለሁሉም ሁሉም ለሠላም'' በሚል መሪ ሀሳብ የሠላም ውይይት መድረክ በሰቆጣ ከተማ ዛሬ አካሂዷል። በዚህ ወቅት የብሔረሰብ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሃይሉ ግርማይ እንደገለጹት፤ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የፀጥታ ስራ በመከናወኑ የብሔረሰብ አስተዳደሩን ሠላም ማስጠበቅ ተችሏል።   በብሔረሰብ አስተዳደሩ ያለውን ሠላም ለማስቀጠል ህዝቡ አንድነቱን ይበልጥ በማጠናከር ለአካባቢው ሠላም ዘብ ሊቆሙ ይገባል ብለዋል። የመንግስት ሠራተኛውም ሠላምን በማስጠበቅ ላይ የድርሻውን በመወጣት ለህብረተሰቡ ቀልጣፍ አገልግሎት ለመስጠት መረባረብ እንዳለበት አሳስበዋል። የብሄረሰብ አስተዳደሩ የተቀዳሚ የዋና አስተዳደሪው የህዝብ ተሳትፎና አደረጃጀት ዋና አማካሪ አቶ ዳግም ባይነሳኝ በበኩላቸው፤ ችግሮችን በሠላም ለመፍታት እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ውስጥ ህዝቡ ብሎም የመንግስት ሠራተኛው ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳላቸው ተናግረዋል። ሠላምን በዘላቂነት ለማስቀጠል የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌላውም ማህበረሰብ የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ አመልክተዋል። የመድረኩ ተሳታፊዎች፤ በአካባቢው አስተማማኝ ሠላም እንዲሰፍን የሚደግፉ መሆናቸውን አስታውቀዋል።    
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ጉባዔ የተለያዩ አዋጆችና ሹመቶችን በማፅደቅ ተጠናቀቀ
Jul 25, 2024 130
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 18/2016(ኢዜአ)፦የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ የተለያዩ አዋጆችና ሹመቶችን በማፅደቅ ተጠናቀቀ። ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የነበረው የምክር ቤቱ 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ ዛሬ ተጠናቋል። በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ካሳለፈባቸው ጉዳዮች መካከል የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችና ደንቦች ይገኙበታል። ምክር ቤቱ ካፀደቃቸው ረቂቅ አዋጆች መካከል የከተማ ቆሻሻ አወጋገድ ረቂቅ አዋጅ፣ የፋይናንስ ረቂቅ አዋጅ፣ የግዥና ንብረት አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ፣ የዋና ኦዲተር ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣ ረቂቅ አዋጅ ይጠቀሳሉ። የገጠር መሬት መጠቀሚያ ክፍያ እና የግብርና ስራ ገቢ ግብር ረቂቅ፣ የክልሉን የአመራር አካዳሚ ለማቋቋም የወጣ ረቂቅ አዋጅ እና የምግብና መድሃኒት ጤና እና ጤና ነክ ጉዳዮች ረቂቅ አዋጅ፣ የደን ልማትና ጥበቃ አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ፣ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ እና የክልሉ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ለማቋቋም የወጣ ረቂቁ አዋጆችም ይገኙበታል። በጉባኤው በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቅራቢነት በፌዴሬሽን ምክር ቤት የማረቆ ብሔረሰብን ወክለው የተመረጡት ጀማል ማሮ የተመረጡበትን ህዝብ ወክለው በፌደሬሽን ምክር ቤት አባል እንዲሆኑ የቀረቡ ሲሆን ምክር ቤቱም ሹመቱን አፅድቋል። በሌላ በኩል ምክር ቤቱ ከወረዳ እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚያገልግሉ 94 ዕጩ ዳኞችን ሹመትም አፅድቋል። ከነዚህም መካከል 13ቱ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ዳኞች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ለዞን፣ ለከተማ አስተዳደርና ለወረዳ ፍርድ ቤቶች የሚያገለግሉ ዳኞች ናቸው። በመሆኑም የዳኞቹ ሹመት በአንድ ተቃውሞ፣ በሁለት ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ ጸድቋል።  
በሀገረ-መንግሥት ግንባታም ሆነ በሀገራዊ ምክክሩ ሴቶች ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸው ይሠራል-ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)
Jul 25, 2024 145
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 18/2016(ኢዜአ)፦ በሀገረ-መንግሥት ግንባታም ሆነ በሀገራዊ ምክክሩ ሴቶች ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸው ይሠራል ሲሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለጹ። የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) መንግስት ባለፉት አመታት ሲሰራበት የቆየውና ዜጎችም ሲጠየቁ የኖሩት በሀገራዊ ምክክር አማካኝነት መሰረታዊ ችግሮችን በውይይት የመፍታት እሳቤ አሁን ላይ ወሳኝ ሊባል በሚችል ምዕራፍ ላይ መድረሱን ገልፀዋል፡፡ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በሀገረ-መንግስት ግንባታም ሆነ በሀገራዊ ምክክሩ ሴቶች የተሟላና ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸው ከሚመለከታቸው ባለድርሻና አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት የተለያዩ መድረኮችን ሲያመቻችና የበኩሉን ድርሻ ሲወጣ መቆየቱን አንስተዋል፡፡   እንደ ሀገር በሚፈጠሩ አለመግባባቶች እና የሃሳብ ልዩነቶች ግንባር ቀደም ተጎጂዎች ሴቶች መሆናቸውን የጠቀሱት ሚኒስትሯ አካታች ሀገራዊ ምክክር ማካሔድ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር እና ተቀራርቦ የመስራት ባህልን ለማጎልበት ጉልህ አስተዋፆ ስለሚያበረክት ኮሚሽኑ ኃላፊነቱን ለመወጣት እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል። ጥምረት ለሴቶች ድምፅ ካለፈው መጋቢት እስከ ግንቦት ባሉት ጊዜያት በስምንት ክልሎች እና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች በመዘዋወር በሺዎች ለሚቆጠሩ ሴቶች የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት አጀንዳዎቻቸውን የማሰባሰብ እና የማጠናቀር ተግባር ሲያከናውን መቆየቱን በመጠቆም ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል።   የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ አሸናፊ ሆነን እንውጣ ከተባለ መመካከር አለብን በምክክሩም ሴቶችን ይዘን መውጣት አለብን ብለዋል። የሴቶች አጀንዳ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አጀንዳ ነው ሲሉም ዋና ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።   የጥምረት ለሴቶች ድምፅ ፕሬዝዳንት ሳባ ገ/መድህን በበኩላቸው በአገራዊ የምክክር መድረክ በሴቶች ተገቢውን ውክልና አግኝተው የራሳቸውን ሚና እንዲጫወቱ ማድረግ መሆኑንም መግለጻቸውን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
በክልሉ ሠላምን በዘላቂነት ለማስፈን ህዝቡ ዋነኛ  ባለቤት ሆኖ መንቀሳቀስ አለበት 
Jul 25, 2024 123
ሰቆጣ፤ ሐምሌ 18/2016 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ዘላቂ ሠላምና መረጋጋትን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት በየአካባቢው ያለው ህዝብ ዋነኛ የሠላም ባለቤት ሆኖ መንቀሳቀስ እንዳለበት ተገለጸ። ''ሠላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሠላም'' በሚል መሪ ሃሳብ የዋግ ኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የመንግስት ሠራተኞች የተሳተፉበት የውይይት መድረክ በሰቆጣ ከተማ እየተካሄደ ነው።   በዚህ ወቅት የብሔረሰብ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሃይሉ ግርማይ እንዳመለከቱት፤ በአካባቢው አጋጥሞ በነበረው ችግር ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ደርሷል። ችግሩን በሰለጠነ አግባብ በጠረጴዛ ዙሪያ በሠላም እንዲፈታ በህብረተሰቡ ዘንድ በተደጋጋሚ ሲጠየቅ እንደቆየ አውስተው፤ ለዚህም መንግስት ቁርጠኛ አቋም ይዞ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በክልሉ ሠላምና መረጋጋት በዘላቂነት ለማስቀጠል የፀጥታ አካላት ከሚያከናወኑት ተግባራት ባለፈ በየአካባቢው ያለው ህዝብ ዋነኛ የሠላም ባለቤት ሆኖ መንቀሳቀስ እንዳለበት አመልክተዋል።    
በሀገራዊ የምክክር ሂደትና የተለያዩ የልማት ፕሮግራሞች የሴቶች ትብብርና ተሳትፎ እያደገ ነው
Jul 25, 2024 341
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 18/2016(ኢዜአ)፦ በሀገራዊ የምክክር ሂደትና የተለያዩ የልማት ፕሮግራሞች የሴቶች ትብብር፣ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱን የብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ፕሬዝዳንት ዘሀራ ኡመድ ገለጹ። በኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ የምጣኔ ኃብትና የማኅበራዊ ልማት ዘርፎች የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እመርታዊ ለውጥ እያመጣ ይገኛል። በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወኑ ባሉ ብሔራዊ ኢኒሼቲቮችና የልማት ሥራዎች ሴቶች በብዛትና በንቃት ከመሳተፍ ባለፈ ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸው ይታወቃል። የብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ፕሬዝዳንት ዘሀራ ኡመድ፤ በዚህ ረገድ ለተገኘው ስኬት ሀገር እየመራ የሚገኘው ፓርቲ ሚናውን በመወጣቱ መሆኑን ተናግረዋል። በሀገራዊ የምክክር ሂደትና የተለያዩ ሀገራዊ የልማት ፕሮግራሞች የሴቶች ትብብርና ተሳትፎ በተጨባጭ እያደገ መምጣቱን ገልፀዋል። በሀገራዊ ምክክር ሂደት የሴቶች ተሳትፎ 50 በመቶ እንዲሆን ኮሚሽኑ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ተሳትፎው እንዲጠናከር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል። በሀገራዊ የምክክር ሂደትና የተለያዩ የልማት ፕሮግራሞች የሴቶች ትብብር፣ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱን ገልፀዋል። የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርን ጨምሮ በሌማት ትሩፋት፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ ሌሎችም የልማት ተግባራትና የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሴቶች በንቃት እየተሳተፉና ተጠቃሚም እየሆኑ ነው ብለዋል። በዘንድሮው ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ6 ሚሊየን በላይ ሴቶች እየተሳተፉ መሆኑንም ወይዘሮ ዘሀራ ለአብነት ጠቅሰዋል። በብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ አማካኝነት ተግባራዊ እየተደረገ ያለው "ምግቤን ከጓሮዬ፤ ጤናዬን ከምግቤ'' የሚለው ንቅናቄም በሀገር አቀፍ ደረጃ በስኬት እየተከናወነ ይገኛልም ብለዋል። በአረንጓዴ አሻራ እና የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብሮችም የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ተጨባጭ ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን ጠቅሰዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም