ሰላማችንን በማጽናት በከተማችን የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት እንዲበቁ የድርሻችንን ለማበርከት ዝግጁ ነን

ጎንደር ፤ሰኔ 22/2017 (ኢዜአ)  ሰላማችንን በማጽናት በከተማችን የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ የድርሻችንን ለማበርከት ዝግጁ ነን ሲሉ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት ሰላምን የሚደግፍና ጽንፈኝነትን የሚያወግዝ ህዝባዊ ሰልፍ ዛሬ በጎንደር ከተማ ተካሂዷል፡፡


 

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች እንደተናገሩት ጎንደር በከፍተኛ የልማት ሥራ ላይ ትገኛለች፤ ሰላሙንና ልማቱን ለማስቀጠል ደግሞ እኛ ነዋሪዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ቁርጠኞች ነን ሲሉ ተናግረዋል

"ጎንደር የቀደመ ገናና ስሟንና ታሪኳን የሚመጥን የመልማት እድል ያገኘችው አሁን ነው" ያሉት በህዝባዊ ሰልፉ ላይ የተሳተፉት አቶ ጌትነት መንግስቱ ናቸው፡፡


 

ከተማዋ ያገኘችው ዘርፈ ብዙ የልማት እድሎች ለህዝቡ የዘመናት የልማት ጥያቄ መሰረታዊ ምላሽ የሚሰጡ በመሆናቸው ለሰላም ዘብ በመቆም ልማቱን ለማስቀጠል የድርሻቸውን ለማበርከት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

ሌላዋ የሰልፉ ተሳታፊ ወይዘሮ አለምነሽ ብርሃኑ በበኩላቸው በከተማው እየተካሄዱ የሚገኙ የኮሪደር ልማትና የአጼ ፋሲል አብያተ መንግስት እድሳትና ጥገና ሥራዎች ታሪካችንን ያደሱ አኩሪ የልማት ተግባራት ናቸው ብለዋል፡፡

"ጎንደር በአሁኑ ወቅት ያገኘችው የልማት ዕድል በምንም መንገድ ወደኋላ ሊመለስና ሊቀለበስ የማይችል ነው" ያሉት ወይዘሮ አለምነሽ ለልማትና ለሰላም ጸር የሆነውን ጽንፈኝነት ለመታገል ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

በፌደራልና በክልሉ መንግስት ድጋፍ በከተማችን እየተካሄዱ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች በርካታ ወጣቶችን የሥራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ አስችሏል ያለው ደግሞ ወጣት መሃመድ አብዲ ነው፡፡

በለውጥና በአዲስ የእድገት ጎዳና ላይ የምትገኘው ሀገራችን ወጣቶች በሃገራቸው ብሩህ ተስፋ እንዲሰንቁና ለልማትና ሰላም ማስፈን እንዲተጉ መነሳሳት ፈጥሯል ብሏል።


 

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው በሰልፉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በጎንደር ከተማ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች መጀመራቸውን አስታውሰዋል።

የከተማው ህዝብ ከዳር አስከ ዳር በመነሳት የልማት ሥራዎችን በገንዘብ፣ በጉልበቱና በእውቀቱ እየደገፈ መሆኑን የጠቆሙት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው፣ "ጎንደር ለሰላም ዋጋ የምትሰጥ ከተማ ነች" ብለዋል፡፡

ለከተማዋ እድገት አስተዋጽኦ ላደረጉ የፌደራልና የክልሉ አመራሮች እንዲሁም በሀገር ውስጥና በውጭ ላሉ ወገኖችም ምስጋና አቅርበዋል።


 

በህዝባዊ ሰልፉ ላይ የመንግስት ሠራተኞች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም