ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ እና ልማት እንዲፋጠን ድጋፋችንን እናጠናክራለን - ኢዜአ አማርኛ
ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ እና ልማት እንዲፋጠን ድጋፋችንን እናጠናክራለን

ባህርዳር፤ ሰኔ 22/2017 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ እና የልማት ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በባህርዳር ከተማ የህዝባዊ ሰልፍ ተሳታፊዎች ገለጹ።
በባህርዳር ከተማ ‘‘ሀገርን ለማፅናት እና ለማበልፀግ ከመንግስት ጎን እንሰለፋለን’’ በሚል መሪ ሀሳብ ሰላምን የሚደግፍ ህዝባዊ ሰልፍ ዛሬ ተካሂዷል።
ከሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል ወጣት ትዕዛዙ ገብረኢየሱስ ለኢዜአ እንደገለጸው በክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ማረጋገጥ ለህዝቡ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው።
በክልሉ አሁን ላይ ባለው ሰላም በከተማው ልማት እንዲፋጠንና የወጣቶች ተጠቃሚነት እያደገ እንዲመጣ ማስቻሉን ገልጿል።
የተገኘው ሰላም ዘላቂ እንዲሆንና የልማት ስራዎች እንዲጠናከሩ ተሳትፏችንን እናጠናክራለን " ያለው ወጣት ትዕዛዙ የታጠቁ ሀይሎች የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ወደ ሰላም እንዲመጡ ጠይቋል ።
"የሰላም እጦት የሚያስከትለው ጥፋት በመሆኑ ለሰላም ዘብ ለመቆም ቆርጠን ተነስተናል" ያሉት ደግሞ የሰልፉ ታዳሚ ወይዘሮ አስረሱ ጌትነት ናቸው።
በከተማው አሁን ላይ ባለው ሰላም ተስፋ ሰጭ የልማት ስራዎች እየተፋጠኑ መሆኑን ተናግረዋል።
"በጫካ ላሉ የታጠቁ ሀይሎች የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ሰላም ሊመጡ ይገባል" ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል።
‘‘በክልላችን ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ ድምፃችንን ለማሰማት በሰልፉ ተሳትፈናል ’’ ያለው ደግሞ ወጣት ሳለአምላክ አድማሱ ነው።
ሰላም ለአንድ ወገን የሚተው አለመሆኑን ጠቁሞ "ሁላችንም ከመንግስት ጎን በመሰለፍ ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ልማት እንዲረጋገጥ በቁርጠኝነት ልንሰራ ይገባል" ብሏል።
የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው የከተማው አስተዳደር ሰላምን በማጽናት ልማትን ለማረጋገጥ በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
"ፅንፈኛው ኃይል በክልሉና በከተማችን ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት አድርሷል" ያሉት አቶ ጎሹ ህፃናት ከትምህርት ገበታ እንዲርቁ ማድረጉን ጠቅሰዋል።
የፅንፈኛው ሀይል የክልሉን ልማትና ዕድገት ወደ ኋላ የሚጎትት በመሆኑ ህብረተሰቡ በዛሬው ሰልፍ ጽንፈኝነትን በማውገዝ የመንግስትን የሰላም ጥሪ የደገፈበት መሆኑን ተናግረዋል ።
ጫካ የሚገኙ ኃይሎች የሰላም ጥሪን ተቀብለው ህዝባቸውን እንዲክሱም አሳስበዋል።
በከተማው ሰላምን ዘላቂ ለማድረግና ልማትን ለማፋጠን እየተደረገ ባለው ጥረት የህብረተሰቡ ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው ይኽው የህዝቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል ።
በሰልፉ ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።