ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ስርዓቶች ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ስራ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው - ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ - ኢዜአ አማርኛ
ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ስርዓቶች ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ስራ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው - ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 20/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሰላም ግንባታና በአብሮነት የመኖር እሴት እንዲጎለብት ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ስርዓቶች ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ ገለጹ።
በተሳሳተ ስሌት ነፍጥ ያነገቡ አካላት መንግስት የፈጠረውን የሰላም አማራጭ እንዲቀበሉ በማስቻል በኩል የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች የማግባባት ሚናቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
ሰላም ሚኒስቴር "ማህበራዊ ሀብቶቻችን ለህብረ-ብሔራዊ አንድነታችን" በሚል መሪ ሀሳብ ሀገር አቀፍ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የጎሳ መሪዎችና የሰላም ተቋማት አመራር አባላት የምክክር መድረክ አካሂዷል።
የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ስርዓቶች የማይተካ ሚና አላቸው።
መንግስት ኢትዮጵያ ካለፈችባቸው የፖለቲካ ታሪክ በሚመነጩ ተግዳሮቶች ለሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ምላሽ ለመስጠት የሰላም አማራጭን የማስፋትና ህግ የማስከበር ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶችም በተሳሳተ ስሌት ነፍጥ ያነገቡ አካላት መንግስት የፈጠረውን የሰላም አማራጭ እንዲቀበሉ በማስቻል ሂደት የማግባባት ሚናቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ አንስተዋል።
የሰላም ሚኒስቴርም የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ያካበቱትን የግጭት አፈታትና የሰላም ግንባታ ስራን ለማስቀጠል በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።
በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ የተካሄደው የምክክር መድረክ የልምድ ልውውጥና የእርስ በእርስ ትውውቅ የተፈጠረበት መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የመድረኩ ተሳታፊዎች በሀገር በቀል የሰላም ግንባታና የግጭት አፈታት ዕውቀትና እሴታቸውን በመጠቀም ቀጣይነት ያለው ስራ የሚሰሩበትን ሥርዓት መዘርጋቱን ገልጸዋል።