በቀበሌ ደረጃ መንግስታዊ አገልግሎት ተደራሽ መደረጉ ቀልጣፋ አገልግሎት ከማስገኘቱ ባለፈ የልማት ተሳታፊነታችንን እያሳደገ ነው -ነዋሪዎች

ጭሮ ፤ ሰኔ 23/2017(ኢዜአ)፦ በምዕራብ ሀረርጌ ዞን በቀበሌ ደረጃ መንግስታዊ አገልግሎት ተደራሽ በመደረጉ ለአስተዳደራዊ ጉዳዮቻቸው ፈጣን ምላሽ ከማስገኘቱ ባለፈ የልማት ተሳታፊነታቸው እያደገ መምጣቱን የዞኑ ዶባ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።

በዞኑ በአዲስ መልክ ለተዘረጋው የቀበሌ አስተዳደር አገልግሎት መስጫ የሚውሉ ጽህፈት ቤቶች ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እየተደረጉ ነው።

ነዋሪዎቹ በሰጡት አስተያየት ለህብረተሰቡ ቅርብ የሆኑ የቀበሌ መዋቅሮች ከዚህ ቀደም ትኩረት በማጣታቸው አገልግሎት ፍለጋ እስከ ወረዳ ማዕከላት ሲመላለሱ ቆይተዋል።

በአሁኑ  ወቅት  የቀበሌ ፅህፈት ቤቶች በዘመናዊ መልኩ ተገንብተው ሙሉ አገልግሎት እያገኙ መሆኑን የተናገሩት በወረዳው የባቱ ቀበሌ ነዋሪ ኢብራሂም ሁሴን ናቸው።


 

በጤና፣ በትምህርት፣ በግብርና እና መሰል ጉዳዮች አገልግሎት ፍለጋ እስከ ወረዳ ማዕከል ድረስ ሲመላለሱ እንደነበር ያነሱት አስተያየት ሰጪው አሁን ላይ እነዚህን አገልግሎቶች በአካባቢያቸው በሚገኝ ቀበሌ ጽህፈት ቤት በቅርበት አገልግሎት ማግኘት ጀምረዋል።

ከዚህ ቀደም በወረዳ ደረጃ ብቻ የሚያገኙትን የመሬት ነክ እና ግብርና አገልግሎቶችን በቀበሌ ማግኘታቸው የልማት ተሳታፊነታቸውን እያሳደገ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አህመድ ኢብሮ ናቸው።

ይህም የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸውን በማቃለል በአካባቢያቸው በሚከናወኑ የልማት ስራዎች ውስጥ ተሳትፏቸው እንዲጨምር ማድረጉንም ተናግረዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የዶባ ወረዳ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ሙዘይን ከማል እንዳሉት በወረዳው የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ በተጀመረው የቀበሌ አገልግሎት ማጠናከር ስራ ህብረተሰቡ በቅርበት አገልግሎት እንዲያገኝ ማድረግ ተችሏል።

ሙሉ አገልግሎቶች ለህብረተሰቡ በቅርበት እንዲሰጡ በመደረጉም አርሶ አደሩ ከግብርና ስራው እንዳይስተጓጎል ሁሉንም መንግስታዊ አገልግሎት በቅርበት እንዲያገኝ ማድረጉን ተናግረዋል።

በምዕራብ ሐረርጌ ዞን በሚገኙ 15 ወረዳዎችና አምስት ከተሞች የቀበሌ አደረጃጀቶችን በማጠናከር 3 ሺህ 522 ባለሙያዎች ተመድበው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ወይዘሮ ኢክራም ጠሀ ናቸው።


 

በዚህም 512 የቀበሌ ፅህፈት ቤቶች በዘመናዊ መልኩ እንዲገነቡ መደረጉን አመልክተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም