ወጣቶች ሰላምን በማዝለቅ ለጠንካራ ሃገረ መንግስት ግንባታ እየተወጡ ያለውን ሚና ሊያጠናክሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቶች ሰላምን በማዝለቅ ለጠንካራ ሃገረ መንግስት ግንባታ እየተወጡ ያለውን ሚና ሊያጠናክሩ ይገባል

ባህር ዳር፤ ሰኔ 21/2017 (ኢዜአ) ፡-ወጣቶች ሰላምን በማዝለቅ ለጠንካራ ሃገረ መንግስት ግንባታ እየተወጡ ያለውን ሚና አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተጠቆመ።
በብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል የወጣቶች ክንፍ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር "ሀገሬን እገነባለሁ ኃላፊነቴን እወጣለሁ" በሚል መሪ ሃሳብ ክልላዊ የውይይት መድረክ በባህር ዳር እየተካሄደ ነው።
በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፍስሃ ደሳለኝ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት እንዳሉት ወጣቶች ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የማይተካ ሚና አላቸው።
በፅንፈኛ ኃይሉ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በወጣቶችና ሌላው ማህበረሰብ የነቃ ተሳትፎ አሁን ላይ የክልሉ የሰላም ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል።
ወጣቱ በመጣው ሰላም ላይ በመመስረትም የለውጡ ትሩፋት በሆነው የልማት ተግባራት ላይ ንቁ ተሳታፊ በመሆን የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ የሚጠበቅበትን እንዲወጣ አሳስበዋል።
"ወጣትነት የእውቀትና የትኩስ ጉልበት ሃብት ነው" ያሉት አቶ ፍስሃ አሁን የተገኘውን ሰላም በማጽናት ለአገር እድገትና ለህዝብ ተጠቃሚነት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
አሰባሳቢ ትርክትን በማስረፅና ህብረ-ብሄራዊ አንድነትን በማጠናከር የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞን ለማረጋገጥ ወጣቶች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሊረባረቡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት በመሆኑ በሰላም ግንባታ ላይ ወጣቶች የጀመሩትን ጥረት በቀጣይም አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።
እንዲሁም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በውጤታማነት እንዲከናወን በተሳትፎና በማስተባበር ሚናቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።
ለግጭት መንስኤ የሆኑ ችግሮች እንዲፈቱና ተከስተው ሲገኙም ፈጥኖ ግጭቶችን ለማስቆም የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በሰላም ሚኒስቴር የግጭት ጥናትና ትንተና ዴስክ ኃላፊ አቶ ይትባረክ ተስፋዬ ናቸው።
የዛሬው መድረክም ወጣቶች በሰላምና በሀገረ መንግስት ግንባታ ላይ የራሳቸውን ድርሻ እንዲወጡ ግንዛቤ ለመፍጠር አልሞ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የዴሞክራሲና ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ መስፍን አበጀ (ዶ/ር) በበኩላቸው ሀገራዊ ጥቅምን የሚያስጠብቅ ትውልድን ለመቅረፅና ለመገንባት የብልፅግና ፓርቲ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በተለይ የተዛቡ አስተሳሰቦችን በማረም፣ ህብረ-ብሄራዊ አንድነትንና ዘላቂ ሰላምን ለማጠናከርና ልማትን ለማፋጠን ወጣቱ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
‘‘ወጣቶች የሀገራችንን ሰላም አፅንተን ለማዝለቅና ልማቱን አጠናክረን ለማስቀጠል የዚህ ዘመን አሻጋሪ ትውልዶች ነን’’ ያለው ደግሞ የመድረኩ ተሳታፊ ወጣት ነቢዩ ጌቱ ነው።
እኛ ወጣቶች የማንም ሃሳብ ተሸካሚና መጠቀሚያ ሳንሆን ሰላምን ከማፅናት ጎን ለጎን የስራ ባህላችንን በመለወጥ ወደ ብልፅግና የሚደረገውን ጉዞ አጠናክረን ልንቀጥል ይገባል ብሏል።
ለአንድ ቀን በተዘጋጀው ክልላዊ የማጠናቀቂያ የወጣቶች መድረክ ላይም ከክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የተውጣጡ ወጣቶች፣ የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ኃላፊዎችና ሌሎች እንግዶች ተሳትፈዋል።