ኢትዮጵያ በአስደናቂ የህዳሴ ጉዞ ላይ ናት - የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ካሺም ሼቲማ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 20/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአስደናቂ የህዳሴ ጉዞ ላይ ትገኛለች ሲሉ የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ካሺም ሼቲማ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከናይጄሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ካሺም ሼቲማ ጋር ቁልፍ በሆኑ የሁለትዮሽ እና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ይታወቃል።

ምክትል ፕሬዝዳንቱ የኢትዮጵያን አስደናቂ ቅርሶችና ታሪኳን አጉልቶ በሚያሳይ መልኩ ታድሶ ለዕይታ ክፍት የሆነውን ብሔራዊ ቤተመንግሥትንም ጎብኝተዋል።


ጉብኝታቸውን በተመለከተም በይፋዊ የክብር መዝገብ ላይ ባሰፈሩት የማስታወሻ መልዕክት ብሔራዊ ቤተ መንግሥቱ ህያው ታሪክ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቅኝ ያልተገዛች ብቸኛዋ ሀገር መሆኗን ያወሱት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፥ በአስደናቂ የህዳሴ ጉዞ ላይ ትገኛለች ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ ድንቅ የታሪክ ጸጋና ታላቅ ሀገርነት ኩራት እንደተሰማቸውም ነው በመልዕክታቸው የጠቀሱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም