በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ጥቅምን በማስጠበቅ እያደረጉ ያለውን አስተዋጽኦ ማጠናከር ይገባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ጥቅምን በማስጠበቅ እያደረጉ ያለውን አስተዋጽኦ ማጠናከር ይገባቸዋል

አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 22/2017(ኢዜአ)፦ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን ብሔራዊ ጥቅም በማስጠበቅ እና በልማት እያደረጉ ያለውን አስተዋጽኦ የበለጠ እንዲያጠናክሩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና ከውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሃላፊዎች የዳያስፖራውን ተሳትፎ በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ምክክር አካሂዷል።
የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢው ዲማ ኖጎ (ዶ/ር) ዳያስፖራው የሀገሩን ብሔራዊ ጥቅም በማስከበርና በልማት በመሳተፍ ሚናው የጎላ እንደሆነ አንስተዋል።
በተለያየ ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ብሔራዊ ጥቅምን በሚያስከብሩ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ ለሀገራቸው በተለያየ ዘርፍ የሚያደርጉትን አስተዋፅኦ እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
ዳያስፖራው በሪሚታንስ፣ ኢንቨስትመንትና በበጎ አድራጎት እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ የበለጠ ለማሳደግ በሚወጡ ህጎች የዳያስፖራውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ትኩረት እንዲሰጡ ይደረጋል ብለዋል።
የዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍጹም አረጋ እንደተናገሩት በተለያየ የዓለም ክፍል የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እየጨመረ ነው።
በኢንቨስትመንት፣ በሪሚታንስ፣ በበጎ አድራጎት፣ በልማት ስራዎች ላይ የሃሳብና የገንዘብ ተሳትፎ በማድረግ፣ በቱሪዝምና ሌሎች ዘርፎች ተሳትፏቸው እየጨመረ መምጣቱን ነው ያስረዱት።
በሀገር የኢኮኖሚ እድገት ላይ ያላቸውን ተሳትፎ የበለጠ ለማሳደግ የአሰራር ማሻሻያዎች እየተደረጉ መሆኑን አምባሳደር ፍጹም ተናግረዋል።
አሰራርን ከማዘመን አንጻር የኦንላይን ቪዛ አገልግሎት፣ ውክልና እና ሰነድ ማረጋገጥን በሚመለከት የሚወስደውን ረዥም ጊዜ በማሳጠር በ24 ሰዓት ማረጋገጥ የሚቻልበት ስርዓት ተዘርግቷል ብለዋል።
የምክር ቤት አባላት ወደ ምርጫ ክልላቸው በሚሄዱበት ወቅት የዳያስፖራ ጉዳይ የሚስተናገድበትንና በስራ ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን ሂደት ክትትል እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዮት ዋና ዳሬክተር ጃፋር በድሩ እንደተናገሩት የውጭ ግንኙነት ስራ በዲፕሎማቶች ብቻ የሚሰራ ባለመሆኑ የባለድርሻ አካላትን ሚና ለማሳደግ እየተሰራ ይገኛል።
በውይይቱ የተሳተፉ የቋሚ ኮሚቴ ሃላፊዎች በበኩላቸው፥ ዳያስፖራው በኢንቨስትመንትና ሌሎች የልማት ስራዎች በሚያደርገው ተሳትፎ የሚያጋጥሙ የአሰራር ማነቆዎችን ለመፍታት ክትትልና ቁጥጥራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ዳያስፖራው በሀገራዊ ዕድገት ውስጥ ተጠቃሚ እንዲሆን የተሰጠው ትኩረትና የተደረጉ የህግ ማሻሻያዎች ለውጥ እያመጡ ነው ብለዋል።
በመድረኩ በዳያስፖራና ኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ እንዲሁም ፍልሰት አስተዳደር ላይ ትኩረት ያደረጉ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የምክክሩ ዓላማ የምክር ቤት አባላት በክረምት የእረፍት ጊዜ ወደ ምርጫ ክልላቸው በሚሄዱበት ወቅት በዳያስፖራ ዙሪያ መነሳት ያለባቸው ጉዳዮችና ከሀገር ውጭ ለስራ በሚሄዱበት ወቅትም ትኩረት ማድረግ ያለባቸውና የሚያስፈልጉ ድጋፎች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር መሆኑ ታውቋል።