ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ የሦስት አገራት አምባሳደሮችን አሰናበቱ

አዲስ አበባ፤ሰኔ 23/2017(ኢዜአ)፦የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በኢትዮጵያ የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ የካናዳ፣የስዊዲንና የሳኡዲ አረቢያ አምባሳደሮችን አሰናበቱ።

ፕሬዝዳንቱ ያሰናበቱት የካናዳ አምባሳደር ጆሽዋ ታባህ፣የስዊድን አምባሳደር ሃንስ ሄንሪክና የሳኢዲ አረቢያ አምባሳደር ፋሃድ አልሁማያዳኒ (ዶ/ር) ናቸው።

ፕሬዝዳንት ታዬ ሦስቱም አምባሳደሮቹ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከአገራቱ ጋር በተለያዩ መስኮች የሁለትዮሽ ግንኙነትና ትብብር እንዲጠናከር ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።


 

በተለይም የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት እንዲሳለጥ እንዲሁም በሌሎች የልማት የትብብር ዘርፎች ግንኙነቱ እንዲጠናከር ላደረጉት አስተዋጽዖም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

አምባሳደሮቹ በሌሎች መስኮች ለአብነትም በመልሶ ማልማት ሥራዎች ጉልህ አስተዋጽኦ መደረጉን አንስተው፥ትብብሮች በቀጣይም ሊጠናከር እንደሚገባ ጠይቀዋል።

በቀጣይ በተለይም ውጤታማ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነቶች ይበልጥ ሊጠናከሩ እንደሚገባ ጥሪ ማቅረባቸውን ውይይቱን የተከታተሉት የፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አምባሳደር ትዝታ ሙሉጌታ ለኢዜአ ገልጸዋል።

አምባሳደሮቹ በበኩላቸው፥ በኢትዮጵያ ቆይታቸው አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር በርካታ ሥራዎች መሥራታቸውንና በዚህም አመርቂ ውጤት መገኙቱን ጠቅሰዋል።

የካናዳ አምባሳደር ጆሽዋ ታባህ በቆይታቸው የካናዳና ኢትዮጵያን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማስፋት የሚያስችሉ ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።


 

በተመሳሳይ የስዊድን አምባሳደር ሃንስ ሄንሪክ በቆይታቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ቅድሚያ በሰጠባቸው መስኮች ትብብር በማድረግ አበረታች ሥራዎች ማከናወናቸውን አስረድተዋል።

አምባሳደሮቹ በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች እየተዘመገቡ ያሉ ውጤቶች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውንና መሰል ሥራዎችን ሊያጠናክር እንደሚገባ ተናግረዋል።

በቀጣይም ግንኙነቱ ይበልጥ እንዲጠናከር የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም