የመንግስትን የልማት እቅዶች በመደገፍ እና የሰላም ጥረቶች በማገዝ የድርሻችንን እንወጣለን

ደሴ፤ሰኔ 22/2017(ኢዜአ)፦  የመንግስትን የልማት እቅዶች በመደገፍና የሰላም ጥረቶች በማገዝ የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ በደሴ ከተማ በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የተሳተፉ ነዋሪዎች ተናገሩ።

በደሴ ከተማና አካባቢው ሰላምና ልማትን የሚደግፍና ፅንፈኝነትን የሚያወግዝ ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሃዷል።

ከሰላማዊ ሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ዘሪሁን ማንደፍሮ፣ ወይዘሮ መብራት ፈለቀ እና አቶ ሰለሞን አሰፋ፤ ከምንም በላይ ሰላምና ልማታችንን አጥብቀን እንሻለን ጸረ ሰላም ቡድኖችን ደግሞ እናወግዛለን ብለዋል።

የደሴና አካባቢው ሰላም አስተማማኝ የሆነው በህዝቡ ትብብርና ጥረት፣ በፀጥታ አካላት ትጋት መሆኑን አንስተው ይህንኑ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉም ተናግረዋል።

በመሆኑም የመንግስትን የልማት እቅዶችን በመደገፍና የሰላም ጥረቶችን በማገዝ የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ አረጋግጠዋል።


 


 

የመንግስት የሰላምና የልማት ጥረት የሚደገፍ በመሆኑ ለሰላማዊ ሰልፍ መውጣታቸውን ተናግረው ለእኩይ ዓላማ የሚንቀሳቀሱ አካላት ከድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባም አንስተዋል።


 

በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በህዝብ ስም እየማሉ ግድያ፣ ዘረፋ፣ እገታና ውንብድና የሚፈጽሙ ጽንፈኞችን በፅኑ እናወግዛለን፤ ለሰላማችንም ዘብ እንቆማለን ሲሉ ተናግረዋል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ፤ በሁሉም አካባቢዎች ህብረተሰቡ አንድነቱን በማጠናከር እያሳየ ያለውን ሁለንተናዊ ድጋፍና ተሳትፎ አድንቀዋል።


 

ከውጭ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር ሀገርን ለማፍረስ የሚሰሩ ቡድኖች ከክህደት እና ሸፍጥ በመውጣት ለሀገር ልማትና እድገት በጋራ እንዲቆሙም ጠይቀዋል።

የተጀመሩ ሀገራዊ የልማት እቅዶችን ከዳር በማድረስ ሀገራዊ ህብረ ብሄራዊ አንድነትና ሰላምን በማፅናት ሀገር መገንባት ይጠበቅብናል ብለዋል።

በዛሬው እለት ከደሴ ከተማ በተጨማሪ በኮምቦልቻ፣ ሐይቅ እና ሌሎችም ከተሞች ተመሳሳይ ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም