ክልሉን የሰላም፣ የልማትና የመቻቻል ተምሳሌት ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት የተገኙ ውጤቶችን ማስቀጠል ይገባል - አቶ አደም ፋራህ - ኢዜአ አማርኛ
ክልሉን የሰላም፣ የልማትና የመቻቻል ተምሳሌት ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት የተገኙ ውጤቶችን ማስቀጠል ይገባል - አቶ አደም ፋራህ

ወላይታ ሶዶ ፤ሰኔ 24/2017 (ኢዜአ)፡-የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን የሰላም፣ የልማትና የመቻቻል ተምሳሌት ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት የተገኙ ውጤቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።
''ጠንካራ ክልላዊ አንድነትና አብሮነት ለዘላቂ ሠላምና ብልጽግና" በሚል መሪ ሃሳብ ክልል አቀፍ የሠላም፣ የልማት እና የአንድነት ኮንፈረንስ በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሄዷል።
በወቅቱም አቶ አደም ፋራህ እንዳሉት፤ በክልሉ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች እየተመዘገበ ያለውን ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠል ተደጋግፎ መስራት ይገባል።
ኮንፈረንሱ በክልሉ ሰላም፣ ልማትና አንድነት ላይ አዎንታዊ ለውጥ በማምጣትና የህዝቡን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የመልካም አስተዳደር ጉዳዮችን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሚያግዝ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በቀጣይ ጊዜያት ከፋፋይ ትርክቶችን በማስወገድ በመደመር ዕሳቤ ወንድማማችነት እና እህትማማችነትን አጠናክሮ በማስቀጠል የብልጽግና ጉዞን ማፋጠን ያስፈልጋል ብለዋል።
የጋራ ማንነትን የሚያጎለብቱ ህብረ-ብሔራዊነትን ለማረጋገጥ ያለፈውን ቅሬታ በይቅርታ አልፎ ለወደፊት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ጠንካራ ክልላዊ ተቋማትን ፈጥሮ በብቁ አመራር እንዲመሩ በማድረግ ብልሹ አሰራርን እና ሙስናን የሚጸየፍ ትውልድ መፍጠር እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የተለያዩ የልማት ኢኒሼቲቮችን ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር የክልሉን ብልጽግና ለማረጋገጥ መትጋት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው ከክልሉ ምስረታ ማግስት ጀምሮ አብሮነትን የሚያጸኑ የጋራ ትርክቶችን ለማስረጽ የተሰራው ስራ ውጤት ማስመዝገቡን ተናግረዋል።
ክልሉ ካለው የመልማት አቅም አንፃር ያልተሻገርናቸው በርካታ ነገሮች አሉ ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በሁሉም መስክ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መትጋት እንደሚገባ አሳስበዋል።
''ጠንካራ ክልላዊ አንድነትና አብሮነት ለዘላቂ ሠላምና ብልጽግና" በሚል መሪ ሃሳብ በወላይታ ሶዶ ከተማ ሲካሄድ የቆየው ክልል አቀፍ የሠላም፣ የልማት እና የአንድነት ኮንፈረንስ ዛሬ ተጠናቋል።