በኦሮሚያ ክልል የተገኘውን ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል ህዝብን ያሳተፈ የተቀናጀ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል የተገኘውን ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል ህዝብን ያሳተፈ የተቀናጀ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል

አምቦ፣ ሰኔ 20/2017(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የተገኘውን ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል ህዝብን ያሳተፈ የተቀናጀ ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የክልሉ ሚሊሻ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የክልሉ ሚሊሻ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበራ ቡኖ በተገኙበት በምዕራብ ሸዋ ዞን ቶኬ ኩታዬ ወረዳ የተሃድሶ ስልጠና የወሰዱ የሚሊሻ አመራሮች የምረቃ መርሃ ግብር ተካሄዷል።
ኃላፊው በወቅቱ እንደገለጹት በክልሉ የተገኘውን ሰላም በዘላቂነት ለማጽናት ከህዝቡ ጋር በቅርበትና በቅንጅት እየተሰራ ነው።
በሂደቱም ከህዝቡ ጋር የሰላምና ጸጥታ ስራዎችን የሚያስጠብቅ ጠንካራ የሚሊሻ አደረጃጀት በመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም የሚፈለገው ውጤት እየተገኘ ነው ብለዋል።
በቀጣይም በሁሉም አካባቢዎች ሰላምን የማስጠበቅና ጸጥታን የማስፈን ስራ በልዩ ትኩረት የሚሰራ መሆኑን አረጋግጠው የሚሊሻ አመራሮችና አባላትም ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበዋል።
የምዕራብ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ዲዳ ጉደታ በበኩላቸው በዞኑ አስተማማኝ ሰላም በመስፈኑ ህዝቡ በተሟላ መልኩ የልማት ስራውን በማከናወን ላይ መሆኑን አንስተዋል።
ከጥቂት ዓመታት በፊት በዞኑ ይስተዋል የነበረው የጸጥታ ችግር በአስተማማኝ መልኩ መፈታቱን ገልጸው በተጠናከረ መልኩ ቀጣይነት እንዲኖረው በቅንጅት ይሰራል ሲሉ ተናግረዋል።
በዞኑ በሚገኙ ሁሉም ቀበሌዎች የአካባቢ ሰላምና ጸጥታ የሚጠብቁ የሚሊሻ አባላት የአካባቢያቸውን ሰላም ለመጠበቅ ይበልጥ መዘጋጀት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ከተመራቂዎቹ መካከል ከባኮ ከተማ የሰለጠኑ አቶ አብዱ ኡመር፣ በስልጠና ቆይታቸው በቂ እውቀትና ክህሎት ማግኘታቸውን ገልጸው ባገኙት ስልጠና መሰረትም የሰላምና ጸጥታ ጥበቃ ስራቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።
ወደ ባኮ ከተማ ስመለስ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ህዝቡን ያሳተፈ የሰላምና ጸጥታ ጥበቃ ላይ በንቃት እሳተፋለሁ ብለዋል።
ከወልመራ ወረዳ የመጡት አቶ ተሰማ ለገሰ፣ ከአካል ብቃት ጀምሮ ለሰላምና ጸጥታ ስራ አስፈላጊ የሆኑ ስልጠናዎችን ሲወስዱ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
ወደመጡበት አካባቢ ሲመለሱም ህዝቡን በማሳተፍ አስተማማኝ ሰለምና ጸጥታ በመገንባት ሂደት የላቀ ሚናቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።