መንግስት ህግ በማስከበር ሰላምና ልማትን ለማጽናት እያደረገ ላለው ጥረት ተሳትፏችንን እናጠናክራለን

ደብረ ብርሃን፣ደብረ ማርቆስ፣ገንዳ ውሃና ወልዲያ፤ሰኔ 22/2017(ኢዜአ)፦መንግስት ህግ በማስከበር ሰላምና ልማትን ለማጽናት እያደረገ ላለው ጥረት ተሳትፏቸውን እንደሚያጠናክሩ በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች ነዋሪዎች ገለጹ።

በክልሉ ደብረ ብርሃን፣ደብረ ማርቆስ፣ መተማ ዮሐንስ እና ወልዲያ ከተሞች ሰላምን የሚደግፉና ጽንፈኝነትን የሚያወግዙ ህዝባዊ ሰልፎች ዛሬ ተካሂደዋል።

በደብረ ብርሃን ከተማ በተካሄደ ህዝባዊ ሰልፍ የተሳተፉት አቶ ከፍያለው ግርማ በሰጡት አስተያየት የሰላም እጦት ችግር በውይይትና በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የበኩላቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ታጥቀው በጫካ ያሉ ሀይሎች የመንግስትን የሰላም አማራጭ ተቀብለው ወደሰላም እንዲመጡና የሰላም ፍላጎታቸውን ለማሰማት በሰልፉ መታደማቸውን ተናግረዋል።


 

ኑሮውን ሎተሪ አዙሮ በመሸጥ የሚመራው ሌላው የሰልፉ ተሳታፊ በፍቃዱ በለጠ በበኩሉ፥ሰርቶ ለማደግና ለመለወጥ ሰላም ወሳኝ መሆኑን ገልጾ፣ ሰላም እንደሚፈልግ በጋራ ድምጹን ለማሰማት በሰልፉ መሳተፉን ገልጿል።

የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት በሰልፉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የሰላም እጦት ችግሩን ለመፍታት መንግስት ህግ ከማስከበር ጎን ለጎን ለታጠቁ አካላት በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ማቅረቡን አስታውሰዋል።


 

የጥፋት ሀይሎች በህዝብና በሀገር ላይ እየፈጸሙት ያለውን የጥፋት ተግባር በማቆም የህዝብን ጽኑ የሰላም ፍላጎት በማክበር የመንግስትን የሰላም አማራጭ ሊቀበሉ ይገባል ብለዋል።

በተያያዘ ዜና በደብረ ማረቆስ ከተማ በተካሄደ ህዝባዊ ሰልፍ ላይ የተሳተፉት ወይዘሮ እታገኝ አዳነ፥ ባለፉት ሁለት ዓመታት ያሳለፍነው ችግር እንዲያበቃ እንፈልጋለን፤ የእኛ ፍላጎት ዘላቂ ሰላምና ልማት ነው ብለዋል።

ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ወደ ሰላም እንዲመጡ እንፈልጋለን ያሉት ወይዘሮ እታገኝ፣ ለአካባቢው ሰላም መንግስት ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ የበኩላቸውን ሚና ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።


 

ሌላዋ ተሳታፊ ወይዘሮ አንለይ ተረፈ በበኩላቸው፥ ሰው በሰላም ወጥቶ መግባትና ሰርቶ መብላት የሚችለው ሰላም ሲኖር ነው ብለዋል።


 

ሌላው የሰልፉ ተሳታፊ አቶ በላይ እንየው በበኩላቸው፥ በግጭት ሰቆቃ፣ መከራና ስቃይ እንጂ የሚመጣ ለውጥ የለም ፤ ሰላምን እንደምንፈልግ በይፋ ለመግለጽ ዛሬ በሰልፉ ላይ ተገኝተናል ብሏል።

አንድነታችንን በማጠናከር ሰላምና ልማትን ማጽናት የትኩረት አቅጣጫችን ነው ያሉት ደግሞ የደብረ ማርቆስ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ተሾመ ዋለ ናቸው።

"ህዝቡ ለሰላሙ ያሳየውን ቁርጠኝነት በማስቀጠል በከተማው የተጀመረው የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ፣የኮሪደር ልማትና ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን በፍጥነት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እናበቃለን ብለዋል።

የምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኑርልኝ ብርሃኑ በበኩላቸው፥ ህብረተሰቡ በተባበረ ድምጽ ጽንፈኞች ከጥፋት ተግባራቸው እንዲታቀቡ ያሳየው ቁርጠኝነት ትልቅ አቅም ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል በመተማ ዮሐንስ ከተማ በተካሄደ ሰልፍ የተሳተፉት አቶ ጥላሁን ንጉሴ በበኩላቸው፥በአካባቢው ጸጥታ ችግር ምክንያት ህዝቡ በሰላም ወጥቶ መግባት ቀርቶ የተሻለ ህክምና እንኳ ለማግኘት ተቸግሮ እንደነበር አስታውሰዋል።

መንግስት የጀመረውን የህግ የማስከበር ሥራ እንደሚደግፉ ገልጸው፣ በጫካ ያለው ሃይል የመንግስትን የሰላም ጥሪ እንዲቀበልና ሰላምን እንደምንፈልግ መልዕክት ለማስተላለፋ ሰልፍ መውጣታቸውን ተናግረዋል።

ሌላኛዋ የሰልፉ ተሳታፊ ወይዘሮ ሲሳይነሽ ይርጋ በበኩላቸው፥ ፅንፈኝነት የነገ ሀገር ተረካቢ ህፃናትን ጭምር ሰለባ እያደረገ በመሆኑ ከመንግስት ጎን ሆነው ለመታገል ቁርጠኛ መሆናቸውን ነው የገለጹት።

ጽንፈኝነትን ማውገዝ ብቻ ሳይሆን መታገልም ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ የመተማ ዮሐንስ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሀብቴ አዲሱ ናቸው።

መንግስት ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ልማትን ለማረጋገጥ የጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ህዝቡ ከመንግስት ጎን ሆኖ የሚያደርገውን አስተዋጾ እንዲያጠናክርም አስገንዝበዋል።

በተመሳሳይ በወልዲያ ከተማ በተካሄደ ሰልፍ ላይ የተገኙ ተሳታፊዎች ባለፉት ሁለት ዓመታት ከሰላም እጦት ያተረፉት የሰዎች ሞት፣ እገታ፣ ዝርፊያና ስደትን ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስት ሰላም እንዲጠናከር ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ሀይሎች ወደሰላም እንዲመጡ ያቀረበውን ጥሪ እንደሚደግፉ ገልጸው፣ የጥፋት ሀይሎች ጥሪውን በመቀበል ወደሰላም እንዲመጡ ጠይቀዋል።

የወልድያ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዱባለ አብራሬ በበኩላቸው፥የጽንፈኞች እኩይ ሴራ የልማት ሥራን እንዳያደናቅፍ ጠንክሮ መታገል ይገባል ብለዋል።

የታጠቁ ሃይሎችም የህዝብን ድምጽ በመስማትና በማክበር መንግስት በተደጋጋሚ ያቀረበውን የሰላም አማረጭ ተቀብለው ህዝባቸውን እንዲክሱም ከንቲባው አስገንዝበዋል።

በተለያዩ ከተሞች በተካሄዱ ህዝባዊ ሰልፎች ላይ የተሳተፉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለሰላም ጽኑ ፍላጎት እንዳላቸውና ጽንፈኝነት ሀገርና ህዝብን ስለሚጎዳ ለሰላማቸው ከመንግስት ጎን እንደሚቆሙ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም