የታጠቁ ቡድኖች የህዝብን የሰላም ፍላጎት እንዲያከብሩ እና የመንግስትን የሰላም ጥሪ እንዲቀበሉ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የታጠቁ ቡድኖች የህዝብን የሰላም ፍላጎት እንዲያከብሩ እና የመንግስትን የሰላም ጥሪ እንዲቀበሉ ተጠየቀ

ሰቆጣ ፤ ሰኔ 22/2017(ኢዜአ)፦ የታጠቁ ቡድኖች የህዝብን የሰላም ፍላጎት እንዲያከብሩ እና የመንግስትን የሰላም ጥሪ እንዲቀበሉ የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች በሰላማዊ ሰልፍ ጠየቁ።
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የተለያዩ ከተሞች ሰላምን የሚደግፍና ጽንፈኝነትን የሚያወግዝ ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዷል።
በሰቆጣ ከተማ በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የተገኙት ቄስ መኳንቱ ወርቁ እና አቶ አወል መሃመድ፤ የሰላምን መንገድ በመግፋት በግጭትና ጦርነት የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ህዝቡን ብዙ ዋጋ እያስከፈሉትና ችግር ላይ እየጣሉት መሆኑን አንስተዋል።
ከምንም በላይ በሰላም ወጥተን መግባት፣ ሰርተን መኖርና ልጆቻችንን ማስተማር እንሻለን ያሉት ሰልፈኞቹ የጦርነት ቅስቀሳ የሚያደርግን አካል በፅኑ እንቃወማለን ብለዋል።
የሰላም ጉዳይ የሁላችንም የጋራ አጀንዳ በመሆኑ ሰላምን በማፅናት ግጭትና ጦርነትን በመጥላት ወደ አደባባይ ወጥተናል ሲሉም ተናግረዋል።
በመሆኑም የታጠቁ ቡድኖች የህዝብን የሰላም ፍላጎት እንዲያከብሩና የመንግስትን የሰላም ጥሪ እንዲቀበሉ ሰልፈኞቹ ጠይቀዋል።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ተቀዳሚ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሃይሉ ግርማይ፤ የመንግስት ፍላጎትና ተደጋጋሚ ጥረት ሰላም መሆኑን በማንሳት ለዚህም ተደጋጋሚ ጥሪ መቅረቡን አስታውሰዋል።
በመሆኑም የህዝቡ ጥያቄ ሰላም በመሆኑ ይህንኑ በማክበር የታጠቁ ቡድኖች ሳይውሉ ሳያድሩ እድሉን እንዲጠቀሙበት ጠይቀዋል።
ከዚህ ባለፈ መንግስት ሰላም የማስከበር ሃላፊነት ያለበት መሆኑን አንስተው በተጠናከረና በተቀናጀ መልኩ የሚሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የሰቆጣ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጌትነት እሸቱ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት በከተማው ያለው አስተማማኝ ሰላም የህዝቡ የረዥም ጊዜ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ አስችሏል ብለዋል።
በመሆኑም ታጥቀው ጫካ የገቡ ቡድኖች የህዝቡን እና የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ከጥፋት ወደ ልማት እንዲመለሱ ጠይቀዋል።