ማህበራዊ
ከንቲባ አዳነች አቤቤ የነገዋ የሴቶች የተሀድሶና የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ሰልጣኞች ጋር የትንሳኤ በዓልን አከበሩ
May 5, 2024 68
አዲስ አበባ ፤ ሚያዝያ 27/2016(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከሴቶች የተሀድሶ እና የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ሰልጣኞች ጋር የትንሳኤ በዓልን አክብረዋል፡፡ አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ እና አበባ የማድረግ ስራችን አካል በሆነው የነገዋ የሴቶች የተሀድሶ እና የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ሰልጣኞች ጋር የትንሳኤ በዓልን አብረን አክብረናል ሲሉ ገልጸዋል።   ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የትንሳኤ በዓልን አብረን ለማሳለፍ የጋበዝናቸው እንግዶች በማዕከሉ በስልጠና ላይ ለሚገኙ ለሁሉም እህቶቻችን የስራ እድል በመፍጠር አብረውን ለመስራት ቃል ገብተዋል ብለዋል። ከንቲባዋ በመልዕክታቸውም ልበ ቀና ባለሃብቶችን በሰልጣኝ ሴት እህቶቻችን ስም ላመሰግናቸው እወዳለሁ ብለዋል:: አዲስ አበባችንን ማህበራዊ ፍትህ የነገሰባት የሁሉም ከተማ የማድረግ ስራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉም ገልጸዋል::
በገንዳ ውኃና ደሴ ከተሞች የትንሳኤን በዓል ምክንያት በማድረግ አቅም ለሌላቸው ወገኖች ማዕድ የማጋራት ስነ ስርዓት
May 5, 2024 52
መተማ፤ ደሴ ፤ ሚዚያ 27/2016 (ኢዜአ)፡- በገንዳ ውኃና ደሴ ከተሞች የትንሳኤን በዓል ምክንያት በማድረግ አነሰተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች የማዕድ ማጋራት ስነ-ስርዓት ተከናወነ። በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውሃ ከተማ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለ320 አነስተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች ማዕድ ማጋራታቸው ተገልጿል። የገንዳ ውሃ ከተማ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሂሩት ጌትነት እንዳሉት፤ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ከህብረተሰቡና ከተቋማት ባሰባሰቡት 400 ሺህ ብር የእርድ እንስሳት በመግዛት ማዕድ አጋርተዋል። ማዕድ ካጋሩ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መካከል ወጣት ፈንታሁን አስማረ፤ መደጋገፍን ባህል በማድረጋቸው አቅም የሌላቸውን እየደገፉ መሆኑን ተናግሯል። አቶ መልካሙ መኮንን፤ በወጣቶቹ ተነሳሽነት በተደረገላቸው ማዕድ ማጋራት በዓሉን በደስታ ማዋል እንደቻሉ ገልፀዋል። በተመሳሳይ በደሴ ከተማ የ'አውራምባ ጥምረት በጎ ፍቃደኞች ማህበር' ለትንሳኤ በዓል ለአረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች ማዕድ የማጋራት መርሃ ግብር መከናወኑን የገለፁት የማህበሩ ስራ አስኪያጅ አቶ ምስክር ሰይድ ናቸው። ማህበሩ ከ150 ለሚበልጡ አቅመ ደካሞች የምሳ ግብዣ ማደረጉን ገልጸዋል። ማዕድ ከተጋሩት መካከል ወይዘሮ ፋጤ ሰይድ በበኩላቸው፤ በዓሉን በደስታና በጋራ ከማሳለፋቸውም ባለፈ የአልባሳት ድጋፍ እንደተደረገላቸው አስታውቀዋል።  
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ጤና ሚኒስቴር የትንሳኤ በዓልን በማስመልከት ማዕድ አጋሩ 
May 5, 2024 61
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 27/2016(ኢዜአ)፦ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የጤና ሚኒስቴር የትንሳኤ በዓልን በማስመልከት በሰንሻይን ፊላንትሮፊ ፋውንዴሽን አረጋውያን መጦሪያ ማዕከል ለሚገኙ አቅመ ደካሞችና አረጋውያን ማዕድ አጋርተዋል። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶቹ በማዕከሉ ለሚገኙ አቅመ ደካሞችና አረጋውያን ማዕድ ያጋሩት ከሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጋር በመተባበር ነው። የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፤ የትንሳኤን በዓል ስናከብር አቅመ ደካሞችን በማገዝና በመደገፍ ሊሆን ይገባል ብለዋል።   ኢትዮጵያዊ የመደጋገፍና የመተሳሰብ እሴት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም የበኩሉን ጥረት ማድረግ እንዳለበትም ገልፀዋል። የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፤ በዓሉን ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውንና የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና አብሮ በማሳለፍ ሁላችንም የድርሻችንን አስተዋጽኦ ማድረግ አለበን ብለዋል።   የሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ሳሙኤል ታፈሰ፤ ማዕከሉ በበዓላት ወቅት ለተቸገሩ ወገኖች ማዕድ በማጋራት ተግባር ተሳትፎ እያደረገ እንደሚገኝ ገልፀዋል።   የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ጤና ሚኒስቴር ላደረጉት አስተዋጽኦም ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ማዕከሉ አሁን ላይ ለ700 አረጋውያን አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰው ሌሎችም ተመሳሳይ እገዛና ድጋፍ እንዲያደረግ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።   በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ሰንሻይን ፊላንትሮፊ ፋውንዴሽን ድጋፍ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የተገነባው የአረጋውያን መጠለያና መጦሪያ ማዕከል በመስከረም ወር 2016 ዓ.ም ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑ ይታወቃል። የማዕከሉ ግንባታ የተከናወነው በ30 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ሲሆን ለግንባታው የተደረገውን 630 ሚሊዮን ብር ወጪ የሸፈነው ፋውንዴሽኑ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው የፋሲካ በዓልን ምክንያት በማድረግ ማዕድ አጋሩ
May 5, 2024 65
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 27/2016(ኢዜአ)፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው የፋሲካ በዓልን ምክንያት በማድረግ ማዕድ አጋሩ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ማዕድ ያጋሩት ከአዲስ አበባ የተለያየ አረጋዊያንና አቅመ ደካሞች መርጃ ማእከላት ለመጡ ወገኖች ነው፡፡ በማዕድ ማጋራት መርሃ ግብሩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው አረጋውያን እና አቅመ ደካሞች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያከናወኑት በጎ ተግባር አርአያነት ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡   በበዓል ወቅት እርስ በርስ መደጋገፍ የኢትዮጵያዊያን ነባር እሴት መሆኑን ጠቅሰው፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልካምነትና በጎ ስራዎች በሁሉም ዘንድ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ በማእድ ማጋራቱ ላይ ከተገኙት መካከል አቶ ሙላቱ ዳባ እና ወይዘሮ እታለም እሸቱ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓሉን ከአረጋዊያንና አቅመ ደካማ ወገኖች ጋር ማሳለፋቸው ልዩ የደስታ ስሜት እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡   ይህ በጎ ተግባር ባህል ሆኖ በየአካባቢው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ነው የገለጹት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋዊያንን በመደገፍ ችግራቸው እንዲቃለል እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው፤ አረጋዊያንና አቅመ ደካማ ዜጎች የትንሳኤ በዓልን በደስታ እንዲያሳልፉ በማሰብ ላከናወኑት ማእድ ማጋራትም ምስጋና አቅርበዋል፡፡   ሃምሳ አለቃ ገብረሚካኤል ደብረብርሃን እና አቶ መንግስቱ ተመስገን በበኩላቸው ሁሉም ዜጋ የጠቅላይ ሚኒስትሩን አርአያነት በመከተል በየአካባቢያቸው አረጋዊያንንና አቅመ ደካሞችን ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡   ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፣ የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሠራተኞችና ጽሕፈት ቤቱ ለሚያሳድጋቸው ሕጻናት ማዕድ ማጋራታቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያን የአብሮነት፣ የመደጋገፍና ተካፍሎ የመብላት እሴቶችን ጠብቀን ልንቀጥል ይገባል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ
May 5, 2024 60
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 27/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያን የአብሮነት፣ የመደጋገፍ፣ የፍቅር፣ የመተዛዘንና ተካፍሎ የመብላት እሴቶች ጠብቀን ልንቀጥል ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ። ከንቲባዋ የትንሣኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ዛሬ ማለዳ አብርሆት ቤተ-መጽሐፍት ማዕድ አጋርተዋል።   በዚሁ መርሃ-ግብር ላይ ባስተላለፉት መልዕክትም፤ በዓሉን ስናከብር እርስ በርሳችን በመዋደድ፣ በመረዳዳትና በመደጋገፍ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።   የኢትዮጵያን የአብሮነት፣ የመደጋገፍ፣ የፍቅር፣ የመተዛዘንና ተካፍሎ የመብላት እሴቶች ጠብቀን ልንቀጥል ይገባልም ብለዋል። የአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ውብአየሁ ማሞ፤ የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመተባበር ከ200 ለሚልቁ ሰዎች ማዕድ አጋርተናል ብለዋል።   የማዕድ ማጋራቱ ዓላማም ለወገኖቻችን ያለንን ፍቅር፣ አብሮነትና አጋርነት ለማሳየት ነው ሲሉ ተናግረዋል። በማዕድ ማጋራት ላይ የተገኙትም ለተደረገላቸው ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። የትንሳኤ በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በመላ ኢትዮጵያ በተለያዩ ዝግጅቶች በመከበር ላይ ይገኛል።  
በአዲስ አበባ የትንሳኤ በአል ዋዜማ ምሽት ላይ በእሳት አደጋ የአንድ ሰው ህይወት አለፈ
May 5, 2024 50
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 27/2016(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ የትንሳኤ በአል ዋዜማ ምሽት ላይ በእሳት አደጋ የአንድ ሰው ህይወት ማለፉን የመዲናዋ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ። የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሞያ ንጋቱ ማሞ፤ ለኢዜአ እንደገለጹት በበአል ዋዜማ ምሽት ላይ በእሳት አደጋ የአንድ ሰው ህይወት አልፏል። አደጋው የተከሰተው በቦሌ ክፍለ-ከተማ ወረዳ 12 በተለምዶ ማሪያም ማዞሪያ አካባቢ ሲሆን የአደጋው ምክንያት ደግሞ በጀኔተር ላይ በተነሳ የእሳት አደጋ መሆኑን ተናግረዋል። በዋዜማው ምሽት ሶስት ሰዓት ላይ ነዳጅ ጨምሮ ጄነሬተር ለማስነሳት ሲሞክር የነበረው የ26 አመቱ ጎልማሳ በእሳት አደጋው ወዲያዉ ህይወቱ ማለፉን ገልጸዋል። የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች አደጋውን ለመቆጣጠር በስፋራው ደርሰው በንብረት ላይ የከፋ ጉዳት ሳያስከተል እሳቱን መቆጣጠር መቻላቸውን ተናግረዋል። በመሆኑም ህዝበ ክርስቲያኑ የትንሳኤ በዓልን ሲያከብር ከእሳትና ድንገተኛ አደጋ በመጠንቀቅ ሊሆን እንደሚገባ ባለሙያው መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
የለውጡ መንግስት ከመጣ ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመረው ሰው ተኮር በጎ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል-ዶክተር አለሙ ስሜ
May 5, 2024 57
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 27/2016(ኢዜአ)፦የለውጡ መንግስት ከመጣ ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)የተጀመረው ሰው ተኮር በጎ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል ሲሉ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ ገለጹ፡፡ ሚኒስትሩ የትንሳኤን በዓል አስመልክቶ ከከንቲባ አዳነች አቤቤ ጋር በመሆን ለአቅመ ደካሞች ማዕድ አጋርተዋል።   የ2016 ዓ.ም የትንሣኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 አምስት መቶ ለሚሆኑ አቅመ ደካሞችና በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ወገኖች ነው ማዕድ ያጋሩት። ዶክተር አለሙ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት የለውጡ መንግስት ከመጣ ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተጀመረው ሰው ተኮር በጎ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል፡፡ ሚኒስትሩ ያለው ለሌለው በማካፈል በዓሉን በመተሳሰብ አብሮ በመብላት ማክበር አለብን ብለዋል። እጅ ያጠራቸውን እና ድጋፍ የሚስፈልጋቸውን ወገኖች መረዳትና ማስብ መንፈሳዊ እርካታም ጨምሮ ይሰጣል ብለዋል፡፡ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው ድሆችን አቅመ ደካማዎችን ዝቅ ብሎ መደገፍ እና ማሰብ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል፡፡ በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር በኩል የትንሣኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለተደረገው ድጋፍም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎችና አምባሳደሮች ለትንሳኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
May 5, 2024 63
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 27/2016(ኢዜአ)፡- በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎች እና አምባሳደሮች ለክርስትና እምነት ተከታዮች ለትንሳኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትና የመልካም ምኞት መግለጫ አስተላለፉ። በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን፤ የትንሳኤ በዓል ለተቸገሩ ወገኖች መልካም ነገርን የማድረግ ጅማሮ ነው ብለዋል። ይህም በዜጎች መካከል ሰላም፣ አንድነትና መተባበር እንዲኖር መልካምነት አሸናፊ እንዲሆን የሚያደርግ መሆኑንም ገልጸዋል። በጋራ በመሆን አንድ የሚያደርጉንን መልካም እሴቶች ለበጎ አላማ በማዋል ችግሮችን ማለፍና ደስታና ብልጽግና ላይ መድረስ እንደሚቻል ተናግረዋል። ለኢትዮጵያውያን ጓደኞቼ፣ ወንድሞቼ እና እህቶቼ በዓሉ የጤና፣ የደስታና የልባችሁ መሻት የሚፈጸምበት እንዲሆን እመኛለሁ ብለዋል አምባሳደሩ በመልዕክታቸው። በኢትዮጵያ የጅቡቲ አምባሳደር አብዲ መሐሙድ ኢይቤ፤ ለመላው ኢትዮጵያውያን የክርስትና እምነት ተከታዮች የትንሳኤ በዓል የደስታ፣ የሰላምና የፍቅር እንዲሆን እመኛለሁ ብለዋል።   በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ኪራ ስሚዝ ሲንድበርግ፤ ለመላው ኢትዮጵያውያን የክርስትና እምነት ተከታዮች የትንሳኤ በዓል የሰላምና የደስታ እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን በትዊተር ገጻቸው አስተላልፈዋል።   በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ በዓሉን አስመልክቶ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባስተላለፈው መልዕክት በዓሉ የሰላምና የደስታ እንዲሆን ተመኝቷል። በኢትዮጵያ የእስራኤል ኤምባሲ በበኩሉ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለፋሲካ በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት በዓሉ የሰላምና የፍቅር እንዲሆን መልካም ምኞቱን ገልጿል። በኢትዮጵያ የዩናይትድ ኪንግደም ኤምባሲ የትንሳኤ በዓል ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የደስታ እንዲሆን ተመኝቷል። በኢትዮጵያ የኢራን እስላሚክ ሪፐብሊክ ኤምባሲም “የኢራን እስላሚክ ሪፐብሊክ ኤምባሲ እና ሰራተኞች ለመላው ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች መልካም የስቅለትና የትንሳኤ በዓል እንዲሆንላችሁ ይመኛሉ፤ መልካም ፋሲካ!” ሲል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክቱን አስተላልፏል። የፓኪስታን፣ የአውስትራሊያ፣ የስዊድን፣ የስዊዘርላንድ፣ የስፔን፣ የብሩንዲና ሌሎችም ኢምባሲዎች የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የአፍሪካ ሕብረት ለትንሳኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈ
May 5, 2024 47
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 27/2016(ኢዜአ)፡- የአፍሪካ ሕብረት የትንሳኤ በዓልን በማስመልከት ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል። የሕብረቱ የፖለቲካ ጉዳዮች፣ ሰላምና ደህንነት ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ፤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ለኢትዮጵያዊያን የክርስትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።   የትንሳኤ በዓል አዲስ ተስፋን የሚፈነጥቅ የበረከትና የፍቅር እንዲሆንም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል። ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በዓሉ የሰላም፣ የፍቅርና የደስታ እንዲሆን እመኛለሁ ብለዋል።   የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁም ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለብርሃነ ትንሳኤው አደረሳችሁ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላለፈዋል። በትናንትናው እለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና የሃይማኖት መሪዎች በተመሳሳይ መልእክታቸውን ማስተላለፋቸው ይታወቃል።
የሸዋሊድ ፌስቲቫል በጅግጅጋ ከተማ በደማቅ ሁኔታ ተከበረ
May 4, 2024 88
ጅግጅጋ ፤ሚያዝያ 26/2016 (ኢዜአ) ፦ ''ሸዋሊድ በዩኒስኮ ከዓለም የማይዳስሱ ባህላዊ ቅርሶች መዝገብ ላይ በመካተቱ ባህሉ በሁሉም እንዲታወቅና ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው'' ሲሉ የሶማሌ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ወርሰን አዊል ተናገሩ። ሸዋሊድ በዓለም የማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ ላይ ከሰፈረ በኋላ በሶማሌ ክልል በጅግጅጋ ከተማ በሚገኙ የሐረሪ ክልል ተወላጆች እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት ለመጀመሪያ ጊዜ ከሐረሪ ክልል ውጪ በደማቅ ሁኔታ ዛሬ ተከብሯል። በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙት የሶማሌ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ወርሰን አዊል እንደተናገሩት፤ ሸዋሊድ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ማግኘቱ ባህላዊ ቅርሱ ታውቆና ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ጠቀሜታው የጎላ ነው። በዓሉ በጅግጅጋ ከተማ መከበሩ ለዘመናት የዘለቀውን የሁለቱ ክልሎች ህዝቦች የጋራ ማንነት፣ ታሪክ፣ እምነት እና ባህል ትስስርን ለማጠናከር እንደሚያስችል ተናግረዋል። የሐረሪ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ዚነት ዩሱፍ በበኩላቸው፤ 1445ኛው የሸዋሊድ በዓል ከክልሉ ውጪ በድሬዳዋና በሌሎች ከተሞች በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር መቆየቱን ገልጸዋል ። በዓሉ በምስራቁ የአገራችን ክፍል የሚኖሩ ህዝቦች ያላቸውን አንድነት፣ አብሮነት እና የጋራ እሴት ለማጠናከር የላቀ አስተዋፅኦ እንዳለው አመልክተዋል። በዓሉ በተለያየ ክልሎች እንዲከበር በማድረግ በህዝቦች መካከል ሰላምና በጋራ የመልማት እድሎች ጎልተው እንዲወጡ በቂ ግንዛቤ ለመፍጠር እንደሚሰራም አውስተዋል።   በዓሉን ከታደሙ የሐረሪ ክልል ተወላጆች መካከል አቶ በርከድሌ ሙሜ፤ ለመጀመሪ ጊዜ ሸዋሊድ በሚኖሩበት ጅግጅጋ ከተማ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር መከበሩ የእርስ በእርስ ትውውቁን ያጠናክረዋል ብለዋል። ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ሳኒያ አብዲ በበኩላቸው፤ የሸዋሊድ የእምነት እና የባህል መሰረት ያለው መሆኑን ገልጸው፤ በዓሉን የሐረሪ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችም እንዲያከብሩት መደረጉ የጋራ ማንነትና አንድነትን እንደሚያሳይ ተናግረዋል።    
ለትንሳኤ በአል መዋያ የሚሆኑ የእርድ እንስሳት ለጸጥታ አባላት ተበረከተ
May 4, 2024 159
ጎንደር፤ ሚያዚያ 26/2016 (ኢዜአ)፦በጎንደር ከተማ በሰላም ማስከበር ስራ ለተሰማሩ የፀጥታ አባላት ለትንሳኤ በዓል መዋያ ስጦታ ተበርክቷል። በተመሳሳይም በቤንች ሸኮ ዞን ለሚገኙ የፀጥታ አባላትና ለሚዛን ማረሚያ ተቋም የበዓል መዋያ የእርድ እንስሳት በስጦታ ተበርክቷል። በጎንደር ከተማ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከንቲባው የህዝብ ግንኙነትና አደረጃጀት ዋና አማካሪ አቶ ቻላቸው ዳኘው በርክክቡ ወቅት እንደገለፁት፤ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎችና ባለሀብቶች በከተማው ሰላም ማስከበር ስራ ለተሰማሩ የፀጥታ አባላት የእርድ እንስሳትን በስጦታ አበርክተዋል። ስጦታው በአንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ብር ወጪ የተገዙ የእርድ እንስሳት መሆናቸውንም አቶ ቻላቸው ገልጸዋል። በዓሉን ምክያት በማድረግ የተደረገው ድጋፍ ህዝባዊ ወገንተኝነትን የሚያሳይ ነው ብለዋል። የፌዴራል ፖሊስ ፈጥኖ ደራሽ መምሪያ የሻለቃ ምክትል መሪ ኢንስፔክተር እንድሪስ አብዱልጀሊል በበኩላቸው፤ 'ህዝቡ ለበዓል መዋያ ላደረገው ድጋፍ ክብርና ምስጋና አለን ብለዋል፡፡ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል። በተመሳሳይም በቤንች ሸኮ ዞን ለሚገኙ የፀጥታ አባላትና ለሚዛን ማረሚያ ተቋም የበዓል መዋያ የእርድ እንስሳት በስጦታ ተበርክቷል። የቤንች ሸኮ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍቲን በወቅቱ እንደገለጹት፤ የፀጥታ አካላት ከዞኑ አስተዳደር ጎን በመቆም ለዞኑ ልማትና ዕድገት የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ በመሆኑ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።    
የፖሊስ አመራር እና አባላት መስዋዕትነት ከፍላችሁ ሀገራችንን ያፀናችሁ ጀግኖች በመሆናችሁ ለከፈላችሁት መስዋዕትነት ሀገር ውለታችሁን ትከፍላለች - ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል
May 4, 2024 166
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 26/2016(ኢዜአ)፡- የፖሊስ አመራር እና አባላት መስዋዕትነት ከፍላችሁ ሀገራችንን ያፀናችሁ ጀግኖች በመሆናችሁ ለከፈላችሁት መስዋዕትነት ሀገር ውለታችሁን ትከፍላለች ሲሉ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ተናገሩ፡፡ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የተመራ ከፍተኛ የፖሊስ አመራሮች ቡድን ሀገርን ለማጽናት ከፀረ-ሰላም ኃይሎች ጋር በጀግንነት ሲፋለሙ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በኢትዮጵያ ፖሊስ ሪፈራል ሆስፒታል በህክምና ላይ የሚገኙ እና የልዩ ፀረ ሽብር መምሪያ አመራርና አባላትን ጎብኝቷል፡፡ ኮሚሽነር ጀነራሉ በጉብኝቱ ወቅት የፖሊስ አመራር እና አባላት መስዋዕትነት ከፍላችሁ ሀገራችንን ያፀናችሁ ጀግኖች በመሆናችሁ ለከፈላችሁት መስዋዕትነት ሀገር ውለታችሁን ትክፍላለች ብለዋል፡፡   ለዚህ ተግባራችሁም ልትኮሩ ይገባል ማለታቸውን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል። አያይዘውም አብዛኞቹ ታካሚ የፖሊስ አመራርና አባላት ሆስፒታሉ በሰጣቸው የተሻለ የህክምና አገልግሎት አገግመው ወደ መደበኛ ሥራቸው የሚመለሱ ናቸው ብለዋል፡፡ ጥቂቶቹ ደግሞ የተሻለ የትምህርትና ሌሎች ዕድሎች ተመቻችተውላቸው ተቋሙ እየተከታተለ አስፈላጊውን ሁሉ እያሟላ እንደሚቀጥሉ ኮሚሽነር ጀነራሉ ተናግረዋል።   ጀግኖች የፖሊስ አመራርና አባላት ለሀገር ሰላምና ደኅንነት ለከፈሉት መስዋዕትነት ምስጋና አቅርበው በራሳቸው እና በልዑካን ቡድኑ ስም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈው በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፋም የገንዘብ ስጦታ አበርክተውላቸዋል። በሆስፒታሉ ሆነው ህክምነቸውን በመከታተል እያገገሙ ያሉ የፖሊስ አመራርና አባላትም በልዑካን ቡድኑ በመጎብኘታቸውና የተበረከተላቸው ስጦታ ከፍተኛ ደስታና የመንፈስ እርካታ እንደፈጠረላቸው መግለጻቸውም ተጠቅሷል፡፡ የደረሰብን የአካል ጉዳት የሀገራችንን ሰላምና የሕዝባችንን ደህንነት ለመጠበቅ ስለሆነ በከፈልነው መስዋዕትነት እንኮራለን ማለታቸውም እንዲሁ። በተጨማሪም የልዑካን ቡድኑ አባላት ኮልፌ የሚገኙትን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ልዩ ፀረ ሽብር መምሪያ አመራርና አባላትን በመጎብኘት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ በዓሉን በድምቀት እንዲያከብሩ የእርድ ሰንጋዎችን ማበርከታቸውም በመረጃው ተመላክቷል። በስፔሻል ኮማንዶ ሰልጥነው የተመረቁና በተለያዩ ግዳጆች ላይ በብቃት ጀግንነት የፈፀሙና አሁንም እየፈፀሙ ካሉ የልዩ ፀረ-ሽብር መምሪያ አመራርና አባላት ጋር በነበራቸው ውይይት ኮሚሽነር ጀነራሉ የስራ መመሪያ መስጠታቸውም ተጠቁሟል፡፡ በዚህም ራሳቸውን ከዘር፣ ከሀይማኖት፣ ከፖለቲካና ከሌብነት በመጠበቅ ሀገራቸውንና ህዝባቸውን በፍጹም ታማኝነት እንዲጠብቁ አሳስበዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለትንሳኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
May 4, 2024 144
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 26/2016(ኢዜአ)፡- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለትንሳኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ። የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የእንኳን አደረሳችሁ ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል :- እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ የትንሣኤ በዓል ሞትንና መቃብርን የማሸነፍ በዓል ነው። ሞት ማከናወኛ ሲሆን መቃብር ደግሞ መደምደሚያ ነው። የመቃብር መዘጋት የነገሩን ላይመለስ መጠናቀቅን ያመለክታል። የክርስቶስ መነሣት ተዘግቶ የሚቀር ነገር እንደሌለ አስተምሮናል። ከሞት ወዲያ ሕይወት፣ ከመቃብር ወዲያ ትንሣኤ መኖሩን አሳይቶናል። አይሁድ በመቃብሩ ላይ ድንጋይ ገጥመው ማኅተም ሲያትሙ ነገር ሁሉ አለቀ፤ ተጠናቀቀ ብለው ነበር። ያ ድምዳሜ ግን ሦስት ቀን ብቻ ነው የቆየው። ሞቱ በሕይወት፣ መቃብሩ በትንሣኤ ተሻረ። ለኢትዮጵያም የምናምነው እንደዚሁ ነው። አለቀች፤ ደቀቀች፤ ተጠናቀቀች፤ ሞተች፤ ተቀበረች ያሏትን ሁሉ አሳፍራ እየተነሣች ናት። መግነዟን ፈትታ፣ ሞቷን ድል ነሥታ፣ መቃብሯን ትታ እየተነሣች ነው። በሁሉም ነገሯ እየተነሣች ነው። ከትንሣኤ በኋላ ዳግም ሞት እንደሌለ፤ ኢትዮጵያም ከዚህ በኋላ ከፍ ከፍ ትላለች እንጂ ሞት ዳግም አያገኛትም። መልካም በዓል ይሁን።
የትንሳኤ በዓልን ስናከብር ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላምና ደህንነት በመጸለይና የተቸገሩ ወገኖችን በማገዝ ሊሆን ይገባል -  የሃይማኖት አባቶች 
May 4, 2024 119
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 26/2016 (ኢዜአ)፦የትንሳኤ በዓልን ስናከብር ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላምና ደህንነት በመጸለይና የተቸገሩ ወገኖችን በማገዝ ሊሆን ይገባል ሲሉ የተለያዩ የሃይማኖት አባቶች ተናገሩ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል እና የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስትያን ካውንስል ዋና ጸሃፊ ቄስ ደረጄ ጀምበሩ ለትንሣኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤ በዓለ ትንሳኤ የእግዚአብሄር ፍቅር መገለጫና የተስፋችን ማሳያ መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል ብለዋል። ለእግዚአብሄር ክብርና ለሰው ልጆች ደኀንነት በአንድነት በመቆም መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል። በመሆኑም የትንሳኤን በአል ስናከብር በፍቅር በመተሳሰብና በመተጋገዝ እንዲሁም የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ ሊሆን ይገባል በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላምና ደህንነት በመጸለይና የተቸገሩ ወገኖችን በማገዝ ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት።   የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል፤ በበኩላቸው የትንሣኤ በዓል የክርስቶስን መነሣት ያስተማረን የምሥራች መሆኑን ተናግረዋል። የትንሳኤን በአል ሲከበር የችግሮች ሁሉ መውጫ ቁልፍ ሰላም ብቻ በመሆኑ በትንሣኤው ብርሃን ለአገርና ለህዝብ የሰላም መሣሪያ በመሆንና ለሰላም መፀለይ ሊሆን ይገባል ብለዋል።   የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስትያን ካውንስል ዋና ጸሃፊ ቄስ ደረጄ ጀምበሩ፤ ምዕመኑ የትንሳኤን በአል ሲያከብር እርዳታና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ወገኖች በማገዝ ሊሆን ይገባል ብለዋል። በክርስቶስ ትንሳኤ ሁሉም በፍቅር ልብና በይቅርታ ለሰላምና አብሮነት በመጸለይ በአሉን እንዲያከበር ሲሉ መልክታቸውን አስላለፍዋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም