የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ጤና ሚኒስቴር የትንሳኤ በዓልን በማስመልከት ማዕድ አጋሩ 

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 27/2016(ኢዜአ)፦ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የጤና ሚኒስቴር የትንሳኤ በዓልን በማስመልከት በሰንሻይን ፊላንትሮፊ ፋውንዴሽን አረጋውያን መጦሪያ ማዕከል ለሚገኙ አቅመ ደካሞችና አረጋውያን ማዕድ አጋርተዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶቹ በማዕከሉ ለሚገኙ አቅመ ደካሞችና አረጋውያን ማዕድ ያጋሩት ከሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጋር በመተባበር ነው።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፤ የትንሳኤን በዓል ስናከብር አቅመ ደካሞችን በማገዝና በመደገፍ ሊሆን ይገባል ብለዋል። 


 

ኢትዮጵያዊ የመደጋገፍና የመተሳሰብ እሴት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም የበኩሉን ጥረት ማድረግ እንዳለበትም ገልፀዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፤ በዓሉን ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውንና የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና አብሮ በማሳለፍ ሁላችንም የድርሻችንን አስተዋጽኦ ማድረግ አለበን ብለዋል።


 

የሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ሳሙኤል ታፈሰ፤ ማዕከሉ በበዓላት ወቅት ለተቸገሩ ወገኖች ማዕድ በማጋራት ተግባር ተሳትፎ እያደረገ እንደሚገኝ ገልፀዋል።


 

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ጤና ሚኒስቴር ላደረጉት አስተዋጽኦም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ማዕከሉ አሁን ላይ ለ700 አረጋውያን አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰው ሌሎችም ተመሳሳይ እገዛና ድጋፍ እንዲያደረግ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።


 

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ሰንሻይን ፊላንትሮፊ ፋውንዴሽን ድጋፍ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የተገነባው የአረጋውያን መጠለያና መጦሪያ ማዕከል በመስከረም ወር 2016 ዓ.ም ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑ ይታወቃል።

የማዕከሉ ግንባታ የተከናወነው በ30 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ሲሆን ለግንባታው የተደረገውን 630 ሚሊዮን ብር ወጪ የሸፈነው ፋውንዴሽኑ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም