የፖሊስ አመራር እና አባላት መስዋዕትነት ከፍላችሁ ሀገራችንን ያፀናችሁ ጀግኖች በመሆናችሁ ለከፈላችሁት መስዋዕትነት ሀገር ውለታችሁን ትከፍላለች - ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 26/2016(ኢዜአ)፡- የፖሊስ አመራር እና አባላት መስዋዕትነት ከፍላችሁ ሀገራችንን ያፀናችሁ ጀግኖች በመሆናችሁ ለከፈላችሁት መስዋዕትነት ሀገር ውለታችሁን ትከፍላለች ሲሉ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ተናገሩ፡፡

በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የተመራ ከፍተኛ የፖሊስ አመራሮች ቡድን ሀገርን ለማጽናት ከፀረ-ሰላም ኃይሎች ጋር በጀግንነት ሲፋለሙ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በኢትዮጵያ ፖሊስ ሪፈራል ሆስፒታል በህክምና ላይ የሚገኙ እና የልዩ ፀረ ሽብር መምሪያ አመራርና አባላትን ጎብኝቷል፡፡

ኮሚሽነር ጀነራሉ በጉብኝቱ ወቅት የፖሊስ አመራር እና አባላት መስዋዕትነት ከፍላችሁ ሀገራችንን ያፀናችሁ ጀግኖች በመሆናችሁ ለከፈላችሁት መስዋዕትነት ሀገር ውለታችሁን ትክፍላለች ብለዋል፡፡


 

ለዚህ ተግባራችሁም ልትኮሩ ይገባል ማለታቸውን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

አያይዘውም አብዛኞቹ ታካሚ የፖሊስ አመራርና አባላት ሆስፒታሉ በሰጣቸው የተሻለ የህክምና አገልግሎት አገግመው ወደ መደበኛ ሥራቸው የሚመለሱ ናቸው ብለዋል፡፡

ጥቂቶቹ ደግሞ የተሻለ የትምህርትና ሌሎች ዕድሎች ተመቻችተውላቸው ተቋሙ እየተከታተለ አስፈላጊውን ሁሉ እያሟላ እንደሚቀጥሉ ኮሚሽነር ጀነራሉ ተናግረዋል።


 

ጀግኖች የፖሊስ አመራርና አባላት ለሀገር ሰላምና ደኅንነት ለከፈሉት መስዋዕትነት ምስጋና አቅርበው በራሳቸው እና በልዑካን ቡድኑ ስም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈው በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፋም የገንዘብ ስጦታ አበርክተውላቸዋል።

በሆስፒታሉ ሆነው ህክምነቸውን በመከታተል እያገገሙ ያሉ የፖሊስ አመራርና አባላትም በልዑካን ቡድኑ በመጎብኘታቸውና የተበረከተላቸው ስጦታ ከፍተኛ ደስታና የመንፈስ እርካታ እንደፈጠረላቸው መግለጻቸውም ተጠቅሷል፡፡

የደረሰብን የአካል ጉዳት የሀገራችንን ሰላምና የሕዝባችንን ደህንነት ለመጠበቅ ስለሆነ በከፈልነው መስዋዕትነት እንኮራለን ማለታቸውም እንዲሁ።

በተጨማሪም የልዑካን ቡድኑ አባላት ኮልፌ የሚገኙትን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ልዩ ፀረ ሽብር መምሪያ አመራርና አባላትን በመጎብኘት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በዓሉን በድምቀት እንዲያከብሩ የእርድ ሰንጋዎችን ማበርከታቸውም በመረጃው ተመላክቷል።

በስፔሻል ኮማንዶ ሰልጥነው የተመረቁና በተለያዩ ግዳጆች ላይ በብቃት ጀግንነት የፈፀሙና አሁንም እየፈፀሙ ካሉ የልዩ ፀረ-ሽብር መምሪያ አመራርና አባላት ጋር በነበራቸው ውይይት ኮሚሽነር ጀነራሉ የስራ መመሪያ መስጠታቸውም ተጠቁሟል፡፡

በዚህም ራሳቸውን ከዘር፣ ከሀይማኖት፣ ከፖለቲካና ከሌብነት በመጠበቅ ሀገራቸውንና ህዝባቸውን በፍጹም ታማኝነት እንዲጠብቁ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም