የትንሳኤ በዓልን ስናከብር ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላምና ደህንነት በመጸለይና የተቸገሩ ወገኖችን በማገዝ ሊሆን ይገባል - የሃይማኖት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
የትንሳኤ በዓልን ስናከብር ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላምና ደህንነት በመጸለይና የተቸገሩ ወገኖችን በማገዝ ሊሆን ይገባል - የሃይማኖት አባቶች
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 26/2016 (ኢዜአ)፦የትንሳኤ በዓልን ስናከብር ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላምና ደህንነት በመጸለይና የተቸገሩ ወገኖችን በማገዝ ሊሆን ይገባል ሲሉ የተለያዩ የሃይማኖት አባቶች ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል እና የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስትያን ካውንስል ዋና ጸሃፊ ቄስ ደረጄ ጀምበሩ ለትንሣኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤ በዓለ ትንሳኤ የእግዚአብሄር ፍቅር መገለጫና የተስፋችን ማሳያ መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል ብለዋል።
ለእግዚአብሄር ክብርና ለሰው ልጆች ደኀንነት በአንድነት በመቆም መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
በመሆኑም የትንሳኤን በአል ስናከብር በፍቅር በመተሳሰብና በመተጋገዝ እንዲሁም የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ ሊሆን ይገባል በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላምና ደህንነት በመጸለይና የተቸገሩ ወገኖችን በማገዝ ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል፤ በበኩላቸው የትንሣኤ በዓል የክርስቶስን መነሣት ያስተማረን የምሥራች መሆኑን ተናግረዋል።
የትንሳኤን በአል ሲከበር የችግሮች ሁሉ መውጫ ቁልፍ ሰላም ብቻ በመሆኑ በትንሣኤው ብርሃን ለአገርና ለህዝብ የሰላም መሣሪያ በመሆንና ለሰላም መፀለይ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስትያን ካውንስል ዋና ጸሃፊ ቄስ ደረጄ ጀምበሩ፤ ምዕመኑ የትንሳኤን በአል ሲያከብር እርዳታና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ወገኖች በማገዝ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
በክርስቶስ ትንሳኤ ሁሉም በፍቅር ልብና በይቅርታ ለሰላምና አብሮነት በመጸለይ በአሉን እንዲያከበር ሲሉ መልክታቸውን አስላለፍዋል።