ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው የፋሲካ በዓልን ምክንያት በማድረግ ማዕድ አጋሩ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 27/2016(ኢዜአ)፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው የፋሲካ በዓልን ምክንያት በማድረግ ማዕድ አጋሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ማዕድ ያጋሩት ከአዲስ አበባ የተለያየ አረጋዊያንና አቅመ ደካሞች መርጃ ማእከላት ለመጡ ወገኖች ነው፡፡

በማዕድ ማጋራት መርሃ ግብሩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው አረጋውያን እና አቅመ ደካሞች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያከናወኑት በጎ ተግባር አርአያነት ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

በበዓል ወቅት እርስ በርስ መደጋገፍ የኢትዮጵያዊያን ነባር እሴት መሆኑን ጠቅሰው፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልካምነትና በጎ ስራዎች በሁሉም ዘንድ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በማእድ ማጋራቱ ላይ ከተገኙት መካከል አቶ ሙላቱ ዳባ እና ወይዘሮ እታለም እሸቱ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓሉን ከአረጋዊያንና አቅመ ደካማ ወገኖች ጋር ማሳለፋቸው ልዩ የደስታ ስሜት እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡


 

ይህ በጎ ተግባር ባህል ሆኖ በየአካባቢው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ነው የገለጹት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋዊያንን በመደገፍ ችግራቸው እንዲቃለል እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው፤ አረጋዊያንና አቅመ ደካማ ዜጎች የትንሳኤ በዓልን በደስታ እንዲያሳልፉ በማሰብ ላከናወኑት ማእድ ማጋራትም ምስጋና አቅርበዋል፡፡


 

ሃምሳ አለቃ ገብረሚካኤል ደብረብርሃን እና አቶ መንግስቱ ተመስገን በበኩላቸው ሁሉም ዜጋ የጠቅላይ ሚኒስትሩን አርአያነት በመከተል በየአካባቢያቸው አረጋዊያንንና አቅመ ደካሞችን ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፣ የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሠራተኞችና ጽሕፈት ቤቱ ለሚያሳድጋቸው ሕጻናት ማዕድ ማጋራታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም