የሸዋሊድ ፌስቲቫል በጅግጅጋ ከተማ በደማቅ ሁኔታ ተከበረ

ጅግጅጋ ፤ሚያዝያ 26/2016 (ኢዜአ) ፦ ''ሸዋሊድ በዩኒስኮ ከዓለም የማይዳስሱ ባህላዊ ቅርሶች መዝገብ ላይ በመካተቱ ባህሉ በሁሉም እንዲታወቅና ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ከፍተኛ ጠቀሜታ  አለው'' ሲሉ የሶማሌ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ወርሰን አዊል ተናገሩ። 

ሸዋሊድ በዓለም የማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ ላይ ከሰፈረ በኋላ በሶማሌ ክልል በጅግጅጋ ከተማ በሚገኙ የሐረሪ ክልል ተወላጆች እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት ለመጀመሪያ ጊዜ ከሐረሪ ክልል ውጪ በደማቅ ሁኔታ ዛሬ ተከብሯል። 

በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙት የሶማሌ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ወርሰን አዊል እንደተናገሩት፤ ሸዋሊድ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ማግኘቱ ባህላዊ ቅርሱ ታውቆና ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ጠቀሜታው የጎላ ነው። 

በዓሉ በጅግጅጋ ከተማ መከበሩ ለዘመናት የዘለቀውን የሁለቱ ክልሎች ህዝቦች የጋራ ማንነት፣ ታሪክ፣ እምነት እና ባህል ትስስርን ለማጠናከር እንደሚያስችል ተናግረዋል። 

የሐረሪ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ዚነት ዩሱፍ በበኩላቸው፤ 1445ኛው የሸዋሊድ በዓል ከክልሉ ውጪ በድሬዳዋና በሌሎች ከተሞች በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር መቆየቱን ገልጸዋል ። 

በዓሉ በምስራቁ የአገራችን ክፍል የሚኖሩ ህዝቦች ያላቸውን አንድነት፣ አብሮነት እና የጋራ እሴት ለማጠናከር የላቀ አስተዋፅኦ እንዳለው አመልክተዋል። 

በዓሉ በተለያየ ክልሎች እንዲከበር በማድረግ በህዝቦች መካከል ሰላምና በጋራ የመልማት እድሎች ጎልተው እንዲወጡ በቂ ግንዛቤ ለመፍጠር እንደሚሰራም አውስተዋል። 


 

በዓሉን ከታደሙ የሐረሪ ክልል ተወላጆች መካከል አቶ በርከድሌ ሙሜ፤ ለመጀመሪ ጊዜ ሸዋሊድ በሚኖሩበት ጅግጅጋ ከተማ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር መከበሩ የእርስ በእርስ ትውውቁን ያጠናክረዋል ብለዋል። 

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ሳኒያ አብዲ በበኩላቸው፤ የሸዋሊድ የእምነት እና የባህል መሰረት ያለው መሆኑን ገልጸው፤ በዓሉን የሐረሪ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችም እንዲያከብሩት መደረጉ የጋራ ማንነትና አንድነትን እንደሚያሳይ ተናግረዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም