የኢጋድ የ40 ዓመታት ጉዞ፤ ከድርቅ አደጋ ምላሽ ሰጪነት እስከ ቀጣናዊ ትስስር ተዋናይነት - ኢዜአ አማርኛ
የኢጋድ የ40 ዓመታት ጉዞ፤ ከድርቅ አደጋ ምላሽ ሰጪነት እስከ ቀጣናዊ ትስስር ተዋናይነት
በሙሴ መለሰ
ምስራቅ አፍሪካ በአፍሪካ አህጉር በየጊዜው ከፍተኛ ለውጥ የሚያስተናግድ እና ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያለው ቀጣና ነው። ከ300 ሚሊየን በላይ ህዝብ የሚኖርበት ይህ ቀጣና ከፍተኛ የሰው ሀብት ያለው ሲሆን ፈጣን የወጣት ህዝብ እድገት እና የገበያ ተደራሽነት መስፋት እየታየበት ይገኛል።
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) የምስራቅ አፍሪካ አጠቃላይ ዓመታዊ ጥቅል ምርት(ጂዲፒ) እ.አ.አ በ2025 598 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር መድረሱን ገልጿል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገቡ ያሉ ሀገራት የሚገኙበት ቀጣና ነው ምስራቅ አፍሪካ። ምስራቅ አፍሪካ ግብርና፣ ቁም እንስሳት፣ ኢነርጂ፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ንግድ፣ ትራንስፖርት፣ የኢኮኖሚ ኮሪደሮች እና በፍጥነት እያደገ የመጣው ዲጂታል ኢኮኖሚ እምቅ የኢኮኖሚ አቅሞቿ ናቸው።
ከመልክዐ ምድራዊ አቀማመጥ አንጻርም የኢትዮጵያ ከፍታማ ስፍራዎች፣ የታላላቅ ሀይቆች ተፋሰስ እና የአፍሪካ ቀንድ ዝቅተኛ ቦታዎች ይጠቀሳሉ። ከቀይ ባህር እስከ ህንድ ውቅያኖስ ምስራቅ አፍሪካን የአፍሪካ፣ መካከለኛው ምስራቅ እና የዓለም የማሪታይም ንግድ መተላለፊያ መስመሮች ይገናኙባታል።
ይህ ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ ምስራቅ አፍሪካ በዓለም አቀፍ ንግድ፣ ሎጂስቲክስ እና ጂኦ ፖለቲካ ውስጥ ያላትን ሚና አሳድጓል። ቀጣናው ለመረጋገት እና ለትብብር ያለው ጠቀሜታም በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
ለብዙ ክፍለ ዘመናት በምስራቅ አፍሪካ የሚገኙ የተለያዩ ማህበረሰቦች በንግድ፣ በፍልሰት እና የባህል ትስስር ተጋምደዋል። በዘመናዊው ዓለም ይህ ታሪካዊ ትስስር ለቀጣናዊ ትስስር ጠንካራ አስተዋጽኦ ያለው ነው። በሀገራት በጋራ የሚገነቡ መሰረተ ልማቶች፣ የተሳናሰኑ ፖሊሲዎች እና የሰዎችና እቃዎች ነጻ ዝውውር የኢኮኖሚ እድገት እና አጠቃላይ ልማትን የሚያሳልጥ ነው።
ቀጣናዊ ትስስር የተበታተነ ገበያ ወደ አንድ ማዕቀፍ ለማምጣት፣ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግና በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ዜጎች በተለይም ወጣቶች የስራ እድል ከመፍጠር አኳያ አስተዋጽኦወ ቁልፍ ነው።
ምስራቅ አፍሪካ እንደ እድሎቹ ሁሉ በርካታ ፈተናዎች ያሉበት ቀጣና ነው። በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚፈጠረው ድርቅ እና ጎርፍ፣ ግጭት፣ መፈናቀል እና የልማት ተደራሽነት ፍትሃዊ አለመሆን በዋናነት የሚነሱ ጉዳዮች ናቸው። እነዚህ ድንበር ተሻጋሪ ፈተናዎች ከተናጠል ይልቅ የጋራ የተግባር ምላሽ ይፈልጋሉ።
ፈተናዎችን ከግምት በማስገባት በቀጣናው በተደጋጋሚ ለሚከሰተው ድርቅ እና የከባቢ አየር ችግር የተቀናጀ ምላሽ መስጠት የሚያስችለው ተቋማዊ ማዕቀፍ ከ40 ዓመታት በፊት ወደ ስራ ገባ። ይህ ተቋም የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) ነው።
የኢጋድ መቋቋም እርሾ በወቅቱ በቀጣናው ያጋጥሙ የነበሩ ቀውሶች ናቸው። እ.አ.አ በ1980ዎቹ መጀመሪያ በቀጣናው የነበረው ድርቅ እና ረሃብ የብዙ ዜጎችን ህይወት የቀጠፈ ሲሆን ይህም ቀጣናው ለአየር ንብረት ለውጥ ያለውን ተጋላጭነት በግልጽ የሚያሳይ ነው። አደጋዎቹ ድንበር ተሻጋሪ በመሆናቸው የተቀናጀ የጋራ ምላሽ የሚፈልጉ ናቸው።
ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን እና ዩጋንዳ ለአንገብጋቢው ቀጣናዊ ጉዳይ ምላሽ በመስጠት ኢጋድን እ.አ.አ በ1986 አቋቋሙ። ኢጋድ በወቅቱ ሲቋቋም ዋነኛ የስራ ድርሻው የነበረው ድርቅ፣ በረሃማነት እና ሁለቱ የሚያደርሷቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖዎችን ለመከላከል የሚደረጉ ቀጣናዊ ጥረቶችን ማስተባበር ነው።
ይሁንና የከባቢ አየር ፈተናዎቹ ከፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ግጭት እና ካለመልማት ጋር ጥልቅ ቁርኝት ያላቸው መሆኑ አድማሱ የሰፋ ግብ ያለው ቀጣናዊ ተቋምን መፍጠር እንደሚያስፈልግ በወቅቱ ይነሳ ነበር። በዚሁ መሰረት ኢጋድ እ.አ.አ በ1996 በድጋሚ አደረጃጀቱ ተስተካክሎና የስራ ድርሻው ሰፍቶ እንደገና ተቋቋመ።
ከድርቅ እና ከባቢ አየር ጉዳዮች በመሻገር ኢጋድ ሰላም እና ደህንነትን ማረጋገጥ፣ የኢኮኖሚ ትብብር እና ትስስር እንዲሁም ቀጣናዊ ትስስርን ማጎልበት የተቋሙ ቁልፍ የትኩረት መስኮች ሆነዋል። የኢጋድ ዋና መቀመጫ ጅቡቲ ነው። የሰፋው የስራ ድርሻ ኢጋድን በአፍሪካ ቀንድ የምክክር፣ የውይይት እና የተቀናጀ ልማት የጋራ ማዕቀፍ እንዲሆን አድርጎታል።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) እ.አ.አ በ2026 የተመሰረተበትን 40ኛ ዓመት እንደሚያከብር ከሰሞኑ አስታውቋል። ኢጋድ በአራት አስርት ዓመታት ውስጥ በስኬት ደረጃ ሊነሱ የሚችሉ ተግባራትን አከናውኗል።
ከሰላም እና ደህንነት አንጻር ኢጋድ በቀጣናው ውስብስብ የሚባሉ ግጭቶች በእርቅ እና በውይይት እንዲፈቱ አስተዋጽኦ አድርጓል። ለዓመታት በሱዳን ሲካሄድ የነበረውን የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲያበቃ እ.አ.አ በ2005 ሁሉን አቀፍ የሰላም ስምምነት እንዲፈረም በሰላም ሂደት ውስጥ የድርሻውን ተወጥቷል። ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ደቡብ ሱዳን በህዝበ ውሳኔ ራሷን የቻለች ሀገር ሆናለች።
ኢጋድ በሶማሊያ የሰላም ጥረቶች ቁልፍ ተዋናይ ነበር። በሶማሊያ የፖለቲካ እርቅ እና መረጋጋት እንዲፈጠር ሲከናወኑ በነበሩ ስራዎች ላይ ተሳትፎ አድርጓል። ቀጣናዊ ተቋሙ ባለው የእርቅ የስራ ክፍል ግጭቶች እንዳይከሰቱና ከተከሰቱም እንዲፈቱ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣም ይገኛል።
ከተቋቋመበት የስራ ድርሻ አኳያ ኢጋድ በምግብ ደህንነት፣ በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል እና አደጋ ስጋት አስተዳደር ላይ ሰፋፊ ተግባራትን አከናውኗል። ለአብነትም የኢጋድ የአየር ንብረት ትንበያና ትግበራ ማዕከል (ICPAC) የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓቶችን በማጠናከር፣ በአየር ትንበያዎች እና የፖሊሲ ድጋፎች አማካኝነት አባል ሀገራት ለድርቅ እና ጎርፍ አደጋዎች ምላሽ እንዲሰጡ የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል። ይህም ቀጣናዊ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽን ለማጠናከርና የመንግስታትን አቅም ከመገንባት አኳያ ትልቅ ድርሻ እንደተወጣ ማዕከሉ ይገልጻል።
ከኢኮኖሚ ትብብር እና ቀጣናዊ ትስስር አኳያም ኢጋድ ድንበር ተሻጋሪ ንግድ እንዲያድግ፣ መሰረተ ልማት እንዲስፋፋና ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንዲጠናከሩ የሚያስችሉ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል። በትራንስፖርት ኮሪደሮች፣ በአርብቶ አደሮች እንቅስቃሴዎችና ቀጣናዊ ገበያዎች ላይ ኢኒሼቲቮችን በመቅረጽ በአባል ሀገራት እንዲተገበር ከማድረግ ባለፈ ድጋፉን እየሰጠ ነው። ኢጋድ በቀጣናው ለንግድ እና ለእንቅስቃሴ የሆኑ መሰናክሎች እንዲቀንሱ አስተዋጽኦ አድርጓል።
ኢጋድ ከፍልሰተኞች ና ተፈናቃዮች ጋር ያሉ ችግሮች እንዲፈቱና ጉዳዩ ከፈተና ባለፈ የልማት እድል እንደሆነ በማንሳት ሁሉን አቀፍ እይታ እንዲፈጠር እየሰራ ይገኛል።
በአራት አስርት ዓመታት ውስጥ ኢጋድ ተቋማዊ አቅሙን በማጠናከርና አጋርነቱን በማስፋት ረገድ የተለያዩ ስራዎችን አከናውኗል። ኢጋድ ከአፍሪካ ህብረት፣ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ከሌሎች ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር እየሰራ ነው። ተቋሙ በቴክኒካዊ እና ፖለቲካዊ ደረጃዎች ለአባል ሀገራት ቋሚ የምክክር ማዕቀፍ ሆኖ እያገለገለ ሲሆን ይህም በሀገራት መካከል የጋራ መተማመንና የጋራ መግባባት እንዲኖር ያለው አስተዋጽኦ ወሳኝ የሚባል ነው።
የኢጋድ የ40 ዓመታት ጉዞ በስኬቶች ብቻ የታጀበ አይደለም። ቀጣናዊ ተቋሙ ከፍተኛ ፈተናዎችም አጋጥመውታል። የመጀመሪያው በተደጋጋሚ ጊዜ የሚቀሰቀሱ እና ዘላቂ መቋጫ ያላገኙ ግጭቶችና የፖለቲካ አለመረጋጋቶች ናቸው። ጉዳዮቹ የኢጋድን የእርቀ ሰላም ጥረቶች ፈተና ውስጥ ከተውታል። አንዳንድ ጊዜ በአባል ሀገራት መካከል ያሉ መከፋፈሎች ኢጋድ ቆራጥ ውሳኔ እንዳይወስን ሲገድበው ታይቷል።
የፋይናንስና ተቋማዊ አቅም ውስነነቶች የኢጋድ የተለያዩ ማዕቀፎች ትግበራ ላይ መስተጓጎሎችን ፈጥረዋል። ኢጋድ ከውጭ አጋሮች የሚያገኘው ፈንድ ከራስ ዘላቂ የፋይናንስ አቅርቦት ጋር ማመጣጠን አለመቻል የተቋሙን የዘላቂነት እና የባለቤትነት ጉዳይ ላይ ተጽእኖ አሳድረዋል። የፖለቲካ ተንታኞች ተቋሙ ከአባል ሀገራቱ የሚያገኝውን ጨምሮ ገቢ እና የፋይናንስ ቅሙን የሚያጠናክርባቸውን መንገዶች በሚገባ ማየት እንዳለበት ይመክራሉ።
የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ ሌላኛው የኢጋድ ፈተና ነው። በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ደጋግመው የሚከሰቱ ድርቆች እና የጎርፍ አደጋዎች በተቋማዊ ምላሽና አቅም ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድረዋል። ፈጣን የህዝብ እድገት፣ የከተሜነት መስፋፋትና መፈናቀል ጫናዎቹ ይበልጥ እንዲበረቱ አድርገዋል።
ቀጣናዊ ስምምነቶችና የአሰራር ማዕቀፎችን ወደ ተጨባጭ የሀገራት ትግበራ የማሸጋገር ጉዳይም ትኩረት እንደሚያሻውም ይነሳል። የሀገራት የሚለያዩ የትኩረት መስኮች እና አቅሞች በቀጣናዊ ማዕቀፎች ሂደትና ትግበራ ላይ የራሳቸውን ተጽእኖ ያሳድራሉ።
40 ዓመታትን ያስቆጠረው ኢጋድ በምስራቅ አፍሪካ እና የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ ትብብር ያለውን ወሳኝ ጠቀሜታ የሚያሳይ ህያው ተቋማዊ ምስክር ነው። ለድርቅ እና ረሃብ ምላሽ ከመስጠት በቀጣናዊ ሰላም፣ ደህንነት፣ አንድነት እና ልማት ቁልፍ ተዋናይነት ተሸጋግሯል።
አንድነት እና የፖለቲካ ቁርጠኝነትን በኢጋድ አባል ሀገራት መካከል ማጠናከር ለቀጣናዊ የተግባር ምላሽና ለተቋሙ ዘላቂ ውጤታማነት ወሳኝ የሚባሉ ጉዳዮች ናቸው። የአባል ሀገራት የጋራ አንድነት የተረጋገጠበት ኢጋድ ለቀውሶች ምላሽ ከመስጠት ባለፈ ለጋራ ፍላጎቶች መሳካት ያለው ሚናም ያድጋል።
ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አቅም ግንባታና ዘላቂ ልማት ላይ ቀጣይነት ባለው መልኩ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ የኢጋድ የትኩረት አጀንዳ ሊሆን ይገባል።
የኢጋድ የሰላም እና መረጋጋት ጥረቶች በሁሉን አቀፍ አስተዳደር፣ በወጣቶችና ሴቶች የነቃ ተሳትፎ እንዲሁም በዘላቂ የሀገር ግንባታ አካሄዶች ሊደገፍ እንደሚገባ የፖለቲካ ባለሙያዎች ምክረ ሀሳባችውን ያስቀምጣሉ። የልማት ፍላጎት አለመሟላት እና የኑሮ ውድነትን ለግጭቶች አበይት መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን ከስር መሰረቱ መፍታት ለዘላቂ መረጋጋት ወሳኝ ነው።
ኢጋድ የተጣለበትን ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስር እውን የማድረግ ኃላፊነቱን የበለጠ ለመወጣት የመሰረተ ልማት ትስስሮች ማጠናከር፣ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እውን ማድረግና በቀጣናው በፍጥነት እያደገ ለመጣው ዜጋ የስራ ፈጠራና እድሎችን የሚያሰፉ ቀጣናዊ የእሴት ሰንሰለቶችን የማስፋት ስራ ላይ አበክሮ መስራት ይኖርበታል።
ፈተናዎች እንዳሉ ሆነው የኢጋድ የ40 ዓመታት ጉዞ የሚያሳየው አንድ ግልጽ ሀቅ አለ። ይህም እውነታ የምስራቅ አፍሪካ መጻኢ ጊዜ እርስ በእርስ መተሳሰርና በትብብር መቆም እንደሆነ ነው።
የተቋቋመበትን አላማ ዳግም ቃል ኪዳኑን በማደስ በቁርጠኝነት መስራት ከቻለ፣ ተቋማዊ አቅሙን በሚገባ ካጎለበተ፣ በሀገራት መካከል አጋርነትና ትብብርን ካጠናከረና የዲጂታል ዘመን በሚገባ በመዋጀት ከሰራ ኢጋድ ቀጣዩ ትውልድ ሰላማዊ፣ አይበገሬናና የበለጸገ ቀጣና እንዲረከብ በማድረግ ረገድ ቁልፍ ሚና መጫወቱን መቀጠል ይችላል።