ቀጥታ፡

በኒጀር በደረሰ ጥቃት መጠነኛ ጉዳት የደረሰባቸው የአስካይ አየር መንገድ አውሮፕላኖች ተጠግነው በቅርቡ አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ

አዲስ አበባ፤ ጥር 26/2018(ኢዜአ)፦ በኒጀር ዋና ከተማ በደረሰ ጥቃት መጠነኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሁለት የአስካይ አየር መንገድ አውሮፕላኖች ተጠግነው በቅርቡ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታወቀ ፡፡

አየር መንገዱ ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጠው ማብራሪያ ባለፈው ሐሙስ ጥር 21/ 2018 ዓ.ም ሌሊት በኒጀር ዋና ከተማ ኒያሚ አውሮፕላን ማረፊያ በደረሰው ጥቃት ሁለት የአስካይ አየር መንገድ ቦይንግ 737 አውሮፕላኖች መጠነኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል ፡፡

አውሮፕላኖቹ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አጋር የሆነው የአስካይ አየር መንገድ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አማካኝነት ከአውሮፕላን አከራዮች የተከራያቸው እና በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የተመዘገቡ መሆናቸውን አስረድቷል፡፡

በአውሮፕላኖቹ ላይ የደረሰውን ጉዳት ለመገምገም የተላከው የቴክኒክ ቡድን ጉዳቱ መጠነኛ መሆኑን ያረጋገጠ ሲሆን አውሮፕላኖቹ ተጠግነው በቅርቡ ወደ አገልግሎት እንደሚገቡም ተገልጿል ::

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም