በኤርትራ መንግሥት እየደረሰብን ላለው መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብቶችና የዘር ማጥፋት ወንጀል ላቀረብነው ክስ ምላሽ እየተጠባበቀን ነው - የቀይ ባሕር አፋር ዲሞክራሲያዊ ድርጅት - ኢዜአ አማርኛ
በኤርትራ መንግሥት እየደረሰብን ላለው መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብቶችና የዘር ማጥፋት ወንጀል ላቀረብነው ክስ ምላሽ እየተጠባበቀን ነው - የቀይ ባሕር አፋር ዲሞክራሲያዊ ድርጅት
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 15/2018(ኢዜአ)፦ በኤርትራ መንግሥት እየደረሰብን ላለው መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብቶችና የዘር ማጥፋት ወንጀል በተመለከተ ለአፍሪካ የሰብዓዊ እና የሕዝቦች መብቶች ኮሚሽን ላቀረብነው ክስ ምላሽ እየተጠባበቅን ነው ሲል የቀይ ባሕር አፋር ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ገለጸ።
የቀይ ባሕር አፋር ዴሞክራሲያዊ ድርጅት በኤርትራ መንግሥት አገዛዝ ደረሰብን ያለውን መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እና የዘር ማጥፋት ዘመቻ አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
ጋምቢያ(ባንጁል) የአፍሪካ የሰብዓዊ እና የሕዝቦች መብቶች ኮሚሽን የቀይ ባሕር አፋር ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ላቀረበው ክስ የኤርትራ መንግስት ምላሽ እንዲሰጥ ክሱን መላኩን አድንቋል።
በኤርትራ መንግስት ላይ የቀረቡትን ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ክስ ተቀብሎ በመዝገብ ቁጥር 868/25 መመዝገቡን፣ የክሱ ፍሬ ነገር እና ይዘት ተቀባይነት ያለው መሆኑን እውቅና በመስጠት የኤርትራ መንግስት እንዲመልስ ክሱን መላኩን ኮሚሽኑ ማስታወቁን ገልጿል።
የድርጅቱ ሊቀ-መንበር ኢብራሂም ሀሩን በመግለጫቸው እንደተናገሩት፤ የኤርትራው መንግሥት በደናክል አካባቢ በቀይ ባህር አፋር ህዝቦች እየፈፀመ ያለው መጠነ ሰፊ፣ ስልታዊ፣ መንግስታዊ መር እና ቀጣይነት ያለው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና የዘር ማጥፋት ወንጀል ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ መጥቷል።
በአሁኑ ወቅት እየደረሱ ነው ካሏቸው የመብት ጥሰቶች መካከልም ከህግ እና ከፍርድ ውጭ ግድያዎች እና ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ማካሄድ፣ ያለ ፍርድ ማሰር እና ማሰቃየት፣ በሺዎች የሚቆጠሩትን መሰወር፣ የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ ማከናወን መሆናቸውን ለአብነት ጠቅሰው፤ በተለይም ከ300ሺህ በላይ የቀይ ባህር አፋር ህዝብን ማፈናቀል እና ፆታዊ ጥቃትን የአገዛዙ የአፈና መሳሪያ አድርጎ መጠቀሙን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ከሀገሪቱ ፖለቲካዊ አስተዳደር ማግለል፣ የቀይ ባህር አፋር ህዝብን ማንነትና ባህል ማጥፋትና ኢኮኖሚያዊ መብቶችን መጣስ ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዚህም ድርጅቱ የአፍሪካ የሰብዓዊ እና የህዝቦች መብቶች ኮሚሽን ከ1993 ጀምሮ በኤርትራ መንግሥት እየደረሰባቸው ያለውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ክስ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።
እኤአ ጁን 04 ቀን 2025 በ122 ገጽ የተደራጀ ክስ ማስገባታቸውን ጠቁመው፤ ኮሚሽኑ የኤርትራ መንግስት በ60 ቀናት ውስጥ ምላሽ እንዲሰጥ ክሱን መላኩን እንደገለጸላቸው ጠቁመዋል።
ለክሱም ከተጠቀሙት ማስረጃዎች መካከል በድርጅቱ የተከናወነ የሰብዓዊ መብት ምርመራ ግኝት፣ በተባበሩት መንግስታት እና በአፍሪካ የሰብዓዊና ሕዝባዊ መብቶች በኤርትራ ላይ የተደረጉ ምርመራዎች፣ ግኝቶችና ማስረጃዎች፣ የመብት ጥሰት የደረሰባቸው የቀይ ባሕር አፋር ተጎጂ ወገኖች እንዲሁም በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች የተገኙ የሰብዓዊ መብት ምርመራዎችን መቅረቡን ተናግረዋል።
ድርጅቱ የአፋር ህዝብ ከሚደርስበት መከራ ለማዳን፣ የዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ድምፅ እንዲሆኑት፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ተቋማት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረት ትኩረት እንዲሰጡንና የኢሳያስ መንግስት ላይ ህጋዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ሰብዓዊ እና ፖለቲካዊ እርምጃ እንዲወስዱ እንዲሁም ተፅዕኖ እንዲያሳድሩ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።