ቀጥታ፡

የአፍሪካ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አዲስ አበባ እየገቡ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 4/2018(ኢዜአ) የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች 48ኛው የአፍሪካ ህብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ እና 39ኛው የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ እየገቡ ይገኛሉ።


 

ዛሬ ንጋት አዲስ አበባ ከገቡት መካከል የጋና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሙኤል ኦኩድዘቶ አብላካዋ፣ የሲሸልስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባሪ ፏር፣ የሴኔጋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቸኪህ ናንግ እና የደቡብ ሱዳን ውጭ ጉዳይ እና አለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር አምባሳደር ሞንደየሰ ሳሚያ ኩምቢያ ይገኙበታል።


 

በተጨማሪም የኢስዋትኒ የውጭ ጉዳይ እና የአለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ፎሊል ድላሚኒ ሻካንቱ፣ የቶጎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሮበርት ዱሰይ፣ የታንዛኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የምስራቅ አፍሪካ ትብብር ሚኒስትር አምባሳደር ማህመድ ታቢት ካምቦ እና የላይበሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳራ በይሶሎው ኒያንቲ አዲስ አበባ ገብተዋል።

እንዲሁም የኮንጎ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኖይላ ናክዊፓኔ አዬጋናጋቶ 48ኛው የአፍሪካ ህብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ እና 39ኛው የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ከገቡት መከካል ይገኙበታል።

ሚኒስትሮቹ ቦሌ አለም አቀፍ ኤርፖርት ሲደርሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የሚኒስትሮች የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ 39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የሚቀርቡ አጀንዳዎችን እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል።


 

የጅቡቲ፣ የቻድ፣ የጊኒ ሪፐብሊክ፣ የሌሴቶ፣ የኬንያ፣ አልጄሪያ እና ሞሮኮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ትላንት ለሊት አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም