ቀጥታ፡

ውኃ ለአፍሪካ የኅልውና ጉዳይ ነው - መሐሙድ አሊ ዩሱፍ

አዲስ አበባ፤ ጥር 4/2018 (ኢዜአ)፦ ውኃ ሁሉንም ዘርፍ የሚነካ አህጉራዊ የኅልውና ጉዳይ መሆኑን የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ገለጹ።

51ኛው የአፍሪካ ሕብረት የቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ (PRC) መደበኛ ስብሰባ ከዛሬ ጀምሮ የሕብረቱ ዋና መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

ስብሰባው"ዘላቂ የውኃ አቅርቦትና ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነትበሚል የአፍሪካ ሕብረት ባዘጋጀው 2026 መሪ ሐሳብ የሚደረግ ነው።


 

በስብሰባው ላይ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ፣ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀ መንበር አምባሳደር ሳልማ ማሊካ ሃዳዲ፣ የአፍሪካ ሕብረትና የሕብረቱ ተቋማት አመራሮች፣ የሕብረቱ አባል ሀገራት አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ተሳትፈዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ የዘንድሮው የአፍሪካ ሕብረት ትኩረቱን ያደረገው በውኃ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ውኃ በሁሉም አይነት እጅጉን ወሳኝ የሆነ ሀብት እና የኅልውና ጉዳይ መሆኑን ገልጸው፤ አህጉራዊ ግቦቹን ለማሳካት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት አስገንዝበዋል።

በብራዚል ቤለም የተካሄደው 30ኛው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 30) ትኩረት ከተሰጣቸው አጀንዳዎች መካከል አንዱ መሆኑንም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ በምታዘጋጀው 32ኛው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 32) ውኃ አንዱ አጀንዳ እንደሚሆንም ተናግረዋል።

ሊቀ መንበሩ ኢትዮጵያ ኮፕ 32ለማዘጋጀት በመመረጧ በድጋሚ እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁ ያሉ ሲሆን፤ ለጉባኤው ስኬታማነት ሕብረቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

በሌላ በኩል ሰላም እና ደኅንነት የአፍሪካ አንገብጋቢ አጀንዳ መሆኑን የገለጹት ሊቀ መንበሩ ሱዳን፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሊቢያን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

-ሕገመንግሥታዊ ለውጦች አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ጠቅሰው፤ ሀገራት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እንዲያከብሩ አሳስበዋል።

የአፍሪካ ብረት ተቋማዊ ሪፎርም እና ኢኮኖሚያዊ ትሥሥርን ጨምሮ አህጉራዊ አጀንዳዎች እየሠራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

አህጉራችን ፈተናዎች ቢኖሩባትም በጋራ ከቆምን እናልፋቸዋለን ሲሉም በአጽንኦት ገልጸዋል።

የዛሬው ስብስባ የካቲት 4 እና 5 ቀን 2018 . ለሚካሄደው 48ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ እንዲሁም የካቲት 7 እና 8 ቀን 2018 . ለሚከናወነው 39ኛው የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ የሚቀርቡ ረቂቅ አጀንዳዎች ላይ ይወያያል ተብሎ ይጠበቃል።

51ኛው የአፍሪካ ሕብረት የቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ ስብሰባ እስከ ጥር 22 ቀን 2018 . የሚቆይ ሲሆን፤ የኮሚቴው መደበኛ ስብስባ ለዋናው ጉባኤ እንደ ይፋዊ የዝግጅት ስብስባ የሚያገለግል ነው።

የአፍሪካ ሕብረት የቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ የሕብረቱን ቋሚ ተወካዮችና የአባል ሀገራቱን አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ያቀፈ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም