ቀጥታ፡

ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓት፤ የአፍሪካ ህብረት የ2026 መሪ ሀሳብ ዋና የትኩረት አጀንዳ

39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የካቲት 14 እና 15 ቀን 2018 ዓ.ም በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ይካሄዳል። “ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” የ2026 የአፍሪካ ህብረት መሪ ቃል ነው።

መሪ ሀሳቡን ያረቀቀው የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚ እና ዘላቂ ከባቢ አየር ኮሚሽን ነው። የዘንድሮው መሪ ሀሳብ ጭብጥ በአፍሪካ የውሃ ደህንነትና ንጽህና አጠባበቅ ላይ ትኩረቱን አድርጓል።

የዘንድሮው መሪ ቃል ከአጀንዳ 2063 ጋር የተቆራኘ መሆኑን የአፍሪካ ህብረት መረጃ ያመለክታል።

ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተረጋገጠ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓት ዘላቂ ልማት፣ አካታች እድገት፣ ጤናማ ማህበረሰብና ጠንካራ ስነ ምህዳር መገንባት፣ የተፈጥሮ ሀብት ዘላቂ አጠቃቀምና የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል ከአጀንዳ 2063 ግቦች ጋር የተሳሰረ መሆኑ ተገልጿል።

ሁሉም አፍሪካዊ ንጹህ፣ ደህንነቱ የተጠበቀና በቂ ውሃ ለመጠጥ፣ ለግብርና፣ ለኢንዱስትሪ እና ለሌሎች ፍላጎቶቹ እንዲያገኝ የማድረግ ራዕይን ለማስተዋወቅ እድል እንደሚፈጥርም ታምኖበታል።


 

ህብረቱ የውሃ ደህንነት እንደ አህጉር የተያዙ ስትራቴጂካዊ ግቦችን ለማሳካት ወሳኝ መሆኑን በማዕቀፎቹ አስቀምጧል። ውሃ እና ንጽህና የኢኮኖሚ እድሎችን በማስፋት፣ የስራ አጥነት ምጣኔን በመቀነስ፣ የስደቶችና ተፈናቃዮችን ጫና ለማቃለል እንዲሁም ለሰላምና ደህንነት መስፈን አስተዋጽኦ እንዳላቸው ተመላክቷል።

የ2026 የአፍሪካ ህብረት መሪ ሀሳብ ህብረቱ ውሃ እና ንጽህና ለጤና፣ ለኢኮኖሚ እድገት፣ የምግብ ዋስትና መረጋገጥና ዘላቂ የአካባቢ ምህዳር ለመፍጠር መሰረት መሆኑን የበለጠ እውቅና እንደተሰጠው አመልክቷል።

ሁሉን አቀፍ እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይገበር የውሃ ደህንነትን የማረጋገጥ አላማ ካለው የአፍሪካ የውሃ ፖሊሲ ጋር የተጣጣመ ነው። የዘንድሮው መሪ ቃል የአፍሪካ እና ዓለም አቀፍ ጥረቶችን ያስተሳሰረ ድልድይ ሆኗል።

በዘላቂ ልማት ግቦች ውስጥ ያለው ግብ ስድስት ከውሃ እና ንጽህና ጋር የተያያዘ ነው። ይህ ግብ እ.አ.አ በ2030 ለሁሌም ዜጋ ደህንነቱ የተረጋገጠ ውሃ አቅርቦትና የንጽህና አጠባበቅን ተደራሽ የማድረግ አላማ አለው።

የአየር ንብረት ለውጥ፣ የህዝብ እድገት፣ የከተሜነት በፍጥነት መስፋፋትና ውሃ በአግባቡ አለመጠቀም የውሃ ደህንነት እና ዘላቂ አቅርቦት ላይ ተጽእኖ አሳድሯል።

የንጽህና አጠባበቅ የአፍሪካ አንዱ ፈተና ነው። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች መሰረታዊ የሚባል የንጽህና መጠበቂያ መሰረተ ልማቶችን አያገኙም። ይህም እንደ ኮሌራ ላሉ የውሃ ወለድ በሽታዎች መስፋፋት ምክንያት ሆኗል።

የተቀናጀ የውሃ አስተዳደር ስርዓት፣ ድንበር ተሻጋሪ ትብብር፣ ለዘላቂ መሰረተ ልማት የሚፈሰወን መዋዕለ ንዋይን ማሳደግ፣ ውሃ በድጋሚ አጣርቶ መጠቀም፣ የውሃ ሀብቶችን መጠበቅ፣ ዘላቂ የውሃ ሀብት አስተዳደር እና ለውሃ ደህንነት ትኩረት የሚሰጡ ፖሊሲዎችና ማዕቀፎችን በውጤታማነት መተግበር ያሉትን እድሎች በዘላቂነት ለመፍታትና ፈተናዎችን ለመቅረፍ ያስችላል።

ደህንነቱ የተረጋገጠ የፍሳሽ ማስወገጃ ስርዓት ላይ ያለፈውን ኢንቨስትመንት ማሳደግ፣ የቆሸሸ ውሃ በአግባቡ ማከም፣ የንጽህና አጠባበቅ ማስፋትና የግንዛቤ ፈጠራ ስራን በስፋት ማከናወን፣ ማህበረሰብ መር የንጽህና አጠባበቅ ኢኒሼቲቮችን ትግበራ ማስፋት፣ ጠንካራ የፖሊሲ ማዕቀፎችና ሀገር በቀል አቅምን መገንባት ደህንነቱ የተረጋገጠ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓትን መፍጠር ያስችላል።

“ዘላቂ የውሃ አቅርቦት እና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” የ2026 የአፍሪካ ህብረት መሪ ቃል ለአፍሪካ ዘላቂ ልማት፣ የኢኮኖሚ እድገት እና ጤናማ ማህበረሰብ ግንባታ ያላቸውን ቁልፍ ሚና የሚያሳይ ነው።

የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተረጋገጠ የንጽህና አጠባበቅን ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ ማድረግ መሰረታዊ መብቶች እንዲጠበቁ ከማድረግ ባለፈ ለማህበረሰብ ደህንነትና የተሻለ የኑሮ ዘይቤ፣ ለአካባቢ ጥበቃና ለአፍሪካ ብልጽግና መረጋገጥ ስትራቴካዊ አቅም ናቸው። 

39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የካቲት 14 እና 15 ቀን 2018 ዓ.ም በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ በሚካሄድበት ወቅት በመሪ ሀሳቡ በጥልቀት በመምከር የተለያዩ የውሳኔ ሀሳቦች ይተላለፋል ተብሎ ይጠበቃል።

ከመሪዎቹ ጉባኤ አስቀድሞ  48ኛው የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ የካቲት 11 እና 12 ቀን 2018 ዓ.ም እና  51ኛው የአፍሪካ ህብረት ቋሚ መልዕክተኞች ስብሰባ ከጥር 4 እስከ 22 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳሉ።

ኢትዮጵያ 39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ እና የአፍሪካ ጣሊያን ስብሰባን ለማዘጋጀት ብሄራዊ የዝግጅት ኮሚቴ ተቋቁሞ እየሰራ እንደሚገኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም