ቀጥታ፡

የአፍሪካ ህብረት እና ጃፓን ትብብራቸውን ለማጽናት ቁርጠኝነታቸውን ገለጹ

አዲስ አበባ፤ ጥር 6/2018(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ህብረት እና ጃፓን በባለብዙ ወገን መድረኮች ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰሩ አስታወቁ።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ከጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አያኖ ኩኒሚትሱ ጋር በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ተወያይተዋል።


 

የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር የአፍሪካ ህብረት እና ጃፓን ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ትብብር እንዳላቸው አውስተው በጃፓን አፍሪካ ልማት ዓለም አቀፍ ፎረም (ቲካድ) ማዕቀፍ ያላቸውን ግንኙነት አንስተዋል።

በዮካሃማ በነሃሔ ወር 2017 ዓ.ም የተካሄደው ዘጠነኛው የጃፓን አፍሪካ ልማት ዓለም አቀፍ ፎረም(ቲካድ) በሁለቱ ወገኖች አጋርነት ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሆኑን አመልክተዋል።

ውይይቱ የሁለትዮሽ ትብብሩን የበለጠ ማጠናከርን ያለመ ነው።

ጃፓን ለአፍሪካ የበሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል (African CDC) እያደረገች ያለው ድጋፍ እንዲሁም የአፍሪካ ዘላቂ እድገት እና ትስስር ለሚደግፉ የመሰረተ ልማት ስራዎች እያፈሰሰች ያለው መዋዕለ ንዋይ እያደገ መምጣቱ ተመላክቷል።

የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አያኖ ኩኒሚትሱ ዘጠነኛው የጃፓን አፍሪካ ልማት ዓለም አቀፍ ፎረም (ቲካድ) በስኬት መካሄዱን አድንቀዋል።

10ኛው ቲካድ በአፍሪካ እንዲካሄድ ጃፓን ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ጋር በቅርበት ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን አመልክተዋል።


 

ሀገራቸው የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) እና የአፍሪካ የመሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም (ፒዳ) ጨምሮ የአፍሪካ ህብረት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ቁልፍ ኢኒሼቲቮች መደገፏን እንደምትቀጥል ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ሚኒስትር ዴኤታዋ በዓለም አስተዳደር ውስጥ እያደገ የመጣውን የአፍሪካ ሚና በማንሳት የአፍሪካ ህብረት በቡድን 20 ቋሚ አባል መሆኗ ትልቅ ሽግግር መሆኑን ተነግረዋል።

ባለስልጣናቱ በአፍሪካ ህብረት እና ጃፓን የከፍተኛ ደረጃ የምክክር መድረክ እና ቲካድ አማካኝነት ትብብራቸውን የበለጠ ለማጠናከር እና የባለብዙወገን ዲፕሎማሲ እንዲጸና በጋራ እንደሚሰሩ መግለጻቸውን ኢዜአ ከህብረቱ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

የአፍሪካ ህብረት እና ጃፓን እ.አ.አ በ1993 አጋርነት መመስረታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ሰላም እና ደህንነት፣ ኢኮኖሚ፣ ልማት፣ ንግድ፣ ጤና ፣ ግብርና፣ ቴክኖሎጂ እና የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ከሁለቱ ወገኖች የትብብር መስኮች መካከል ይጠቀሳሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም