ቀጥታ፡

51ኛው የአፍሪካ ሕብረት የቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባ ዛሬ ይጀመራል

አዲስ አበባ፤ ጥር 4/2018 (ኢዜአ)፦ 51ኛው የአፍሪካ ሕብረት የቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ (PRC) መደበኛ ስብሰባ ከዛሬ ጀምሮ የህብረቱ ዋና መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ መካሄድ ይጀምራል።

ስብሰባው "ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል የአፍሪካ ህብረት ባዘጋጀው የ2026 መሪ ሃሳብ የሚደረግ ነው።

የዘንድሮው መሪ ሀሳብ ጭብጥ በአፍሪካ የውሃ ደህንነትና ንጽህና አጠባበቅ ላይ ትኩረቱን አድርጓል።

በስብሰባው ላይ የአፍሪካ ሕብረትና የሕብረቱ ተቋማት አመራሮች፣የሕብረቱ አባል አገራት አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች እንደሚሳተፉበት ኢዜአ ከህብረቱ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ስብስባው የካቲት 4 እና 5 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚካሄደው 48ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ እንዲሁም የካቲት 7 እና 8 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚከናወነው 39ኛው የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ የሚቀርቡ ረቂቅ አጀንዳዎች ላይ ይወያያል ተብሎ ይጠበቃል።

በተጨማሪም ኮሚቴው በአፍሪካ ሕብረት ስር የሚገኙ የተለያዩ ተቋማትን የአፈጻጸም እንዲሁም ሕብረቱ እ.አ.አ በ2025 ያካሄዳቸውን ስብሰባዎች የተመለከቱ ሪፖርቶችን ያደምጣል። 

ሰላም እና ደህንነት፣ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣናን ጨምሮ የኢኮኖሚ ትስስር፣ የተቋማዊ ሪፎርሞች እና የበጀት እቅዶችን የተመለከቱ የቴክኒክ ሰነዶችንም ያዘጋጃል። 

ኮሚቴው በ2026 የአፍሪካ ህብረት መሪ ሀሳብ ላይ ምክረ ሀሳቦችን ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል። 

51ኛው የአፍሪካ ሕብረት የቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ ስብሰባ እስከ ጥር 22 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።

የኮሚቴው መደበኛ ስብስባ ለዋናው ጉባኤ እንደ ይፋዊ የዝግጅት ስብስባ የሚያገለግል ነው። 

የአፍሪካ ሕብረት የቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ የሕብረቱን ቋሚ ተወካዮችና የአባል አገራቱን አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ያቀፈ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም