ፖለቲካ
ለሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ስኬት የራሳችንን ሚና ከመወጣት ባሻገር ህዝብን በማስተባበር ሃላፊነታችንን እንወጣለን- የምክር ቤት አባላት
Jun 1, 2024 66
ሚዛን አማን ፤ ግንቦት 24/2016 (ኢዜአ)፦ ለሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ስኬት የራሳቸውን ሚና ከመወጣት ባሻገር የክልሉን ሕዝብ በባለቤትነት እንዲሳተፍ የማስተባበር ኃላፊነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የብሔረሰቦች ምክር ቤት አባላት ገለጹ። ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የምክር ቤቱ አባላት እንደገለፁት፤ ምክክሩ ለዘመናት ችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሄና ዕድል ይዞ የመጣ በመሆኑ ለስኬታማነቱ ሕዝብን በማስተባበር ኃላፊነታችንን እንወጣለን ብለዋል። ምክክሩ የኢትዮጵያውያንን መልካም እሴቶች መሠረት ባደረገ መልኩ የሚከናወን በመሆኑ ሂደቱን ይበልጥ እንደሚያቀላጥፍ ገልጸው ለዘላቂ አብሮነትና ሰላምም ትልቅ ትርጉም እንዳለውም አመልክተዋል። ከምክር ቤቱ አባላት መካከል አቶ ተስፋዬ መኩሪያ የምክክር ኮሚሽኑ በጋራ ማንነት ላይ ተስማምቶ የጋራ ሀገር ለመገንባት የሚያስችል በጎ እድልን ይዞ የመጣ ተቋም ነው ብለዋል። በመሆኑም እንደ ብሔረሰቦች ምክር ቤት አባል ለተግባራዊነቱ ሕዝቦች በባለቤትነት እንዲሳተፉ የማስቻል ኃላፊነት ወስደው እንደሚንቀሳቀሱም ገልፀዋል። በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ መመካከር ወንድማማችነትን በማጎልበት ሀገራዊ ለውጡ በጋራ ተሳተፎ እንዲፋጠን ያደርጋል የሚል እምነት እንዳላቸው የገለጹት ደግሞ ሌላኛዋ የምክር ቤቱ አባል ወይዘሮ ፀሐይ አየለ ናቸው። በምክክር ለሚመጣው ዘላቂ ሰላምና አብሮነት ሲባል ዛሬ ላይ የምክክር ሂደቱን በቻሉት አቅም በመደገፍና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ባሉበት አካባቢ ደግሞ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ማስተባበርን የጨመረ ጥረት አደርጋለሁ ብለዋል። ሌላው የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት አባል አቶ ባህሩ ወልደጊዮርጊስ በበኩላቸው ለኢትዮጵያ ልዕልና እንደ ሀገር አንድ በሚያደርጉን ነገሮች ላይ ማተኮር አለብን ብለዋል። ልዩነቶችን በማጥበብ ለሀገር አንድነት መጽናት መንግስት የፈጠረውን መልካም አጋጣሚ ደግፎ ከግብ ማድረስ እንደሚገባም ተናግረዋል። የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ አቶ መቱ አኩ በኢትዮጵያ ለምክክር ትልቅ ትርጉም ያላቸው በርካታ በጎ እሴቶት እንዳሉ ጠቅሰዋል። የእሴቶቹ ባለቤት የሆነውን ሕዝብ ይዘን ከሠራን የሃገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ተግባር ውጤታማ የማይሆንበት ምክንያት እንደሌለም አረጋግጠዋል። በተለይ የአንድ ወገን እይታን በመተው ግራ ቀኝ ተመልክቶና ተደማምጦ የእውነትን ሚዛን መጠበቅ በምክክሩ ወቅት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አመልክተዋል። የጋራ የሆኑ ገዢ ሃሳቦች ላይ ተነጋግሮ በመተማመን መጓዝ ከተቻለ ኢትዮጵያን ከፍ የሚያደርግ ትውልድ ይገነባል ብለዋል።
መንግሥት በሀገራዊ ምክክሩ መግባባት ላይ የሚደረስባቸውን ድምዳሜዎች ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
Jun 1, 2024 108
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 24/2016 (ኢዜአ)፦ መንግሥት በሀገራዊ ምክክሩ መግባባት ላይ የሚደረስባቸውን ድምዳሜዎች ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሀገር አቀፍ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍን በአዲስ አበባ አስጀምሯል። በአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም አዳራሽ በተካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ማስጀመሪያ መድረክ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደ አንድ የምክክሩ ሂደት ባለድርሻ አካል መንግሥታቸውን ወክለው ተገኝተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመድረኩ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በጦርነት እያለፈች እና በርካታ ስብራቶች እየገጠሟት ያለች ሀገር መሆኗን ገልፀዋል። ከዚህ የጦርነት እና የስብራት ታሪክ ለመውጣት ምክክር ሁነኛ መፍትሄ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው አስምረውበታል። “ዛሬ ለኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ አዲስ ምዕራፍ ሁላችንም በንቃት ልንሳተፍ ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ከተቃርኖ ይልቅ ተዛምዶን በማጠናከር፣ መጓደልን በመሙላት ኢትዮጵያን ተስፋ ያላት ሀገር ማድረግ የሀገራዊ ምክክሩ ዓላማ እንደሆነ ጠቁመዋል። አክለውም በታሪክ ሂደት ተደጋግሞ የማይገኘውን ይህንን ታሪካዊ የምክክር አጋጣሚ በሚገባ መጠቀም ሁላችንንም አሸናፊ ያደርገናል ሲሉም ተናግረዋል። በመሆኑም የትኛው አካል ይህ የምክክር እድል እንዳያመልጠው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል። መንግስት በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ስራ ላይ በምንም ሁኔታ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት የለውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኮሚሽኑን የሚመሩት ኮሚሽነሮችም በካበተ እውቀታቸውና ተሞክሯቸው ለኢትዮጵያ የሚጠቅም ስራ ከመስራት ውጪ ሌላ ፍላጎት የላቸውም ሲሉም በኮሚሽነሮቹ ላይ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል። በምክክሩ መግባባት ላይ የተደረሰባቸውን ድምዳሜዎች ለማስፈፀም መንግስታቸው ቁርጠኛ መሆኑን ጠቁመው፤ የማንስማማባቸው አጀንዳዎች የሚገጥሙን ከሆነም በህዝበ ውሳኔ (ሪፈረንደም) እልባት ያገኛሉ ብለዋል። ሕዝብ ከወሰነ በኋላ ማናችንም ብንሆን የሕዝቡን ውሳኔ ማክበር ይኖርብናል ሲሉ መግለጻቸውን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል፡፡ በሀይል አማራጭ የሀሳብ ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚደረግ ጥረት ጊዜያዊ አሸናፊና ተሸናፊ ፈጥሮ ከማለፍ በዘለለ ለችግራችን ዘላቂ መፍትሄ አያስገኝም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ እያካሄደቸው ባለው ምክክር የሚከስር እንደሌለ ገልፀው በሂደቱ ሀገር አሸናፊ ትሆናለች ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት ሀገር አቀፍ ምክክር ተጀመረ
Jun 1, 2024 106
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 24/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገር አቀፍ ደረጃ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበትን የምክክር ምዕራፍ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት አስጀምሯል። በዓድዋ ድል መታሰቢያ በተጀመረው ሀገር አቀፍ የምክክር ምዕራፍ ላይም የሕብረተሰብ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሦስቱ የመንግስት አካላት (ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚና ሕግ ተርጓሚ)፣ የተቋማትና የማኅበራት ተወካዮች እንዲሁም ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ተሳትፈዋል፡፡   የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) በመድረኩ ላይ እንዳሉት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በርካታ ፈተና ቢገጥመውም ሳይበገር መቀራረብንና መግባባትን ለማምጣት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡ እስከ አሁን በ10 ክልሎችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች ከ1 ሺህ በሚልቁ ወረዳዎች በአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ሂደት የሚሳተፉ ተወካዮች ማስመረጥ መቻሉን ጠቁመው፤ በአዲስ አበባ የአጀንዳ መሰብሰብ ስራ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡ በቀጣይም የተሳታፊዎች መረጣ በተካሄደባቸው ክልሎችና በድሬዳዋ ከተማ አጀንዳ እንደሚሰበሰብ አስረድተው፤ በአማራና ትግራይ ክልሎች ደግሞ የተሳታፊዎች ልየታና መረጣ እንደሚካሄድ አመላክተዋል፡፡ ኮሚሽኑ የአሁኑ ወጣት ትውልድ ከቀደሙት ትውልዶች ብዙ ተምሮ የተሻለ የሰላምና የእድገት ውርስ ይተዋል የሚል እምነት እንዳለውም ገልጸዋል፡፡ “ከስብራት ሕይወት ወጥተን ወደ ተሻለ ሕይወት እንሸጋገር ዘንድ ወጣቱ ችግሩን በአጀንዳ ቀረፃ ጠብመንጃውን ወደ ሐሳብ መንጃና ማንሸራሸሪያ እንዲቀይር ኮሚሽኑ በትህትና ይጠይቃል” ብለዋል፡፡ የሀገራችንን ችግር ወደ ሀገራዊ መፍትሔ ለማምጣት ኮሚሽኑ በምክክር ሂደት የሰላም በር በየትኛውም ቦታ ላሉ ወገኖች እንዲመቻች ጠንክሮ እንደሚሰራ ማረጋገጣቸውን የኮሚሽኑ መረጃ አመላክቷል፡፡ በተጀመረው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ አጀንዳውን በግልም ሆነ በጋራ ወደ ኮሚሽኑ ማምጣት እንደሚችል ገልጸው፤ ምክክሩ አካታች እንደሚሆንና ሂደቱም ግልፅና ተዓማኒ በሆነ መልኩ እንደሚከናወን አስረድተዋል፡፡
በአካባቢያችን የተገኘውን ሰላም በማጽናት ልማታችንን ለማረጋገጥ እየሰራን ነው
Jun 1, 2024 89
አዲስ አበባ ፤ ግንቦት 24/2016(ኢዜአ)፦ በአካባቢያቸው የተገኘውን ሰላም ዘላቂ በማድረግ ልማታቸውን ለማረጋገጥ እየሰሩ መሆኑን በምስራቅ ወለጋ ዞን የጉቶ ጊዳ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ። የወለጋ ዞኖች ነዋሪዎች የለውጡን መንግሥት ለመደገፍ ያለመ ሰልፍ በነቀምቴ ባካሄዱበት ወቅት ሰላማቸውን ለመጠበቅ፣ ልማታቸውን ለማረጋገጥ፣ እንዲሁም ለውጡን ለማጽናትና ወለጋን የሰላምና የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ እንደሚሰሩ መግለጻቸው ይታወሳል። በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት ሕዝቡ በሰላም፣ በአንድነትና በልማት ላይ በማተኮር እጅ ለእጅ ተያይዞ መሥራት አለበት ብለዋል። ልማትና እድገትን ለማፋጠን ሰላም ወሳኝ መሆኑን በመግለጽ ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን በመቆም በአካባቢው ሰላም እንዲጸና መትጋት እንደሚገባውም ተናግረዋል። የአካባቢው ሕዝብ በድጋፍ ሰልፉ ላይ በገባው ቃል መሰረት ከመንግሥት ጎን በመቆም ሰላም ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት በመሥራቱ ሰላም እየተረጋገጠ ይገኛል። ኢዜአ በምስራቅ ወለጋ ዞን ጉቶ ጊዳ ወረዳ ተገኝቶ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች በሰላም እጦት ምክንያት ተፈትነው መቆየታቸውን አስታውሰው አሁን ላይ ሕዝብና መንግሥት በመቀናጀት ባከናወኑት ተግባር በአካባቢው ሰላም መስፈኑን ተናግረዋል። አካባቢው ሰላም በመፈጠሩ ፊታቸውን ወደ ልማት ሥራዎች ማዞራቸውንም ገልጸዋል። የወረዳው ነዋሪ አቶ አለማየሁ ቤኒ እንዳሉትም በአካባቢያቸው ሰላም በመደፍረሱ በርካታ ችግሮችን ማሳለፋቸውን አስታውሰው ሕዝብና መንግሥት በመቀናጀት በሰሯቸው ሥራዎች ዛሬ ላይ ሰላማቸው መመለሱን ተናግረዋል። ይህን ሰላም ዘላቂ በማድረግ ልማታቸውን ለማረጋገጥ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ነው የተናገሩት። አቶ ኦልቀባ አንኮሳ በበኩላቸው በሰላም እጦት ምክንያት ከተለያዩ ቀበሌዎች በርካታ ሰዎች ተፈናቅለው እንደነበር አስታውሰዋል። ዛሬ ላይ በአካባቢው በተገኘው ሰላም ተፈናቃዮች ወደ ቀየአቸው እንዲመለሱና የልማት ሥራዎቻቸውን እንዲያከናውኑ ዕድል መፈጠሩን ጠቁመዋል። ነዋሪዎቹ በአካባቢያቸው የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግና በልማት ሥራዎች ተጠቃሚ ለመሆን በርትተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል። ሰላም ለሁሉም ነገር መሰረት ነው ያሉት ነዋሪዎቹ የተገኘውን ሰላም ለማጽናት ከመንግሥት ጎን በመሆን እንደሚሰሩም ገልጸዋል። ትናንት ወዳሳለፉት አስቸጋሪ ሁኔታ ላለመመለስ ተደራጅተው የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል። በመንግሥት በኩል እየቀረቡላቸው የሚገኙትን የግብርና ግብዓቶች በአግባቡ በመጠቀም በግብርና ሥራዎች ውጤታማ ለመሆን እየሰሩ መሆናቸውም ጠቁመዋል።   በምስራቅ ወለጋ ዞን የጉቶ ጊዳ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ተመስገን ገቢሳ የተገኘውን ሰላም ለማጽናት ህዝቡን በማደራጀት የአካባቢውን ሰላም በራሱ እንዲጠብቅ የማድረግ ሥራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል። ህዝቡ እኩይ አላማ አንግበው ሰላሙን የሚያደፈርሱ አካላትን ምንነት በመረዳቱ ከመንግሥት ጎን ሆኖ ሰላሙን እየጠበቀና ልማቱን እያረጋገጠ ይገኛል ብለዋል።      
በምክክር ምዕራፍ የአጀንዳ ማሰባሰብ የታየው አካታችና አሳታፊ ሂደት የሚበረታታ ነው-የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት
Jun 1, 2024 81
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 24/2016(ኢዜአ)፦ በሀገራዊ የምክክር ምዕራፍ የአጀንዳ ማሰባሰብ የታየው አካታችና አሳታፊ ሂደት የሚበረታታ መሆኑን የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት ዳይሬክተርና የሴቶች ድምጽ በአገራዊ ምክክር ጥምረት ሰብሳቢ ሳባ ገብረመድህን ተናገሩ። ዳይሬክተሯ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ የሴቶች ድምጽ በአገራዊ ምክክር ጥምረት ከ50 በላይ ድርጅቶችን አካቶ የምክክር ሂደቱ ከተጀመረ አንስቶ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። ጥምረቱ በአዲስ አበባ በየወረዳው የተለያዩ የሴቶች መድረኮችን በማዘጋጀት በምክክሩ መነሳት ያለባቸው አጀንዳዎች ላይ ውይይት ማድረጉን ገልጸዋል። በመዲናዋ የተጀመረው የሀገራዊ ምክክር ምዕራፍ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ሴቶችን ጨምሮ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ አካታችነትን ያረጋገጠና የሚበረታታ እንደሆነ ገልጸው፥ ይህም እስከመጨረሻው በስኬት እንዲቀጥል ሁሉም በጎ ሚና መጫወት አለበት ብለዋል። በአሁኑ ወቀት በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የሚደረጉ የምክክር ሂደቶች ለዋናው ሀገራዊ ምክክር መሰረት እንደሚጥሉ ያነሱት ዳይሬክተሯ፥ ምክክር በዴሞክራሲዊና ሰላማዊ መንገድ መግባባትን ለመፍጠርና ፍትህን ለማምጣት ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል። ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ሀገርን በዘላቂነት ከግጭትና ሌሎች መሰረታዊ ችግሮች ለማላቀቅ ትልቅ እድል ይዞ የመጣውን አገራዊ ምክክር በአግባቡ መጠቀምና ለስኬቱ በኃላፊነት መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል። ሴቶች ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የመፍትሔ አካል በመሆናቸው ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉም ነው ወይዘሮ ሳባ ገብረመድህን የጠየቁት። እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አካታች ሀገራዊ ምክክሮችን ማካሄድ የተሻለ ሀገራዊ መግባባትን ለመገንባት በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 ተቋቁሞ ወደ ስራ የገባው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አሁን ላይ ሶስተኛውን ምዕራፍ መተግበር ጀምሯል። አካታች የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ የቅድመ ዝግጅት፣ ዝግጅት፣ የምክክር ሂደት፣ የትግበራና ክትትል ምዕራፎች አሉት። የምክክር ምዕራፍ አካል የሆነው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ በይፋ የተጀመረ ሲሆን የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ወኪሎች ለሶስት ቀናት በአጀንዳ ሀሳቦች ላይ ሲያደርጉት የነበረውን ውይይት አጠናቀዋል። በዚህም በከተማ አስተዳደር ደረጃ በሚካሄደው ምክክር እንዲንፀባረቁላቸው የፈለጓቸውን አጀንዳዎች በመለየት ለኮሚሽኑ ያስረከቡ ሲሆን፥ አጀንዳዎቻቸውን በምክክሩ ላይ የሚያቀርቡ 121 ተወካዮቻቸውን መምረጣቸውን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታውቋል።        
የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ በ2017 በጀት ጣሪያ ላይ ተወያይቶ አቅጣጫ አስቀመጠ
Jun 1, 2024 98
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 24/2016(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ ዛሬ በ3ኛ አመት 13ኛ መደበኛ ስብሰባው የመካከለኛ ዘመን የ2017 በጀት ጣሪያ ላይ ተወያይቶ አቅጣጫ አስቀምጧል። ካቢኔው ዛሬ ባደረገው ከ2007 እስከ 2019 በጀት ዓመት የመካከለኛ ዘመን የወጪ ማዕቀፍ ውይይት መሰረት የ2017 በጀት ዓመት ከተለያዩ የገቢ አርዕስቶች 230 ነጥብ 39 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ማቀዱ ተገልጿል። የበጀት ድልድሉም ከጠቅላላ በጀት ውስጥ 61% ለካፒታል ወጪ ሆኖ በጀቱም በዋናነት በቅርቡ በከተማ አስተዳደሩ የትራንስፎርሜቲቭ ፕላን ዝግጀት ለተያዙ ቁልፍና እድገት ተኮር ዘርፎች የበጀት ድልድሉ የትኩረት አቅጣጯ መሆን አንዳለበት ካቢኔው መወያየቱም ተመላክቷል። በመጨረሻም አዲስ አበባ በገቢ ግብር በጀቷን የምታስተዳድር ከተማ እንደ መሆኗ መጠን የገቢ አቅሟን አሟጦ መሰበሰብ የሚገባ መሆኑ አጽንኦት ሰጥቶ በመወያየት የገቢ አሰባሰብ ስርአት ላይ ትኩረት ሰጥተው ተቋማት መስራት የሚችሉበት ቀጣይ አቅጣጫም በትኩረት ድጋፍ እና ክትትል እንደሚደረግበት ውሳኔ ማሳለፉንም የከንቲባ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።    
የሜጀር ጄኔራል ሙልጌታ ቡሊ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ባለው ውስን አቅም ችሎታውና እውቀቱ የተገነባ ሠራዊት ለመፍጠር የሚያከናውነው ተግባር የሚደነቅ ነው -ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ
May 31, 2024 123
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 23/2016 (ኢዜአ)፦ የሜጀር ጄኔራል ሙልጌታ ቡሊ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ባለው ውስን አቅም ችሎታውና እውቀቱ የተገነባ ሠራዊት ለመፍጠር የሚያከናውነው ተግባር የሚደነቅ ነው ሲሉ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ። የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የሜጄር ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅን በዛሬው ዕለት ጎብኝተዋል። ኮሌጁ የተሻለና ዘመናዊ ሠራዊት ለመገንባት የሚያደርገውን ጥረት ለመደገፍ የሚያስችል ምክክርም አካሂደዋል።   ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ሠራዊቱ በታጠቀው መሳሪያ ላይ የተሻለ አቅምና እውቀት እንዲኖረው ከሚያስችሉ ኮሌጆች መካከል ብቸኛው ኮሌጅ የሜጄር ጀኔራል ሙልጌታ ቡሊ ፓሊ ቴክኒክ ኮሌጅ መሆኑን ጠቁመው፤ ኮሌጁን መደገፍና ያሉበትን ችግሮች መቅረፍ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን መሠረታዊ ጉዳይ ነው ብለዋል። ኮሌጁም የማሰልጠን አቅሙን ወደ ዲጂታል መቀየር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ማተኮርና መስራት እንዳለበት ጠቁመዋል። ኮሌጁ ከተመሠረተ ጀምሮ በርካታ ወታደር ሙያተኞችን ከሀገር ውስጥ እስከ ጎረቤት ሀገር ድረስ ማሰልጠኑን የጠቆሙት የኮሌጁ አዛዥ ብርጋዲየር ጀኔራል አበበ ዋቅሹማ በቀጣይም ያለበትን የመማር ማስተማር ችግር መቅረፍ ከተቻለ በሙሉ አቅሙ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማሰልጠን ይችላል ብለዋል። በጉብኙቱ ላይ የተገኙት የመከላከያ ከፍተኛ አመራሮችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም ኮሌጁ የሠራዊቱን የማድረግ አቅም በማጠናከር የተማረና ቴክኒካዊ እውቀቱ የጎለበተ ሰራዊት ለማፍራት የሚያከናውነውን ተግባር ማድነቃቸውን የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመለክታል። ከዚህ የተሻለ ስራ መስራት እንዲችልም ያለበትን ችግር ለመፍታትና ለማጠናከር በጋራ ለመስራት መዘጋጀታቸውን ማረጋገጣቸው ተገልጿል።            
ለምክክርና ውይይት ቅድሚያ በመስጠት ለዘላቂ ሠላም ግንባታ የበኩላችንን አሻራ ልናኖር ይገባል - ተሳታፊዎች
May 31, 2024 111
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 23/2016(ኢዜአ)፦ለምክክርና ውይይት ቅድሚያ በመስጠት ለዘላቂ ሠላም ግንባታ የበኩላችንን አሻራ ልናኖር ይገባል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ምዕራፍ ተሳታፊዎች ገለጹ። "ኢትዮጵያ እየመከረች ነው" በሚል መሪ ኃሳብ አጀንዳ ማሰባሰቢያ የምክክር ምዕራፍ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። በምክክር ምዕራፉ ላይ በርካታ ተወካዮች በመሳተፍ ላይ ሲሆኑ ተሳታፊዎች የወከሉትን የኅብረተሰብ ክፍል አጀንዳዎች በማቅረብ ለአገር ሠላምና ዕድገት መሳለጥ ሚናቸውን እየተወጡ ነው። አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ በሚካሄድባቸው ቦታዎች ኢዜአ ተዘዋውሮ የተመለከተ ሲሆን ተሳታፊዎችንም አነጋግሯል። ተሳታፊዎቹ በሰጡት አስተያየት አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደቱ አካታችና ነጻነትን በማይጋፋ መልኩ እየተካሄደ መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል። ሂደቱ ችግሮችን በሰከነ መንገድ ለመፍታት ለሚካሄዱ ቀጣይ አገራዊ ምዕራፎችም መሰረት የሚጥል እንደሆነም አንስተዋል። ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የመንግሥት ሰራተኞችን በመወከል የተገኙት የትምወርቅ ሰሙ በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ በመሳተፌ ትልቅ ደስታ ተሰምቶኛል፤ለአገሬ መለወጥ አስተዋጽኦ ማበርከት የምችልበት ዕድልንም ፈጥሮልኛል ብለዋል። ምክክሩ ላይ ያለንን አጀንዳዎች ያለገደብ እያቀረብን ነው፤ ውይይትና ምክክርም እያደረግን ነው ያሉት የትምወርቅ ይህም የውይይት እሴቶችን የሚያዳብር ነው ብለዋል። ለሠላም እጦትና ሌሎች ማኅበረሰባዊ ቀውሶች መከሰት ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ብልሹ አሰራር አንዱ መሆኑን ጠቅሰው የመንግሥት ሠራተኛው ከብልሹ አሰራር ራሱን በማራቅ ሃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል። እኛ የመንግሥት ሰራተኞች ሃላፊነታችንን በአግባቡ ብንወጣ የመፍትሄ አካል መሆን እንችላለን ሲሉም ተናግረዋል። በንግግርና ውይይት የማይፈታ ችግር የለም፤ ለምክክርና ውይይት ቅድሚያ በመስጠት ለዘላቂ ሠላም ግንባታ የበኩላችንን አሻራ ልናኖር ይገባል ያሉት ደግሞ ሌላው ተሳታፊ አቶ ተስፋዬ አሸናፊ ናቸው። ምክክሩ ጥሩ ምዕራፍ ላይ የደረሰ በመሆኑ ዕድሉን ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል። ሌላው ተሳታፊ አቶ ኪሩቤል እንዳለው በበኩላቸው ካልተወያየን እና ካልተመካከርን ወደ መፍትሄ መሄድ አንችልም፤ ልዩነት ያላቸውም አካላት የሰለጠነ መንገድን በመምረጥ ለአገር ሠላም አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም ጥሪ አቅርበዋል።    
የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን የሚያደርገውን ድጋፍ ያጠናክራል
May 31, 2024 104
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 23/2016(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ሙሉጌታ አበበ ተናገሩ። የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው የምክክር ምዕራፍ እንዲሁም ቀጣይ ውይይቶችን አስመልክቶ ለባለድርሻ አካላት ገለጻና የገንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሂዷል። የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ሙሉጌታ አበበ ለኢዜአ እንዳሉት ለአገራዊ መግባባት ኢትዮጵያ ችግሮቿን በንግግር መፍታት እንዳለባት ምክር ቤቱ በጽኑ ያምናል። ይህንንም ተከትሎ ምክር ቤቱ በአዲስ አበባ በ119 ወረዳዎች ላይ አጀንዳ ለመለየትና አጀንዳ የሚለዩ ሰዎችን ለማስመረጥ የሚያግዙ ሰዎችን ምክር ቤቱ ወክሎ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ይዞ የመጣውን እድል በመጠቀምና ውይይትን ልምድ በማድረግ በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር አበክሮ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት። በመሆኑም በጋራ ምክር ቤት ውስጥ የሚገኙ ፓርቲዎች አለን የምንለውን ነገር በምክክር ኮሚሽን ተወያይተን ለአገር ሥጋት የሚሆኑ ጉዳዮችን እናሻሽላለን የሚል ተስፋ አለን ብለዋል። አገራዊ ምክክሩ ከታችኛው ማህበረሰብ ጀምሮ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማሳተፍ ያለው ሂደት የሚስተዋሉ የፖለቲካ ችግሮችን ለመፍታት ያግዛል ብለዋል። በምክር ቤትም ሆነ በፓርቲ ለምክክሩ መሳካት እያደረገ ያለውን አስተዋጽዖ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው ሁሉም ዜጋ በምክክሩ በባለቤትነት ስሜት የነቃ ተሳትፎ ሊያደርግ እንደሚገባ ተናግረዋል። የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ብሌን ገብረመድህን የክልላዊና ከተማ አስተዳደሮች የሚደረገው የምክክር ምዕራፍ በኅብረተሰብ ክፍሎች ውይይት ግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ መጀመሩን አውስተዋል። ይህ ሂደት የምክክር ሃሳብን ማዳበር፣ ማዳመጥ፣ መከባበር፣ የሌሎችን ሃሳብ ማክበር የሚንጸባረቅበት ሲሆን እስካሁን ባለው ሂደት በእቅዱ መሰረት እየሄደ መሆኑን ገልጸዋል። ከነገ ጀምሮ ከኅብረተሰብ ክፍል፣ ከመንግሥት፣ ከተለያዩ ማኅበራትና ተቋማት በአንድ ላይ በሚያደርጉት ውይይት የሃሳብ ብዝሃነትን በማክበርና በመደማመጥ በአጀንዳዎች ላይ እንዲመክሩ አስገንዝበዋል። ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡና ወቅታዊ ችግሮች መፍቻ ምክረ ኃሳቦችን ለማውጣት መመካከር ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ኮሚሽነሯ በአጽኖት አንስተዋል። ውጤታማ የሆነ አገራዊ ምክክር ለማካሄድ ወሳኝ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ ምክክር የሚደረግባቸውን አጀንዳዎች መለየትና በአጀንዳዎች ላይ ከመግባባት መድረስ እንደሆነ የኮሚሽኑ መረጃ ያሳያል።  
አገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን የሚጠበቅብንን ሚና እንወጣለን - ዩኒቨርሲቲዎች
May 31, 2024 109
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 23/2016(ኢዜአ)፦አገራዊ ምክክሩ ችግሮችን በውይይት በመፍታት የአገሪቱን እድገትና ብልጽግና ቀጣይነት ለማረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ ለውጤታማነቱ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ የወልቂጤና የቦንጋ ዩኒቨርሲቲዎች ገለጹ። የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በ2014 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል። ኮሚሽኑ ምክክሩን ለመጀመር የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን አሁን ላይም በአዲስ አበባ የምክክር ምዕራፉን እያካሄደ ነው። የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፋሪስ ደሊል (ዶ/ር) እንደተናገሩት የአገራዊ ምክክር ውጤታማ እንዲሆን ለማድረግ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በተለይም ምሁራን የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ተሰርቷል። በተለይም ለአገር ሰላም፣ እድገትና ብልፅግና መሥራት እንደሚገባና ለዚህም ሁሉም ተመካክሮ፣ ኃሳብ አዋጥቶና ተግባብቶ መሄድ እንዳለበት ዩኒቨርሲቲው ለማኅበረሰቡ ሲያስገነዝብ መቆየቱንም ተናግረዋል። ዩኒቨርሲቲው በቀጣይም ኮሚሽኑን የሚሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት ቁርጠኛ እንደሆነ ተናግረዋል። አገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን ዩኒቨርሲቲው የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነው ያሉት ደግሞ የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጴጥሮስ ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር) ናቸው። ምክክሩ ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ያለው ፋይዳ የጎላ በመሆኑ ለቀጣዩ ትውልድ የተረጋጋች አገር ለማስረከብ ምክክሩን መደገፍ አስፈላጊ እንደሆነም ነው ያስረዱት። ሁሉም ዜጋ ለምክክሩ ስኬት የሚጠበቅበትን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።      
በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው የምክክር ምዕራፍ በእቅዱ መሰረት እየተከናወነ ነው 
May 31, 2024 104
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 23/2016(ኢዜአ)፡-በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው የምክክር ምዕራፍ በእቅዱ መሰረት እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ብሌን ገብረመድህን ተናገሩ። የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው የምክክር ምዕራፍ እንዲሁም ቀጣይ ውይይቶችን አስመልክቶ ለባለድርሻ አካላት ገለጻና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ እያካሄደ ነው። በመድረኩ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ ምሁራን፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ማኅበራት ተወካዮች፣ ከሦስቱ የመንግሥት አካላት የተወከሉ ተወካዮች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል። የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ብሌን ገብረመድህን በአዲስ አበባ የተጀመረው የምክክር ምዕራፍ የነበረውን አጠቃላይ ሂደት ለኢዜአ አብራርተዋል። ግንቦት 21/2016 ዓ.ም ቀን የተጀመረውና ለሦስት ቀናት እየተካሄደ ያለው ምክክር በዛሬው ዕለት ተወካዮች በኅብረተሰብ ክፍል አደራጅተው የተጠናቀረ አጀንዳ በማውጣት ወደ ቀጣይ ክፍል የሚወክሏቸውን ተሳታፊዎች እንደሚለዩ አስረድተዋል። እስካሁን ባለው የምክክር ሂደት ተወካዮች ተረጋግተው በመደማመጥ ጊዜ ሰጥተው የተወያዩበት መሆኑን ጠቅሰው አጠቃላይ የምክክር ምዕራፉ በዕቅዱ መሰረት እየሄደ መሆኑን ተናግረዋል። የኅብረተሰብ ተወካዮች በንዑስ ቡድን ተከፋፍለው ባደረጉት ውይይት የታየው መከባበር፣ መደማመጥ፣ ትግስትና ጥያቄና ኃሳቦችን በሰለጠነው መንገድ ማንሳታቸው ችግሮችን በምክክር መፍታት እንደሚቻል ያሳየ ነው ብለዋል። ይህም ለሰላምና ለምክክር ያላቸውን ዝግጁነት ያሳየ መሆኑን ነው ኮሚሽነሯ የገለጹት።          
በሀገራዊ ምክክሩ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ በዋና ዋና ጉዳዮች የጋራ መግባባት ለመፍጠር መሥራት ይገባል
May 31, 2024 93
አዲስ አበባ ፤ ግንቦት 23/2016(ኢዜአ)፦በሀገራዊ ምክክሩ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ በዋና ዋና ጉዳዮች የጋራ መግባባት ለመፍጠር መረባረብ እንደሚገባ የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሙሉጌታ አበበ ተናገሩ። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው የምክክር ምዕራፍ እንዲሁም ቀጣይ ውይይቶችን አስመልክቶ ለባለድርሻ አካላት ገለጻና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ እያካሄደ ነው። በመድረኩ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ ምሁራን፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ማኅበራት ተወካዮች፣ ከሦስቱ የመንግሥት አካላት የተወከሉ ተወካዮች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል። በመድረኩ ተገኝቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሙሉጌታ አበበ፤ ለሀገራዊ መግባባት ኢትዮጵያ ችግሮቿን በንግግር መፍታት እንዳለባት ምክር ቤቱ በጽኑ ያምናል ብለዋል። ይህንንም ተከትሎ ምክር ቤቱ በአዲስ አበባ በ119 ወረዳዎች ላይ አጀንዳ ለመለየትና አጀንዳ የሚለዩ ሰዎችን ለማስመረጥ የሚያግዙ ሰዎችን ምክር ቤቱ ወክሎ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ይዞ የመጣውን እድል በመጠቀምና ውይይትን ልምድ በማድረግ በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር አበክሮ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት። በመሆኑም በጋራ ምክር ቤት ውስጥ የሚገኙ "ፓርቲዎች አለን የምንለውን ነገር በምክክር ኮሚሽን ተወያይተን ለሀገር ሥጋት የሚሆኑ ጉዳዮችን እናሻሽላለን የሚል ተስፋ አለን" ብለዋል። ምክር ቤቱ ለምክክሩ መሳካት እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው ሁሉም ዜጋ በምክክሩ በባለቤትነት ስሜት የነቃ ተሳትፎ ሊያደርግ እንደሚገባ ተናግረዋል።  
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ33ኛ መደበኛ ስብሰባው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ
May 31, 2024 155
አዲስ አበባ ፤ ግንቦት 23/2016(ኢዜአ)፦ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 33ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ውሳኔዎች፦ 1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅን ለማሻሻል በቀረበ አዋጅ ላይ ነው፡፡ ከህጋዊ እና ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማዕቀፍ ውጪ የቆዩ የፖለቲካ ቡድኖች በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ፍላጎት በሚያሳዩበት ጊዜ እነዚህን አካላት ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ አድርጎ ለመመዝገብ የሚያስችል ስርዓት በነባሩ አዋጅ ላይ አልተካተተም፡፡ በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ እና ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ፍላጎት በሚያሳዩበት ጊዜ መልሶ መመዝገብ የሚያስችል ስርዓት ለመዘርጋት ረቂቅ የአዋጅ ማሸሻያ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡ 2. በመቀጠልም ምክር ቤቱ የተወያየው በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የንብረት ማስመለስ አዋጅ ላይ ነው፡፡ የወንጀል ፍሬ የሆኑ ንብረቶችንና ገንዘቦችን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመያዝ፣ ለማገድ፣ ለመውረስ ወይም ለማስተዳደር የሚያስችል ግልጽና ዝርዝር የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት አስፈላጊ በመሆኑ፤ በተለያዩ አዋጆች ውስጥ ተበታትነው ያሉትን የንብረት ማስመለስ እና አስተዳደር ድንጋጌዎች በአንድ ወጥ ሕግ ውስጥ በማካተት ለአፈጻጸም ምቹ የሆነ ሥርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡   3. ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየው በህገ ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አድርጎ ስለማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በቀረበው አዋጅ ላይ ነው፡፡ በወንጀል የተገኘን ንብረት ህጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀል የደህንነት ስጋት ከመሆኑ በተጨማሪ የፋይናንስ ስርዓቱ የተረጋጋ፣ ግልጸኝነት ያለው፣ ጤናማና ቀልጣፋ እንዳይሆን የሚያደርግ ነው፡፡ ስለሆነም ይህን ወንጀል ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡ 4. በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው የነዳጅ ውጤቶችን የግብይት ሥርዓት ለመደንገግ በቀረበው አዋጅ ላይ ነው፡፡ የነዳጅ ውጤቶች ካላቸዉ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ አንጻር አቅርቦታቸውን፣ ክምችታቸውን፣ ስርጭታቸውን፣ ዋጋቸውን፣ ጥራታቸዉን እና ደህንነታቸውን መቆጣጠር አስፈላጊ በመሆኑ፤ እንዲሁም ከአስመጪ ጀምሮ እስከ ተጠቃሚዎች ድረስ ያለው ግብይት ዘመናዊ፣ ቀልጣፋ፣ ግልጽ፣ ፍትሐዊ እና ተደራሽ የሆነ የአቅርቦት ሰንሰለት እና የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ 3ኛ አመት 12ኛ መደበኛ ስብሰባው በኮሪደር ልማት ሥራዎች ላይ ተወያይቶ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ እና ውሳኔ አሳለፈ
May 30, 2024 141
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 22/2016(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ 3ኛ አመት 12ኛ መደበኛ ስብሰባው በኮሪደር ልማት ሥራዎች ላይ ተወያይቶ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ እና ውሳኔ አሳልፏል። በኮሪደር ልማት ሥራው ሂደት ያለበት ደረጃ እና በሂደት ለሥራው መሳለጥ የተወሰደው የተቀናጀ አመራር ሂደት ለካቢኔ አባላት ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን፤ በውይይቱም ከፍተኛ አመራሩ በጥብቅ የሥራ ዲስፕሊን መመራቱን እና የተሰጠው አቅጣጫ፤ ድጋፍ፣ ክትትል ለከተማው ትልቅ ተሞክሮ ያሳየ መሆኑ ተገልጿል። የልማት ሥራው ከ35ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን በግንባታ ግብአቶች ላይ ሰፊ የገበያ ትስስር የፈጠረ መሆኑ፦   ከ48 ኪ.ሜ በላይ የተሽከርካሪ የመንገድ ልማት፣ 4 የመሬት ውስጥ የእግረኛ መንገዶች የያዘ መሆኑ 96 ኪ.ሜ ሰፋፊ የእግረኛና 100 ኪ.ሜ የብስክሌት መንገዶች በከፍተኛ ጥራት እየተሰራ መሆኑ የ5ኪ.ሜ የመሮጫ ትራክ፣ 48 የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡን የሚያሳልጡ የአውቶቡስ እና የታክሲ ተርሚናሎችንና መጫኛ ማውረጃ ስፍራዎች በግንባታ ሂደት ላይ መሆናቸው በጥቅሉ ከ 240 ኪ.ሜ በላይ የሚሆን የመንገድ እና ተያያዥ መሰረተ ልማት ግንባታዎች በከፍተኛ ጥራት እየተከናወነ መሆኑ ኣቢኔው በጥንካሬ ገምግሟል 70 የከተማን ውበት የሚጨምሩ የህዝብ መናፈሻ ስፍራዎች፣ ፋውንቴኖችና የአረንጏዴ ስፍራዎች፣ የመዝናኛና የመናፈሻ ስፍራዎች፣ የልጆች መጫዎቻና የህዝብ ፕላዛዎች፣ 120 የሚሆኑ የመጸዳጃ ቤቶች፣ የከተማዋን ማዘጋጃዊ አገልግሎቶችን ደረጃ ከፍ የሚያደርጉ የፍሳሽ ማስተላለፊያዎች፣ ከተማችንን የሚመጥኑ የደህንነት ካሜራዎች፣ የብልህ ትራንስፖርት ስርዓት (intelligent transport system) በመሬት ውስጥ የመዘርጋት ስራዎች፤   ከ400 በላይ ህንጻዎች እንዲታደሱ የማድረግ እንዲሁም የከተማዋን ደረጃ የሚመጥኑ የቀለምና የመብራት ስራዎች እና ሌሎች በርካታ ግንባታዎችን በከፍተኛ ትጋት እና የሥራ ጥራት መሰራታቸው ለከተማዋ ትልቅ ተሞክሮ መሆኑን በጥንካሬ ተነስቷል። በግንባታ ላይ የሚገኙት ስራዎች ሲጠናቀቁ አዲስ አበባ እንደ ስሟ ውብና አበባ፣ ለነዋሪዎቿ ምቹ እንዲሁም እየጨመረ የመጣውን የመዲናችንን ዓለም አቀፍ የስበት ማዕከል እና ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የሰነቅነውን ራዕይ በማሳካት ረገድ የላቀ ሚና የሚጫወቱ መሆኑን ካቢኔው ተወያይቷል። ይህንኑ የሥራ ጥንካሬ እና ልማት እውን እንዲሆን በቀጣይ ቀናት በርብርብ እና በተጀመረበት የጥንካሬ መንፈስ ስራውን ማጠናቀቅ እንደሚገባ አቅጣጫ ተቀምጧል። የከተማዋን ነዋሪዎች ንፁህ ምቹ እና ደረጃውን ወደ ጠበቀ መኖሪያ ቤቶች የተደረገው ዝውውር በጥሩ ተሞክሮ የተነሳ ሲሆን አሁንም አልፈው የሚነሱ የህብረተሰብ ቅሬታዎች በትኩረት ማዳመጥ እና ምላሽ መስጠት እንደሚገባ አቅጣጫ ተቀምጧል። የሀገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ብቃት እና ፍጥነት እንዲሁም 24/7 የመስራት ባህል ያደገበት እና በግል ተቋማት እና በመንግስት መተማመን ያሳደገ የሥራ ልምምድ መሆኑም በካቢኔ አባላቱ በጥንካሬ ተነስቷል። ይህን ተሞክሮ ይዞ በቀጣይ የዝናቡ መጠን ሳይጨምር ሥራዎችን በጥራት እና በተጀመረበት ፍጥነት መጨረስ እንደሚያስፈልግ አቅጣጫ ተቀምጧል። የኮሪደር ልማት ግዢን በተመለከተ የከተማውን ሀብት ባማከለ መልኩ በቁጠባ እና በጥራት ከሚሰሩ ድርጅቶች ጋር የተደረገው መናበብ እና ውይይት በጥንካሬ መቀጠል እንዳለበት እና ለሀገር ውስጥ ተቋራጮች የተፈጠረው እድል የከተማዋን ስራ ዕድል እና በአብዛኛው በራስ አቅም ለመገንባት የተሄደበት መሆኑ ተጠቅሷል። አዲስ አበባ ላይ አቅዶ መጨረስ 24/7 መስራት ባህል ብቻ ሳይሆን መደበኛ የስራ ባህል መሆኑን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
የቀይ ባሕር አካባቢን የጂኦ-ፖለቲካል ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ የቀጣናው አገራት ትብብር ወሳኝ ሚና አለው
May 30, 2024 121
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 22/2016(ኢዜአ)፦ የቀይ ባሕር አካባቢን የጂኦ-ፖለቲካል ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ የቀጣናው አገራት ትብብር ወሳኝ ሚና እንዳለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን ገለጹ። ሁለተኛው የቀይ ባሕር ቀጣና ጂኦ-ፖለቲካል ለውጥና የባሕር ደኅንነት እንዲሁም ኢትዮጵያን አማራጭ ወደብ ማግኘት የሚያስችሏትን ዓለም አቀፍ ተሞክሮ የሚዳስስ ውይይት በአዲስ አበባ ተካሂዷል። በመድረኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የስራ ኃላፊዎች፣ የመከላከያ ሠራዊት መኮንኖች፣ በኢትዮጵያ የሀገራት አምባሳደሮች፣ ዓለም አቀፍ ምሁራንና ሌሎች አካላት ተሳትፈዋል። በዚሁ ጊዜ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን፤ የቀይ ባሕርን ቀጣናዊ የጂኦ-ፖለቲካል ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ የተባበረ ጥረት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። የቀይ ባሕር ቀጣናዊ ጂኦ-ፖለቲካል የምክክር መድረክም ኢትዮጵያ ቀጣይነት ላለው ቀጣናዊ ትብብር የሚኖራትን ሚና በማጉላት የጋራ አረዳድ ለመያዝ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ቀጣናን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ በሚደረገው የጋራ ጥረት ጉልህ ድርሻ እንዳላት ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ኢኮኖሚያዊ ዕድገቷን ማስተናገድ የሚችል የባሕር በር ባለቤት ለመሆን የሚደረገው ጥረት ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በዓለም አቀፍ የሰላምና ደኅንነት ዘርፍም በታሪክ የሚታወስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ እንደምትገኝ አንስተዋል። የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ፤ ኢትዮጵያ የቀይ ባሕርን ደኅንነት በማስጠበቅ ቀጣናዊ ትርምስን ለማርገብ የማይተካ ሚና ያላት ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።   የቀይ ባሕር ጂኦ-ፖለቲካል እንቅስቃሴ ኢትዮጵያን ይመለከታል ያሉት አቶ ጃፋር፤ የቀጣናው ሀገራት የሚያደርጉት ኢትዮጵያን ያገለለ የሰላምና ደኅንነት አካሄድም ውጤታማ እንደማይሆን ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቁርኝትና ህልውና ከቀይ ባሕር ጋር የተሳሰረ ስለመሆኑም አብራርተዋል፡፡ በቀይ ባሕር ዙሪያ የሚደረገው ኢትዮጵያን የሚያገል ሂደትም አንድም በውስጥ አርቆ አለማሰብ አሊያም ከታሪካዊ ጠላቶች የሚመነጭ መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህም ቀይ ባሕር ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ፣ ወታደራዊና ስትራቴጂካዊ እንቅስቃሴ ያለውን ወሳኝነት ታሳቢ በማድረግ ቀጣናዊ ፈጣንና ተለዋዋጭ ሁኔታ መሰረት ያደረገ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል። 2ኛው የቀይ ባሕር ጉዳይ ዓለም አቀፍ የምክክር መድረክም ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን ስትራቴጂክ ሚና በማስገንዘብ ብሔራዊ ደኅንነት እና ጥቅሟን ለማስጠበቅ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው አስረድተዋል። በመድረኩም ከላይኛው የቀይ ባሕር ቀጣና እስከ ኤደን ባሕረ ሰላጤ ድረስ የተውጣጡ ምሁራንና የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት መካሄዱ ደግሞ ቀጣናዊ ሰላምና ደኅንነትን ለማስከበር ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል። በዚህ መነሻነትም ቀይ ባሕር ለኢትዮጵያ በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ ሳይሆን የህልውናዋ አካል በመሆኑ በሚደረጉ ትርክቶች፣ ምክክር፣ የሰላምና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳትፎ ታደርጋለች ብለዋል። በምክክር መድረኩ ላይ በቀይ ባሕር ቀጣና የሚስተዋለው የሰላምና ደኅንነት ሥጋት፤ በመርከብ አገልግሎት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖና በፍትሃዊ የወደብ አገልግሎት የዓለም አቀፍ ልምድና ተሞክሮን የሚዳስሱ የውይይት መነሻ ጽሁፎች ቀርበው ምክክር ተካሂዶባቸዋል። በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት በተዘጋጀው መድረክ በቀይ ባሕር ቀጣና አዳዲስ የደኅንነት ሥጋቶችን፣ ፍትሃዊ የወደብ አጠቃቀምና የዓለም አቀፍ ልምድና ተሞክሮዎች ላይ መፍትሔ አመላካች ኃሳቦች ቀርበዋል።  
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሶስት ረቂቅ አዋጆችን ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መራ
May 30, 2024 109
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 22/2016(ኢዜአ)፦ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ29ኛ መደበኛ ስብሰባው ሶስት ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ለዝርዝር እይታ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል፡፡ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 354/9 ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅን አስመልክቶ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ ረቂቅ አዋጁ ለዜጎችና ለውጭ ሀገር ዜጎች የጉዞ ሰነድ፣ ህጋዊ የይለፍ ፈቃድ ጊዜያዊና ቋሚ የመኖሪያ ፍቃድ ለመስጠት የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡   በተጨማሪም በህግ የተከለከሉ ሰዎች በህገ-ወጥ መንገድ ከሀገር እንዳይወጡና ወደ ሀገር እንዳይገቡ ቁጥጥር በማድረግ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን በመቆጣጠር የሀገርን ብሔራዊ ደህንነትና ሉአላዊነት ለማረጋገጥ የሚያግዝ መሆኑንም አብራርተዋል። ምክር ቤቱ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት 354/9 ማሻሻያ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ አዋጅ ቁጥር 19/2016 አድርጎ በሙሉ ድምጽ ለውጭ ግንኙነትና ለሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር ዕይታ መርቷል፡፡   ምክር ቤቱ በሁለተኝነት የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት እንደገና ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ውይይት አድርጓል። በምክር ቤቱ የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በኢፌዲሪ ሕገ መንግስት ከተቀመጡት መሰረታዊ መብቶች አንዱ የሆነውን የዜጎችን የመዘዋወር ነፃነት ማስከበር ያስችል ዘንድ ለኢትዮጵያውያንና ለውጭ ሀገር ሰዎች ሕጋዊ የጉዞ ሰነድና ቪዛ ለመስጠትና ለማረጋገጥ እንዲሁም ብሔራዊ መታወቂያን በመስጠት የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅምና ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያግዝ ረቂቅ አዋጅ መሆኑን ለምክር ቤቱ አብራርተዋል፡፡ ምክር ቤቱም የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት እንደገና ማቋቋሚያ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ አዋጅ ቁጥር 20/2016 አድርጎ ለዝርዝር ዕይታ ለውጭ ግንኙነትና ለሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ መርቷል፡፡ በመጨረሻም ምክር ቤቱ የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ የተወያየ ሲሆን በጉዳዩ ማብራሪያ የሰጡት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ የረቂቅ አዋጁ ዋና ዓላማ አገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋ፣ ተደራሽ፣ ግልጽና ውጤታማ ለማድረግ አንደሆነ አመላክተዋል። የአፈፃፀም ስልቱ ህገ-መንግስቱን መሠረት ያደረገና ዘለቄታዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ የመልካም አስተዳደር መርሆዎችና አሰራሮች በሁሉም ዘርፍ ተግባራዊ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚያግዝ ረቂቅ አዋጅ መሆኑንም ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡ የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባን አስመልክቶ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ አዋጅ ቁጥር 21/2016 ሆኖ ለዝርዝር ዕይታ ለህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ ተመርቷል፡፡ የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው የተመሩትን ረቂቅ አዋጆች ካላቸው ሀገራዊ ፋይዳና ጠቀሜታ እንዲሁም ከአገልግሎት አሰጣጥ አኳያ ያላቸውን መስተጋብር ቋሚ ኮሚቴዎቹ ትኩረት ሰጥተው በዝርዝር እንዲያዩ ማስገንዘባቸውን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
በድሬዳዋ የሚገኙ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአስተዳደሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት ላይ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናገሩ
May 30, 2024 88
ድሬዳዋ ፤ ግንቦት 22/2016(ኢዜአ)፦በድሬዳዋ አስተዳደር እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ተግባራት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ የአመራር አባላት ተናገሩ። በድሬዳዋ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ዛሬ ከአስተዳደሩ ከንቲባና የአመራር አባላት ጋር ለውጡን ተከትሎ እየተካሄዱ በሚገኙ ተግባራት እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል። በዚሁ ወቅት ውይይቱን የመሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር እንደገለጹት፤ ድሬዳዋን የተሻለችና የበለፀገች ለማድረግ ሁሉም ተቀናጅቶ መስራት ይኖርበታል። ድሬዳዋን የመለወጥና ወደ ከፍታ የማሻገር ጉዳይ የአንድ ፓርቲ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ተሳትፎና ርብርብ እንደሚጠይቅም አመልክተዋል። በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የዘጠኝ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች አመራር አባላቱ እንደተናገሩት፤ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተከናወኑ ተግባራት በድሬዳዋ አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ ተረጋግጧል። የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ አስተባባሪ እና የድሬዳዋ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ዮናስ በትሩ እንደገለፁት፤ በድሬዳዋ የሚገኙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በድሬዳዋ የልማት እና የለውጥ ስራዎች ውስጥ እንዲሳተፉ ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል።   "በድሬደዋ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ተጨባጭ ውጤቶች አምጥተዋል፤ እኛም በአስተዳደሩ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ እንድንሳተፍ መደላድል ተፈጥሮልናል" ብለዋል። በድሬዳዋ የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) አስተባባሪ አቶ ወንድወሰን ዘለቀ በበኩላቸው በከንቲባ ከድር ጁሃር የሚመራው የለውጡ አመራር የድሬዳዋ ዘላቂ ሰላምን ከማረጋገጥ በዘለለ የወጣቶችን ጥያቄዎች ለማቃለል የጀመራቸው ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ገልጸዋል። የተጀመሩትን ተግባራት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል። አስተዳደሩ ለገበያ መረጋጋት እና ለስራ አጥነት ጥያቄዎች የተቀናጀ ምላሽ ለመስጠት የበለጠ መስራት እንዳለበት የገለፁት ደግሞ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ፀሐፊ አቶ ገብረስላሴ ሳዕልሶ ናቸው። አክለውም በአስተዳደሩ የዴሞክራሲያዊ ተቋማትን በማጠናከር ረገድ የተጀመሩትን የልማት እና የአሳታፊነት ሂደቶችን ማጠናከር ይገባል ብለዋል። በድሬዳዋ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ኃላፊ አቶ የሺጥላ ሞላ በበኩላቸው አስተዳደሩ የጀመራቸው ስራዎች ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ከመሬት አስተዳደር ጋር ለተያያዙ ችግሮች እና የመኖሪያ ቤቶች ዕጥረት መፍትሄ መስጠት እንዳለበት አንስተዋል።   የመኢአድ የድሬዳዋ የሴቶች አስተባባሪ ወይዘሮ ሀና ቢሆነኝ እንዳሉት በድሬዳዋና በሀገር መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ያካሄዱት ውይይት የተሻለ ነገር ለማምጣት የሚያግዝ በመሆኑ ሊጠናከር እንደሚገባ አመላክተዋል። ድሬዳዋን በአገር አቀፍ ደረጃ በሰላም እና በልማት ተጠቃሽ ለማድረግ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የድርሻችንን እንወጣለን በማለትም አክለዋል።  
ወጣቶች ለአገራዊ ምክክር ሂደቱ ስኬታማነት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገለጹ
May 30, 2024 88
ሆሳዕና/ጋምቤላ/ሐረር ፤ ግንቦት 22/2016 (ኢዜአ)፦ ለአገራዊ ምክክር ሂደቱ ስኬታማነት ሀሳብ በማዋጣትና በማህበረሰቡ ዘንድ ግንዛቤ በመፍጠር የድርሻቸውን እንደሚወጡ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሆሳዕና፣ የጋምቤላና የሐረር ከተሞች ወጣቶች ገለጹ። ኢትዮጵያዊያን በሚያካሂዱት ምክክር ስብራቶቻቸውን ጠግነው፣ የፖለቲካ ችግሮቻቸውን አርመውና ተደማምጠው ከፈተናዎች ለመውጣት ዝግጁ መሆናቸውን እየገለጹ ናቸው። በዚሁ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሆሳዕና፣ የጋምቤላና የሐረር ከተሞች ወጣቶች እንደገለጹት፤ በምክክር ሂደቱ ለሀገር የሚበጁ ሃሳቦችን በማንሳት የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ ተዘጋጅተዋል። "የወጣቱ ትልቁ አስተዋጽኦ ሐሳብ ማዋጣት ነው" የሚትለው በሆሳዕና ከተማ የሴች ዱና ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ቤተልሔም አሰፋ ናት። እንደ ወጣት ቤተልሔም ገለጻ፤ ወጣቱ ነገ እንዲሆንለት የሚፈልገውና ሀገሩ ነገ ምን መሆን እንዳለባት ለመወሰን ሀሳብ ትልቅ አቅም ያለው መሆኑን ነው የገለጸችው። በመሆኑም ራሷን ጨምሮ ወጣቱ ለሀገሩ ለኢትዮጵያ ከመሸሽ ይልቅ ሐሳብ ማዋጣት እንደሚገባ ነው የመከረችው። በሚደረጉ ቅስቀሳዎች ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን ከጎሮቤት አንስቶ ከቀበሌ እስከ ዞን ድረስ በማህበረሰቡ ዘንድ ሀሳቡን በማስረጽና ግንዛቤ በመፍጠር ላይ በርትቶ እንደሚሰራ የገለጸው ደግሞ ከጋምቤላ ክልል አስተያየቱን ለኢዜአ የሰጠው ወጣት ኮሬ አጄሽዋ ነው።   በተለያየ መልኩ የሚገለጡ ልዩነቶችን ለመፍታት "ኮሚሽኑ ብዙ ሥራ ይጠበቅበታል" ያለው ወጣት ኮሬ፤ ለዚህ ደግሞ ወጣቶች የሚጠበቅብንን ሃላፊነት ከኮሚሽኑ ጋር ጠንክረን እንሰራለን ብሏል። በሀገራችን ዘርፈ-ብዙ ጉዳዮች ላይ በእርጋታና ስክነት በመምከር የመፍትሔው አካል ለመሆን መዘጋጀቱን በማከል። ኮሚሽኑ የዘረጋው የምክክር መድረክ ሰው ያለምንም ፍርሃትና መሸማቀቅ ሀሳቡን አውጥቶ የሚገልጽበት መድረክ መሆኑን ያነሳው ደግሞ የሐረር ከተማ ወጣት ዳዊት ተመስገን ነው።   ወጣት ዳዊት የምክክር መድረኩ በተለይ ወጣቱ ሐሳቡን በሚገባ አውጥቶ ከወገኖቹ ጋር የሚጋራበት መሆኑን ገልጾ፤ ወጣቱ "ሀሳቡን በማዋጣት ያልተግባባንባቸውን ጉዳዮች በመመካከር መግባባት እንደምንችል የተሰናዳ መድረክ ነው" ብሏል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሁሉንም ወረዳዎች የህብረተሰብ ክፍሎች የወከሉ ተሳታፊዎች የአጀንዳ ሀሳቦቻቸው ላይ የሚወያዩበት የምክክር ምዕራፍ ትናንት በይፋ መጀመሩ ይታወሳል፡፡    
የምክክር ሂደቱ ሁሉን አቀፍና አሳታፊ በመሆኑ ለስኬታማነቱ በባለቤትነት ስሜት እየሰራን ነው
May 30, 2024 96
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 22/2016(ኢዜአ)፦ የምክክር ሂደቱ ሁሉን አቀፍና አሳታፊ በመሆኑ ለስኬታማነቱ በባለቤትነት ስሜት እየሰራን ነው ሲሉ በአዲስ አበባ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ተሳታፊ አካል ጉዳተኞች ገለጹ። በአዲስ አበባ ከሚገኙ 119 ወረዳዎች የተውጣጡ የማኅበረሰብ ተወካዮች የተሳተፉበት አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ በይፋ ተጀምሯል፡፡   ኮሚሽኑ እስካሁን ባለው ሂደት የቅድመ ዝግጅትና የዝግጅት ምዕራፉን በስኬት አጠናቆ የምክክር ምዕራፉን የጀመረ ሲሆን በሂደቱ የአጀንዳ ግብአት የሚዘጋጅበትና በሀገራዊ ጉባዔ የሚወከሉ ተሳታፊዎች የሚመርጡበት ይሆናል። በምክክር ሂደቱ የአካል ጉዳተኞች ተወካዮች መካከል ያብባል ባሳዝን፤ ምክክሩ የሀገር መፃኢ ተስፋ የተጣለበት፣ የምንፈልገውን ሰላም የምናረጋግጥበት ታሪካዊ አጋጣሚ በመሆኑ በንቃት እየተሳተፍን ነው ብለዋል። ሌላኛው አስተያየት ሰጭ ኤልያስ ገድሉ፤ የምክክር ሂደቱ ሁሉን አቀፍና አሳታፊ በመሆኑ በባለቤትነት ስሜት እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።   አቶ እንዳለ ደነቀ እና አቶ መዝገቡ አብዩ፤ በበኩላቸው ለችግሮቻችን የመፍትሄው አካል ለመሆን ውይይትን አማራጭ ማድረግ የግድ ነው ሲሉ ተናግረዋል።   በአዲስ አበባ ከተማ በሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ከ2 ሺህ 500 በላይ ተወካዮች እየተሳተፉ ሲሆን ሂደቱ በአካታችነት፣ ግልጽነት፣ አሳታፊነት የሚቀጥል መሆኑን ኮሚሽኑ አረጋግጧል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም