በሀገራዊ ምክክሩ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ በዋና ዋና ጉዳዮች የጋራ መግባባት ለመፍጠር መሥራት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በሀገራዊ ምክክሩ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ በዋና ዋና ጉዳዮች የጋራ መግባባት ለመፍጠር መሥራት ይገባል
አዲስ አበባ ፤ ግንቦት 23/2016(ኢዜአ)፦በሀገራዊ ምክክሩ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ በዋና ዋና ጉዳዮች የጋራ መግባባት ለመፍጠር መረባረብ እንደሚገባ የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሙሉጌታ አበበ ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው የምክክር ምዕራፍ እንዲሁም ቀጣይ ውይይቶችን አስመልክቶ ለባለድርሻ አካላት ገለጻና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ ምሁራን፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ማኅበራት ተወካዮች፣ ከሦስቱ የመንግሥት አካላት የተወከሉ ተወካዮች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በመድረኩ ተገኝቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሙሉጌታ አበበ፤ ለሀገራዊ መግባባት ኢትዮጵያ ችግሮቿን በንግግር መፍታት እንዳለባት ምክር ቤቱ በጽኑ ያምናል ብለዋል።
ይህንንም ተከትሎ ምክር ቤቱ በአዲስ አበባ በ119 ወረዳዎች ላይ አጀንዳ ለመለየትና አጀንዳ የሚለዩ ሰዎችን ለማስመረጥ የሚያግዙ ሰዎችን ምክር ቤቱ ወክሎ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ይዞ የመጣውን እድል በመጠቀምና ውይይትን ልምድ በማድረግ በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር አበክሮ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በመሆኑም በጋራ ምክር ቤት ውስጥ የሚገኙ "ፓርቲዎች አለን የምንለውን ነገር በምክክር ኮሚሽን ተወያይተን ለሀገር ሥጋት የሚሆኑ ጉዳዮችን እናሻሽላለን የሚል ተስፋ አለን" ብለዋል።
ምክር ቤቱ ለምክክሩ መሳካት እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው ሁሉም ዜጋ በምክክሩ በባለቤትነት ስሜት የነቃ ተሳትፎ ሊያደርግ እንደሚገባ ተናግረዋል።