ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው የምክክር ምዕራፍ በእቅዱ መሰረት እየተከናወነ ነው 

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 23/2016(ኢዜአ)፡-በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው የምክክር ምዕራፍ በእቅዱ መሰረት እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ብሌን ገብረመድህን ተናገሩ። 

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው የምክክር ምዕራፍ እንዲሁም ቀጣይ ውይይቶችን አስመልክቶ ለባለድርሻ አካላት ገለጻና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ እያካሄደ ነው። 

በመድረኩ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ ምሁራን፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ማኅበራት ተወካዮች፣ ከሦስቱ የመንግሥት አካላት የተወከሉ ተወካዮች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል። 

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ብሌን ገብረመድህን በአዲስ አበባ የተጀመረው የምክክር ምዕራፍ የነበረውን አጠቃላይ ሂደት ለኢዜአ አብራርተዋል።

ግንቦት 21/2016 ዓ.ም ቀን የተጀመረውና ለሦስት ቀናት እየተካሄደ ያለው ምክክር በዛሬው ዕለት ተወካዮች በኅብረተሰብ ክፍል አደራጅተው የተጠናቀረ አጀንዳ በማውጣት ወደ ቀጣይ ክፍል የሚወክሏቸውን ተሳታፊዎች እንደሚለዩ አስረድተዋል።

እስካሁን ባለው የምክክር ሂደት ተወካዮች ተረጋግተው በመደማመጥ ጊዜ ሰጥተው የተወያዩበት መሆኑን ጠቅሰው አጠቃላይ የምክክር ምዕራፉ በዕቅዱ መሰረት እየሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

የኅብረተሰብ ተወካዮች በንዑስ ቡድን ተከፋፍለው ባደረጉት ውይይት የታየው መከባበር፣ መደማመጥ፣ ትግስትና ጥያቄና ኃሳቦችን በሰለጠነው መንገድ ማንሳታቸው ችግሮችን በምክክር መፍታት እንደሚቻል ያሳየ ነው ብለዋል።

ይህም ለሰላምና ለምክክር ያላቸውን ዝግጁነት ያሳየ መሆኑን ነው ኮሚሽነሯ የገለጹት። 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም