ቀጥታ፡

በምክክር ምዕራፍ የአጀንዳ ማሰባሰብ የታየው አካታችና አሳታፊ ሂደት የሚበረታታ ነው-የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 24/2016(ኢዜአ)፦ በሀገራዊ የምክክር ምዕራፍ የአጀንዳ ማሰባሰብ የታየው አካታችና አሳታፊ ሂደት የሚበረታታ  መሆኑን የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት ዳይሬክተርና የሴቶች ድምጽ በአገራዊ ምክክር ጥምረት ሰብሳቢ ሳባ ገብረመድህን ተናገሩ።

ዳይሬክተሯ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ የሴቶች ድምጽ በአገራዊ ምክክር ጥምረት ከ50 በላይ ድርጅቶችን አካቶ የምክክር ሂደቱ ከተጀመረ አንስቶ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል።

ጥምረቱ በአዲስ አበባ በየወረዳው የተለያዩ የሴቶች መድረኮችን በማዘጋጀት በምክክሩ መነሳት ያለባቸው አጀንዳዎች ላይ ውይይት ማድረጉን ገልጸዋል።

በመዲናዋ የተጀመረው የሀገራዊ ምክክር ምዕራፍ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ሴቶችን ጨምሮ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ አካታችነትን ያረጋገጠና የሚበረታታ እንደሆነ ገልጸው፥ ይህም እስከመጨረሻው በስኬት እንዲቀጥል ሁሉም በጎ ሚና መጫወት አለበት ብለዋል።

በአሁኑ ወቀት በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የሚደረጉ የምክክር ሂደቶች ለዋናው ሀገራዊ ምክክር መሰረት እንደሚጥሉ ያነሱት ዳይሬክተሯ፥  ምክክር በዴሞክራሲዊና ሰላማዊ መንገድ መግባባትን ለመፍጠርና ፍትህን ለማምጣት ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።

ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ሀገርን በዘላቂነት ከግጭትና ሌሎች መሰረታዊ ችግሮች ለማላቀቅ ትልቅ እድል ይዞ የመጣውን አገራዊ ምክክር በአግባቡ መጠቀምና ለስኬቱ በኃላፊነት መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ሴቶች ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የመፍትሔ አካል በመሆናቸው ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉም ነው ወይዘሮ ሳባ ገብረመድህን የጠየቁት።

እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አካታች ሀገራዊ ምክክሮችን ማካሄድ የተሻለ ሀገራዊ መግባባትን ለመገንባት በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 ተቋቁሞ ወደ ስራ የገባው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አሁን ላይ ሶስተኛውን ምዕራፍ መተግበር ጀምሯል።

አካታች የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ የቅድመ ዝግጅት፣ ዝግጅት፣ የምክክር ሂደት፣ የትግበራና ክትትል ምዕራፎች አሉት።

የምክክር ምዕራፍ አካል የሆነው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ በይፋ የተጀመረ ሲሆን የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ወኪሎች ለሶስት ቀናት በአጀንዳ ሀሳቦች ላይ ሲያደርጉት የነበረውን ውይይት አጠናቀዋል።

በዚህም በከተማ አስተዳደር ደረጃ በሚካሄደው ምክክር እንዲንፀባረቁላቸው የፈለጓቸውን አጀንዳዎች በመለየት ለኮሚሽኑ ያስረከቡ ሲሆን፥ አጀንዳዎቻቸውን በምክክሩ ላይ የሚያቀርቡ 121 ተወካዮቻቸውን መምረጣቸውን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታውቋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም