ወጣቶች ለአገራዊ ምክክር ሂደቱ ስኬታማነት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገለጹ

ሆሳዕና/ጋምቤላ/ሐረር ፤ ግንቦት 22/2016 (ኢዜአ)፦ ለአገራዊ ምክክር ሂደቱ ስኬታማነት ሀሳብ በማዋጣትና በማህበረሰቡ ዘንድ ግንዛቤ በመፍጠር የድርሻቸውን እንደሚወጡ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሆሳዕና፣ የጋምቤላና የሐረር ከተሞች ወጣቶች ገለጹ።

ኢትዮጵያዊያን በሚያካሂዱት ምክክር ስብራቶቻቸውን ጠግነው፣ የፖለቲካ ችግሮቻቸውን አርመውና ተደማምጠው ከፈተናዎች ለመውጣት ዝግጁ መሆናቸውን እየገለጹ ናቸው።

በዚሁ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሆሳዕና፣ የጋምቤላና የሐረር ከተሞች ወጣቶች እንደገለጹት፤ በምክክር ሂደቱ ለሀገር የሚበጁ ሃሳቦችን በማንሳት የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ ተዘጋጅተዋል።

"የወጣቱ ትልቁ አስተዋጽኦ ሐሳብ ማዋጣት ነው" የሚትለው በሆሳዕና ከተማ የሴች ዱና ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ቤተልሔም አሰፋ ናት። 

እንደ ወጣት ቤተልሔም ገለጻ፤ ወጣቱ ነገ እንዲሆንለት የሚፈልገውና ሀገሩ ነገ ምን መሆን እንዳለባት ለመወሰን ሀሳብ ትልቅ አቅም ያለው መሆኑን ነው የገለጸችው።

በመሆኑም ራሷን ጨምሮ ወጣቱ ለሀገሩ ለኢትዮጵያ ከመሸሽ ይልቅ ሐሳብ ማዋጣት እንደሚገባ ነው የመከረችው። 

በሚደረጉ ቅስቀሳዎች ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን ከጎሮቤት አንስቶ ከቀበሌ እስከ ዞን ድረስ በማህበረሰቡ ዘንድ ሀሳቡን በማስረጽና ግንዛቤ በመፍጠር ላይ በርትቶ እንደሚሰራ የገለጸው ደግሞ ከጋምቤላ ክልል አስተያየቱን ለኢዜአ የሰጠው ወጣት ኮሬ አጄሽዋ ነው። 


 

በተለያየ መልኩ የሚገለጡ ልዩነቶችን ለመፍታት "ኮሚሽኑ ብዙ ሥራ ይጠበቅበታል" ያለው ወጣት ኮሬ፤ ለዚህ ደግሞ ወጣቶች የሚጠበቅብንን ሃላፊነት ከኮሚሽኑ ጋር ጠንክረን እንሰራለን ብሏል።

በሀገራችን ዘርፈ-ብዙ ጉዳዮች ላይ በእርጋታና ስክነት በመምከር የመፍትሔው አካል ለመሆን መዘጋጀቱን በማከል።

ኮሚሽኑ የዘረጋው የምክክር መድረክ ሰው ያለምንም ፍርሃትና መሸማቀቅ ሀሳቡን አውጥቶ የሚገልጽበት መድረክ መሆኑን ያነሳው ደግሞ የሐረር ከተማ ወጣት ዳዊት ተመስገን ነው።


 

ወጣት ዳዊት የምክክር መድረኩ በተለይ ወጣቱ ሐሳቡን በሚገባ አውጥቶ ከወገኖቹ ጋር የሚጋራበት መሆኑን ገልጾ፤ ወጣቱ "ሀሳቡን በማዋጣት ያልተግባባንባቸውን ጉዳዮች በመመካከር መግባባት እንደምንችል የተሰናዳ መድረክ ነው" ብሏል። 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሁሉንም ወረዳዎች የህብረተሰብ ክፍሎች የወከሉ ተሳታፊዎች የአጀንዳ ሀሳቦቻቸው ላይ የሚወያዩበት የምክክር ምዕራፍ ትናንት በይፋ መጀመሩ ይታወሳል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም